Friday, December 1, 2023

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የሚዘነጉ ስደተኞች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓለም ዛሬ ላይ ተጨንቃለች፡፡ ከበለጸጉት እስከ ደሃ አገሮች ድረስ መነጋገሪያና ሥጋት የሆነው ኮሮና ኖቭል ቫይረስ፣ አገሮች ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ እያስገደደ ነው፡፡ በድንበሮችም ብቻ አላበቃም፣ ሰዎች በራቸውን ዘግተው እንዲቀመጡም አድርጓል፡፡

ሁሉም ራሱን ለማዳን በሚሯሯጥበት በአሁኑ ሰዓት፣ በዓለም ቅድሚያ የተሰጠው የሕክምና ቁሳቁስ ላይ ቢሆንም፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከፊት የተደቀነ ችግር ሆኗል፡፡ አገሮችና ሕዝቦች ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ምግብ ከአገራቸው እንዳይወጣ እስከማድረግም ደርሰዋል፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ የሚዘነጉ ሕዝቦች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

በአሜሪካ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎቿ አሁን ላይ ሥራ አጥ በመሆናቸው የምግብና ሌሎች ዕርዳታን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ቀዳሚ በሆነችው አሜሪካ የተከሰተው ቀውስ፣ በማደግ ላይ ባሉና በደሃ አገሮች የበረታ ነው፡፡ በኮሮና ኖቭል ቫይረስ ወረርሽ ምክንያት ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ እንደሚጋለጡም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አስታውቀዋል፡፡

መሥራት የሚችሉትን ሁሉ ከገበያ ያስወጣው ወረርሽኝ፣ መሥራት የማይችሉትን ከባድ ፈተና ከቷል፡፡ ይህ ሲሆን አገሮች ዜጎቻቸውን በሕክምናም፣ በምግብም ለመድረስ ደፋ ቀና ሲሉ፣ ስደተኞች ለበሽታው ሆነ ለረሃቡ ተጋላጭ የመሆናቸውን ያህል አልተደረሰላቸውም፡፡ ይልቁንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተዘነጉ ሆነዋል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን ለመጠበቅ ራሳቸውን አግልለዋል፣ ማኅበራዊ ርቀትን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ይህ ለስደተኞች የሚታሰብ ብሎም የሚተገበር አይደለም፡፡

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የሚዘነጉ ስደተኞች

በዓለም 25.9 ሚሊዮን ስደተኞችና 3.5 ሚሊዮን የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁትን ጨምሮ 70.8 ሚሊዮን ሕዝብ በግዳጅ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ በርካቶችም በስደተኛ መጠለያ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በመጠለያዎቹ ያለው የሕክምና አቅርቦት አናሳ መሆኑ ደግሞ ስደተኞቹን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ አድርጓቸዋል፡፡ በጦርነት ሳቢያ የተሰደዱ በአሥር ሺዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተጨናነቁ ካምፖች ውስጥ ይኖራሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሲሲሊ ፓውሊ፣ ስደተኞች በቫይረሱ እንዳይጠቁ ለማስቻል ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

የካምፕ ነዋሪዎች ንፅህና መጠበቅን ለማረጋገጥም፣ ንፁህ ውኃና ሳሙና እንዲሁም  ፀረ ተዋህሲያን ርጭት እንዲኖር እየተደረገም ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም 33 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን፣ የካምፖቹን ሁኔታ ለማሻሻልና የጤና ባለሙያዎችን ለማሠልጠን የሚውልም ይሆናል፡፡

በተመድም ሆነ በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስደተኞችን ለመርዳት የተለያዩ ሥራዎች ስለመከናወናቸው ቢነገርም፣ በስደተኛ ካምፖች ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው፡፡

በዓለም ከሚገኙ የስደተኛ ካምፖች አብዛኞቹ በችግር የተተበተቡ ናቸው፡፡ ከአቅማቸው በላይ መያዝ፣ የጤና ችግር መከሰት፣ የውኃና የምግብ አቅርቦት እጥረት፣ እርስ በርስ ግጭትና ሌሎችም የስደተኛ ካምፖች መገለጫዎች ናቸው፡፡

ኮሮናን በተመለከተ ደግሞ ማኅበራዊ መራራቅም ሆነ በተደጋጋሚ እጅን መታጠብ ሊተገበር የሚችል አይደለም፡፡ ካምፖች ሲታዩም ከሚነገርላቸው በባሰ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የያዙ ናቸው፡፡

በግሪክ ሊስቦስ የሚገኘው ሞሪያ ስደተኞች ካምፕ ሲገነባ 3,000 ስደተኞችን ይይዛል ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ላይ በድንኳንና በሼድ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ከ20,000 በላይ ስደተኞች በካምፑ ታጭቀዋል፡፡ ስድስት አባላት ያላቸው አንዳንድ ቤተሰቦች በአንድ ድንኳን ውስጥ ሆነው ማየትም የተለመደ ነው፡፡ የሚበላና የሚጠጣ ለማግኘት ረዥም ሰልፍ መሰለፍ የተለመደ በመሆኑ፣ በካምፑ ነዋሪዎች ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ይቻላል ለማለት አያስደፍርም፡፡

በሞሪያ ስደተኞች ካምፕ የአፍና አፍንጫ ማስክም ሆነ ሳኒታይዘር ማግኘት ቅንጦት ነው፡፡ ይህ ቀርቶ አፋጣኝ ሕክምና ማግኘት የሚገባቸው ሕሙማን እንኳን የሕክምና ዕርዳታ እያገኙ አይደለም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ችግር በባንግላዴሽ ኮክስ ባዛር በሚገኘው ሮሃኒንጋ የስደተኞች ካምፕም አለ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሮሃኒንጋ ስደተኞች በሚገኙበት ካምፕ፣ እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ስለመኖሩ ባይነገርም፣ በባንግላዴሽ የኮሮና ቫይረስ ሞት ተመዝግቧል፡፡ በካምፑ የሚገኙ ስደተኞችም ስለቫይረሱ ምንም መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡

በሰሜን ሶሪያና የመን ያለው ሁኔታም አስከፊ ነው፡፡ ሁለቱም አገሮች በግጭት ውስጥ ያሉ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ዜጎቻቸው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከሰሜን ሶሪያ የተፈናቀሉና በቱርክ ድንበር አካባቢ ድንኳን በመጣልና በባዶው ሜዳ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በሰሜን ሶሪያ በሚገኝ ካምፕ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ሲኖሩ፣ እስካሁን ኮሮና ቫይረስ አልተከሰተም፡፡ ሆኖም ቢከሰት የሶሪያ መንግሥት ይህንን መመከት የሚችል አቅም እንደሌለው የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡

የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከገባች አምስት ዓመታትን ባስቆጠረችው የመን የጤና ሥርዓት የለም ማለት እንደሚቻል ተመድ ይገልጻል፡፡ በየመን 50 በመቶ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡ ሕዝቡ በተለያዩ ኢንፌክሽኞች የተጠቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኮሮና ቫይረስ በስደተኞች ካምፕ ቢገባ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል የሚል ፍርሃትም አለ፡፡

ኮሮና ቫይረስ የዓለም ሥጋት ከሆነ አንስቶ ስደተኞች መዘንጋታቸው አግባብ አለመሆኑንና ዓለም ፊቱን ወደ ስደተኞችም ማዞር እንደሚገባው ተመድ ያስታወቀ ሲሆን፣ በ70 ያህል አገሮች እየተካሄደ የሚገኝ የርስ በርስ ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኖርዌይ ሪፊውጂ ካውንስል እንደሚለው፣ አሁን ላይ በስደተኞች ካምፕ ያለውን ሁኔታ ማስተካከል ካልተቻለ ስደተኞች በኮሮና ቫይረስ ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በላቀ እንደሚጠቁ በመጠቆም፣ ችግሩን በጋራ ለመወጣት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረባረብ ጠይቋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የሚዘነጉ ስደተኞች

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -