በተመስገን ተጋፋው
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የፊት መሸፈኛ ማስክ እየሠራ እንደሚገኝ የአቡጊዳ የሮቦቲክና የቴክኖሎጂ ማዕከል አስታወቀ፡፡
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ታሪኩ ፈቃዱ (ዶ/ር)፣ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚረዳው የፊት መሸፈኛ ማስክ የተሠራው የጤና ባለሙያዎች ተጋላጭ ስለሆኑ በቅድሚያ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ታሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፊት መሸፈኛ ማስኩንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ጋር በመሆን እየሠሩ እንደሚገኙ ዶ/ር ታሪኩ አስረድተዋል፡፡
ምርቱን በብዛት ለማቅረብ እንዲቻል የፕላስቲክ ፋብሪካዎችን በማናገርና አብሮ ለመሥራት ሒደት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ታሪኩ፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚያገለግለውን አንድ የፊት መሸፈኛ ማስክ ለመሥራት ሁለት ሰዓት ያህል የሚፈጅ ሲሆን፣ በቀን አሥር ማስኮችን እንደሚያመርቱ አክለዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ ዶ/ር ታሪኩ አሳስበዋል፡፡
የአቡጊዳ የሮቦቲክና የቴክኖሎጂ ማዕከል መሥራች ምሕረት ዋልጋ (ኢንጂነር)፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚያገለግል የፊት ማስክ በመሥራት፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሙከራ ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
ለማስኩ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንደማያስከፍሉና ዲዛይንኑንና አሠራሩን ለመማር የሚፈልጉ ሰዎች በነፃ መማር እንደሚችሉም አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት በጥቂቱ ለማገዝም እጅን በ25 ሳንቲ ሜትር ርቀት በማስጠጋት ሳኒታይዘር መርጨት የሚችል ሮቦት ሠርተው ማቅረባቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡