Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አካል ቢራራቅም በመንፈስ አንድ ነን!

የማይቀርበት የእንጀራ ጉዳይ ሆኖ ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን ወደ አውቶቡስ ተራ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ በቃ እስኪባል የዕለት ጉርስ ፍለጋ እግር ይኳትናል፡፡ የሰው ልጅ በሁለት ጽንፍ ተወጥሮ ሩሁን እንደሳተ ጎዳናው ላይ ቢንቀሳቀስም፣ የሕይወት ጥሪ በደመነፍስ እየመራው የዘወትር እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ አልተገታም፡፡ ይህች ነፍስ ከሥጋ ተነጥላ እስክትሄድ ድረስ፣ የሰው ልጅ በድካሙ ይኖር ዘንድ ተፈርዶበታልና መንከላወሱ የግድ ነው፡፡ አካሉ ከወገኑ በዕርምጃዎች ፈቀቅታ ቢራራቅም፣ በመንፈስ ላለመራራቅ ይባትላል፡፡ ሕይወት እንድትቀጥል ደግሞ እንጀራን ተጋርቶ መብላት የግድ ይላል፡፡ የጉዞው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ በታክሲያችን ውስጥ ሁለት ሰዎች ገብተን ወያላው አራት ሰዎች ለመጨመር በተለመደው ጥሪ ‹አንድ ሰው የቀረ…› እያለ ሲጮህ የተሰላቸው ወጣቱ ሾፌር፣ ‹‹እየተንቀረፈፍክ መሥራት አቅቶህ ካስቸገርከኝ እንደ ጓደኞችህ ተቀንሰህ ትቦዝናለህ፤›› ሲለው፣ ‹‹እንዴ መንግሥት ከሰበሰበው ዕርዳታ አንቀባሮ ያኖረኛል… እኔም በበጎ ፈቃደኝነት አገለግለዋለሁ…›› ይለዋል እየተጠቃቀሱ፡፡ መግባባት ማለት ይኸው አይደል!

በዚህ መሀል አምስት የተጣደፉ ሰዎች ተንጋግተው ገብተው የሁለቱን ንትርክ ሲያረግቡ፣ አንድ ሰው ትርፍ ነው ተብሎ ሌላ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ዘግይተው ከተሳፈሩት አንዱ፣ ‹‹እናንተ ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ መጠቅጠቅ ትታችሁ ታክሲው ሳይሞላ ትርፍ አንጭንም ማለት ያመጣችሁት…›› በማለት ዓይኑን እያጉረጠረጠ ሲጠይቅ ሾፌሩ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አባቴ አልሰማህም ወይስ ከማርስ ገና ዱብ ማለትህ ነው?›› ሲለው ሰውየው ምንም ባልተፈጠረ ስሜት፣ ‹‹ምኑን ነው ያልሰማሁት?›› ሲል እውነትም እዚህ ምድር ላይ ያልነበረ ይመስል ነበር፡፡ አንዳንዱ እኮ ጦሱ ለሌላው ባይተርፍ ታድሎ ያሰኛል!

ወያላው በሰውየው ንግግር የተገረመ መስሎ፣ ‹‹ሳበው!›› ሲለው ሾፌሩ ማርሹን አስገብቶ በባዶው ጎዳና ላይ ታክሲውን አስወነጨፈው፡፡ ያ ግራ የተጋባ ሰው አሁንም በበፊቱ ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹ለመሆኑ እናንተ ሰዎች ታክሲው ሳይሞላ የሽርሽር ጉዞ ያስመሰላችሁት ነዳጅ ተገኝቶ ነው እንዴ?›› በማለት ሌላ ጥያቄ ሲያቀርብ ወያላው ፈገግ እያለ፣ ‹‹ነዳጅ ብቻ ሳይሆን የእማማ ኢትዮጵያ ምድር ወርቅ ትላለህ አልማዝ፣ ዶላር ትላለህ ዩሮ፣ ብቻ ምን አለፋህ እንደ ጉድ እየወጣበት ስለሆነ ነው ከዚህ አውቶቡስ ተራ መቶ ብር ከፍለህ የምትሄደው…›› ሲለው፣ ሰውየው ምን ጉድ ነው የምሰማው ብሎ ነው መሰል ዞር ዞር እያለ ያየን ጀመር፡፡ በጉድ ዘመን ምን የማይታይ አለ!

ከሾፌሩ አጠገብ ብቻውን ተደላድሎ የተቀመጠ ጎልማሳ አንገቱን ወደ ኋላ መለስ አድርጎ፣ ‹‹ሰውየው በጣም ግራ የገባህ ትመስላለህ ምን ሆነህ ነው?›› አለው፡፡ ሰውየው አሁንም ዞር ዞር ብሎ ካየ በኋላ፣ ‹‹እናንተ እኮ እየፈራችሁ ነው እንጂ ችግር ሳይኖርባችሁ አይቀርም…›› ብሎ ከት ብሎ ሲስቅ ጠረጠርን፡፡ ምናልባት የአዕምሮ ሁከት ይኖርበት ይሆናል ብሎ ጎልማሳው፣ ‹‹ለመሆኑ ከነጋ መድኃኒትህን ወስደሃል?›› ሲለው፣ ‹‹እጄን መታጠብ አልፈልግም እንጂ መድኃኒቴን እንኳ አልረሳም…›› ሲለው ልባችን ተሰበረ፡፡ በዚህ ጊዜ እንዲህ ያሉትን ወገኖቻችንን ካልጠበቅን ሰው መሆናችን ከንቱ ነው!

ሰውየው ስድስት ኪሎ ወርዶ ሲሰናበተን በከንፈር መጠጣ ስንሸኘው፣ ‹‹እጃችሁን ብቻ ሳይሆን ልባችሁንም አፅዱ እባካችሁ…›› ሲለን መብረቅ እንደ መታው ክው ብለን ቀረን፡፡ ታክሲው በጎደለ ሞልቶ ሲንቀሳቀስ አንደኛው በመስኮት ካየው ውጭ ካለ ሰው ጋር ሰላም ሲባባል አጠገቡ ያለው ጓደኛው፣ ‹‹ይኼ ሰውዬ አሁንም እዚያ ነው የሚሠራው?›› ሲለው፣ ‹‹አዎን! ሰሞኑን ቤታችሁ ሆናችሁ ሥሩ ከተባሉት ውስጥ አንዱ ነው…›› እያለ ሲመልስ ወያላው ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ተጠያቂው ወያላውን፣ ‹‹ምን ያስቅሃል?›› ብሎ ሲያፈጥበት፣ ‹‹ሰሞኑን የሰማሁት ቀልድ ትዝ ብሎኝ ነው…›› ብሎ አሁንም ሲስቅ ሾፌሩ፣ ‹‹አቶ አያልቅበት ንገረንና እኛም እንሳቅ እስቲ በዚህ የጭንቀት ጊዜ…›› ብሎ አደፋፈረው፡፡ የሚያደፋፍር ጠፍቶ እንጂ ለምለም ምድር ይዘን እንቸገር ነበር!

ወያላው መደገፊያውን ካመቻቸ በኋላ፣ ‹‹በዚህ የኮሮና መዓት ምክንያት ከመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ ገሚሱ ከቤታችሁ ሆናችሁ ሥሩ ተብለው መሸኘታቸው ትዝ አላችሁ?›› ሲል፣ ሁላችንም ለቀልዱ ቸኩለን በኅብረት፣ ‹‹አዎን እናስታውሳለን!›› ስንለው ወያላው አሁንም ከት ብሎ ሲስቅ፣ የእኛ መጓጓት ይሁን ወይም የቀልዱ አስቂኝ መሆን አልገባንም፡፡ ነገር ግን ወያላው ትን እስኪለው መሳቁን ቀጠለ፡፡ ‹‹አሥራ ሁለት ሆነን አንዲት ቆንጆ ወደን፣ እሷ ትስቃለች እኛ ተጨንቀን›› የተባለው መቼ ይሆን!

ወያላው ሳቁ ገርገብ ሲልልት፣ ‹‹የእኛ አገር ነገር እኮ ያስቃል…›› ብሎ ሲጀምር አንዱ የቸኮለ ጎረምሳ፣ ‹‹እባክህ ወደ ገደለው ግባ በሰስፔንስ አትግደለን…›› አለው፡፡ ወያላውም ፈገግ ብሎ፣ ‹‹ፍሬንድ ተረጋጋ! ይኸውላችሁ ቤቱ የሚበላው የረባ ነገር የሌለው ምስኪን የመንግሥት ሠራተኛ፣ ከእነ ደመወዙ ከቤትህ ትሠራለህ ተብሎ ሆዱ እያወቀው ዕረፍት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዳንዱ በጠዋት ከቤት ወጥቶ ማታ መሸታ ቤት ጎራ እያለ የሚገባ አባወራ ቤት መዋል ሲጀምር፣ አሁን ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር መግባባት አቅቶት ይወራጫል፡፡ ሌላው ቤቱ ውስጥ የሚያየው ቁሳቁስ በትውስት የመጣ ይመስል በድንጋጤ እያየ፣ የሚስቱን ታታሪነት መቀበል ከብዶታል…›› ብሎ ገልመጥ ሲያደርገን ማቀርቀር ጀመርን፡፡ ልካችንን የሚነግረን ጠፍቶ ነው እንጂ እኛ እኮ ብዙ ጉድ አለን!

ወያላው ከእኛ መለስ ብሎ፣ ‹‹ገሚሱ ከትምህርት ቤት ከወጣ በኋላ አንብቦ ስለማያውቅ ንባብ ከአሁኑ ቋቅ እያለው ነው፡፡ በመንግሥት ዋይፋይ የብሔር ትግሉን ሲያፋፍም የነበረው የኢንተርኔት አርበኛ፣ ለስልኩ ዳታ ቀለብ ማቅረብ ተስኖት መፈጠሩን ጠልቷል፡፡ ያደላቸው ደግሞ ሕይወትን እንደ አዲስ እያጣጣሙ ክፉ ጊዜን ለመልካም ማዋል እንደሚቻል ከቤተሰቦቻቸው፣ ከመጻሕፍቶቻቸውና ከቤት ውስጥ ሥራቸው ጋር በመደላደል እየተጠቀሙበት ነው…›› ብሎ ቀና ብሎ ሲያየን ያ ችኩል ጎረምሳ፣ ‹‹ይኼንን ነው ቀልድ ያልከን?›› ብሎ ሲበሳጭ የአንዳንድ ሰው ጭንቅላት ከምን ይሆን የተሠራው ያሰኝ ነበረ!

ብልሁ ወያላ ኮሌጅ ሳይገባ የማኅበረሰቡን ገመና እንዲህ ፍንትው አድርጎ ሲያሳየን፣ ከቀልዱ ይልቅ ቁምነገሩ የበለጠባቸው በአድናቆት እያዩት ነበር፡፡ ታክሲያችን ጊዮርጊስን አልፎ ወደ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ሲንደረደር ወያላው ጉሮሮውን ጠራርጎ፣ ‹‹ወገኖቼ ቀልዱን ደግሞ እስቲ እንዲህ ልተርክላችሁ…›› ሲለን ትኩረታችንን ወደ እሱ መለስን፡፡ ‹‹እናማ ምን ሆነ መሰላችሁ? አንዱ ቤትህ ተቀምጠህ ሥራ የተባለ የመሸታ ወዳጅ፣ አንዱን ቀን የሠፈር ግሮሰሪ ከቢጤዎቹ ጋር በጓሮ አስከፍተው እንደ ደርግ ዘመን ዝጉብኝ ወይም ሴክሬቶ ገብተው፣ ቢራቸውን ሲለበልቡ ቆይተው ጠርሙስ ጂን ያስከፍታሉ፤›› ሲል ሁላችንም በአንድ ድምፅ በድንጋጤ ‹ይኼማ አይደረግም› ስንለው፣ ‹‹ወገኖቼ ተደርጎ እኮ ነው የምነግራችሁ!›› ሲለን ቀልድ መሆኑን አስረስቶን ትረካውን ቀጠለ፡፡ እንዲያ ነው እንጂ!

‹‹አጅሬና ጓደኞቹ ጂናቸውን ቺርስ እየተባባሉ ሁለተኛ ጠርሙስ እንዳስከፈቱ ስለኮሮና ቫይረስ አመጣጥ፣ ማን ላቦራቶሪ ውስጥ እንደተፈጠረ፣ ለምን ከቻይና ጀምሮ አሜሪካና አውሮፓን እንዳጠቃ፣ አፍሪካን ጨረፍ እንጂ እንደማይጎዳት ሲፈላሰፉ የአጅሬው ድንገት ስልክ ጮኸ…›› ሲለን ሁላችንም በድንጋጤ ውስጥ ሆነን የወያላውን ዓይኖች ማየት ጀመርን፡፡ በዚህ መሀል ያ ችኩል ጎረምሳ፣ ‹‹ጤና ሚኒስቴር ኳረንቲን ሊያስገባቸው ይሆናል…›› እያለ ሲቀባጥር ታክሲያችን ራሱ ኳረንቲን ይመስል ነበረ፡፡ ‹‹አርኩ (ጣሊያን) ይሄድና ሶልዲውም ያልቅና፣ ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና›› የተባለው በፋሽስት ወረራ ጊዜ ነው የተባለው ተወዶ አይደለም ለካ!

ወያላችን ጎረምሳውን በትዝብት ይሁን በንቀት ስሜት እያየው፣ ‹‹ፍሬንድ አትቸኩል ብዬሃለሁ! እንዳንተ ዓይነቶቹ ናቸው ፍሬን እንደ ተበጠሰበት መኪና ካገኙት ጋር እየተላተሙ ችግር የሚፍጥሩት…›› ሲለው ጎረምሳው በኃፍረት የሚገባበት ጠፋው፡፡ ወያላው ካቆመበት ለመጀመር ሐሳቡን ሲሰበስብ አንድ ትልቅ ሰው፣ ‹‹የዚያ ሰካራም ስልክ ሲጮህ ነበር ወግህ የተቋረጠው…›› ብለው ሲያስታውሱት፣ ‹‹አባቴ ክብረት ይስጥልኝ ያኑርልኝ፡፡ አጅሬ የሚጮኸውን ስልኩን ሲያየው ደዋዩ አለቃው ነው፡፡ ሞቅታ ውስጥ ሆኖ፣ ‹ሔሎ አለቃዬ ምን ልታዘዝ?› ሲለው አለቅየው የዝጉብኝ ግሮሰሪ ታዳሚዎች ድምፅ ግራ አጋብቶት፣ ‹አንተ የት ነው ያለኸው? ምንድነው የምሰማው ድምፅ?› ብሎ ሲጮህበት፣ ‹ተረጋጋ አለቃዬ! የሠፈራችንን ሰዎች ራቅ ራቅ አድርጌ ሰብስቤ ስለኮረና ቫይረስ ታሪካዊ አመጣጥና ከበስተጀርባው ያለውን ሴራ እያስተማርኩ, ከቤት ሆኖ መሥራትን ተግባራዊ እያደረግኩ ነው› አለው…›› ሲለን ዓይናችንን ፈጠጠ፡፡ ድንጋጤ ነዋ!

‹‹አለቃው ድሮም ይህንን መሸተኛ ድሮም በሚገባ ያውቀው ኖሮ፣ ‹ሰማህ ታዲያ ለምንድነው ምላስህ የሚኮላተፈው?› ብሎ ወጥሮ ሲይዘው አጅሬው ሞቅታው እንደ ተነቃበት ገብቶት፣ ‹ወይ አለቃዬ ለካ ገና አልገባህም?› ማለት፡፡ አለቃው በጣም ተናዶ፣ ‹አንተ ሰካራም ምኑ ነው የማይገባኝ? ይልቁንስ ለምን ምላስህ እንደሚኮላተፍ ንገረኝ› ብሎ ሲያፋጥጠው፣ ‹አለቃዬ የኮሮና ጭንቀት እንኳን ምላስን መላ ሰውነትን አይደል እንዴ የሚያኮላትፈው?› ብሎ ሲመልስለት፣ የአለቅየው የንዴት ሳቅ ዋሽንግተንና ቤጂንግ ድረስ መሰማቱን የዘገበው ሲኤንኤን ነው…›› ሲለን፣ ጎረምሳው ሳቁን መቆጣጠር አቅቶት ሆዱን ይዞ ሲንፈራፈር ሌሎቻችን እንባ በእንባ ሆንን፡፡ ‹ከልብ ከሳቁ እንባ አይገድም› ማለት አሁን ነበር የሚሻለው!

ታክሲያችን አውቶቡስ ተራ ለመድረስ ጥቂት መንገድ ቀርቶታል፡፡ የዕለቱ ተረኛ አዝናኛችን ወያላው የፈረንሣይ ሁለት ሐኪሞች የኮሮና መድኃኒት በአፍሪካውያን ላይ እንዲሞከር መናገራቸውን አስታውሶን፣ ‹‹በእግር ኳስ ዓለም በጣም የማደንቃቸው ዲዲየር ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶ በግንባር ቀደምነት የሐኪሞቹን ፍላጎት ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ይደነቃል…›› ብሎን ከነፍሰ ገዳዮች አይተናነሱም ሲል በዘረኝነት የወነጀላቸውን ሐኪሞች አወገዘ፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ልሂቃኖቻችን እንዲህ ይተነትኑታል ለማለት ይቻላል!

ትልቁ ሰው ወያላውን በመገረም እያዩት፣ ‹‹ሳይህ በጣም ልጅ ነህ፣ ንግግርህ ደግሞ የፕሮፌሰር ነው፣ በትምህርትህም ከአንደኛ ደረጃ የዘለልክ አትመስልም፡፡ ይህንን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘኸው ልጄ?›› ብለው ሲጠይቁት፣ ‹‹አባቴ እግዚአብሔር ያክብርዎት! እኔ አዋቂዎች ሲናገሩ ማዳመጥ እወዳለሁ፣ በትርፍ ጊዜዬ ደግሞ ያገኘሁትን ሁሉ አነባለሁ፣ አርቀው ከሚያስቡ ሰዎች ጋር እወያያለሁ፣ ይኸው ነው ሌላ ሚስጥር የለም…›› ብሎ ሲመልስላቸው ሰማነው፡፡ ሸፌሩ መጨረሻው አድርሶን ሲያቆም፣ ‹‹አባታችን እሱ አብሮኝ ባይሠራ ኖሮ እኔም ሰው አልሆንም ነበር…›› ሲላቸው፣ ‹‹እንዲያ ከሆነማ ነገን የምትዘልቁ እናንተ ናችሁና በርቱ!›› ብለው ተሰናበቱን፡፡ ለጊዜው በአካል ብንራራቅም በመንፈስ አንድ ሆነን ተሰነባበትን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት