Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የበረሃ አንበጣን የመከላከል ሥራ የኮሮና ወረርሽኝ እየተስተጓጎለ ነው ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ቆይታውን ማድረግ የጀመረው ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ይህ ተባይ፣ እስከ መጪው ነሐሴ ወር እንደሚቆይ የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን፣ ማክሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የአንበጣውን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚረዱ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በሰዎችና በሎጂስቲክስ ትራንስፖርት ላይ የተጣሉ ገደቦች ባስከተሉት ተፅዕኖ ምክንያት የመከላከል ሥራውን ፈታኝ አድርገውታል፡፡

ይሁንና የበረሃ አንበጣውን በአውሮፕላን ርጭት፣ የአሰሳ ሥራውም በሔሊኮፕተር እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በስድስት አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ይገኛል ያሉት አቶ ኡመር፣ የቅኝት ሥራም ሔሊኮፕተሮች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሰፊው አንበጣ የሚገኝበት አካባቢ በመሆኑ ይህ ሥራም በስፋት በእነዚህ አካባቢዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

ይህም ሆኖ የቅኝት ሥራዎች እየቀነሱ፣ የኬሚካል አቅርቦት ላይም ጋሬጣ መፈጠሩ የበረሃ አንበጣውን የማጥፋት ዘመቻ ላይ ችግር እንደፈጠረ ያብራሩት የግብርና ሚኒስትሩ፣ ከደቡብ አፍሪካ ሔሊኮፕትሮችን ለማምጣት ይደረግ የነበረውን ጥረትም አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡ እንዲመጡ የሚጠበቁት ሔሊኮፕተሮች በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት በሦስት አገሮች ያርፋሉ፡፡ ይሁንና በኮሮና ሥጋት ምክንያት በየአገሮቹ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ለመቆየት የሚገደዱ በመሆናቸውና በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ለተጨማሪ 14 ቀናት መቆየት ስለሚጠበቅባቸው፣ ይህ አማራጭ አላስኬድ በማለቱ በአገር ውስጥ ባሉ ሔሊኮፕተሮችና አውሮፕላኖች መጠቀም አስገድዷል፡፡

እስካሁን በተደረገ የመጀመርያ ዙር የዳሰሳ ጥናት፣ አንበጣው በ3.6 ሚሊዮን ሔክታር ላይ የነበረ ሰብል ማውደሙ ተረጋግጧል፡፡ 200 ሺሕ ሔክታር ላይ የሚገኝ ሰብል፣ ተክሎችና ዛፎችን በመውረር ይዞታውን እያስፋፋ የቆየው የበረሃ አንበጣ፣ የበለጠ ተስፋፍቶ እንዲቆይ የሚያመቸው ዕድል እያገኘ ነው፡፡ የሰው ኃይል በመጠቀም ይደረግ የነበረው ርብርብም በበሽታው ሥጋት ምክንያት በእጅጉ እንዲቀንስ አስገድዷል፡፡

የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተንሰራፋው የበረሃ አንበጣ፣ ኬንያንና ሶማሊያን አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋባቸው የሚገኙ አገሮች አስብሏቸዋል፡፡ በተለይም ሶማሊያ በአንበጣው ሳቢያ የሚደርስባትን የምግብ ሰብል ውድመት በመሥጋት የአደጋ ጊዜ አዋጅ ማውጣቷ ይታወሳል፡፡ በሦስቱ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች በአንበጣው ወረርሽኝ ሳቢያ ለምግብ ዕጦት እንደሚዳረጉ ሲያስጠነቅቅ የቆየው የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት፣ በኮሮና ምክንያት በተፈጠረው የእንቅስቃሴ እግዳ ሳቢያ ተጨማሪ አራት ሚሊዮን ቤተሰቦች ለችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡

ከየመን የገባው የበረሃ አንበጣ የወቅቱ የአየር ጠባይ በፈጠረለት ምቹ አጋጣሚ እየተባዛና ከቦታ ቦታ እያዳረሰ ግዛቱን ሲያስፋፋ ቆይቷል፡፡ የአንበጣውን ወረራ ለመከላከል በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ የእርሻና የምግብ ተቋሙ አንበጣውን ለመከላከል ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አስታውቆ ነበር፡፡ እስካሁንም ከ140 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ድጋፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የኮሮና መከሰት እነዚህ አገሮች ሲያከናውኑ የነበረውን የመከላከል ሥራ አደጋ ውስጥ እንደከተተው ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ ለሚያደርጓቸው የአንበጣ መከላከያ ሥራዎች፣ የፀረ ተባይ ኬሚካል ግዥና ሥርጭት ላይ ሳንካ መፍጥሩን ተመድ አስታውቋል፡፡

በእስያና በአውሮፓ አገሮች በሮቻቸውን በመዝጋታቸው የካርጎ ጭነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አስገደድዷል፡፡ ከዚህ ሲከፋም አምራች ኩባንያዎች ምርት እያቆሙ በመሆናቸው የአንበጣው አደጋ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ እነዚህን አገሮች ሥጋት ላይ እንደጣላቸው ተገልጿል፡፡ ሶማሊያ ለግዥ ያዘዘችው የፀረ ተባይ በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ እንደሚደርሳት ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጭነቱ እንዲዘገይ ኮሮና አስገድዷል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ በመግዛት ያከማቸችው በቂ የኬሚካል ክምችት ቢኖራትም ርጭት ማካሄድና ቅኝት ማከናወን የሚያስችሉ አውሮፕላኖችና ሔሊኮፕተሮች እጥረት ጋሬጣ ሆኖባታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ በማወጇና ሕዝቧም በቤቱ እንዲከተት በማስጠንቀቋ፣ ኢትዮጵያ ያዘዘቻቸውን ሔሊኮፕተሮች ማግኘት አልቻለችም፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በተፈጠረው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዳይቋረጥ አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩን የማገዝ ሥራ እንደሚካሄድ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። አቶ ኡመር እንዳሉት ከሆነ፣ አርሶ አደሩ ግብዓት እስካገኘ ደረስ ምርት የማምረት ተግባሩን እንደማያቋርጥ ይጠበቃል፡፡

ከውጭ በግዥ የሚገባው የስንዴ አቅርቦት ግን ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም። በወር ከ640 ሺሕ ኩንታል በላይ ስንዴ ከውጭ እንዲገባ ሲደረግ ቢቆይም፣ በኮሮና ችግር ምክንያት መዘግየት መፈጠሩ እንደማይቀር በመታመኑ ከብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በዱቤ 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በመጠባበቂያነት መያዙን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች