Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንዳይባባስ የሚያግዙ ለውጦች እያደረጉ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተና የመስፋፋት ሥጋትን ካሳደረ ወዲህ የፋይናንስ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀይረው ንክኪን በሚቀንስ መንገድ ለማራመድ ሲንቀሳቀሱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ወረርሽኙ ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ አኳያ ደንበኞቻቸው ተጋላጭ የማይሆኑባቸውን አሠራሮች በመተግበር፣ በተወሰኑ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ እያደረጉ ነው፡፡ ከክፍያ ነፃ የተደረጉ አገልግሎቶችም ይፋ እየተደረጉ ነው፡፡

ለአብነት ዘመን ባንክ፣ ለአበባ አምራቾች ከሰጠው ብድር ላይ መከፈል የነበረበትን የሦስት ወራት ወለድ እንደረሰዘ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሌሎቹም ባንኮች የብድርና የወለድ ክፍያ ላይ የጊዜ ማራዘሚያ ሲያደርጉ እየታዩ ነው፡፡ የግል ባንኮች በተለይ የወቅቱን ሁኔታ ከግምት በማስገባት አዳዲስ ውሳኔዎች እያስላለፉ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን ለውጦችን ይዘው ብቅ ካሉት ውስጥ ሕብረት፣ ዓባይና ወጋገን ባንኮች ይጠቀሳሉ፡፡

የኮሮና ቫይረስ የደቀነውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ለመቀነስና ችግሩ በሕዝቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና በመመልከት ማሻሻያ ያደረገው ዓባይ ባንክ፣  የቦርድ አመራሩ በወሰነው መሠረት በአምስት ዋና ዋና መስኮች ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ደንበኞች እንደየሁኔታቸው እየታየላቸው እንዲፈቀድላቸው፣ የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ ሲቀርብ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን፣ የቅድሚያ ብድር ክፍያ ቅጣት እንዲነሳና ኤቲኤም ለሚጠቀሙ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ በነፃ እንዲቀርብ መውሰኑን አስታውቋል፡፡ ደንበኞች በአንድ ጊዜ እስከ 10,000 ብር ድረስ ከኤቲኤም ወጪ ማድረግ እንዲችሉ የሚፈቅድ አሠራርም ባንኩ መተግበር ጀምሯል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሰው ዓባይ ባንክ፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማለትም ሳሙና፣ አልኮል፣ የእጅ ሳኒታይዘር፣ ጓንትና የመሳሰሉት ቁሳቁሶችን  ለመላው ሠራተኞቹ እንዳሠራጨ ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ማኅበራዊ ጥግግትን በመቀነስ አካላዊ ንክኪን ማራቅ አንዱ የመከላከያ መንገድ በመሆኑ፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነፍሰ ጡርና የጤና እክል ያለባቸው ሠራተኞች ዕረፍት እንዲወጡ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ዓባይ ባንክ ከሌሎች ባንኮች በተለየ በሁሉም ቅርንጫፎች እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ ይቆይ የነበረውን መበደኛ አገልግሎት ለጊዜው በማቋረጥ አገልግሎቱ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲያጥር በማድረግ ኮሮና ተኮር ለውጦችን እየተገበረ ይገኛል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአገልግሎት ለውጥ ለማድረግ የሚያስገደዱ ውሳኔዎችን ያሳለፈው ወጋገን ባንክም፣ የቫይረሱን ሥርጭትን ለመግታት በብሔራዊ ደረጃ ለተቋቋመው ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ የባንኩ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ክንዴ አበበ እንደተናገሩት፣ ወጋገን ባንክ የኮሮና ቫይረስን የመከላከሉ ተግባር ውጤታማ እስኪሆን ድረስ ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ጎን ሆኖ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ሁሉም በላይ አንድ ሆኖ በትብብር ከሠራ በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር እንደሚቻል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል የባንኩ ዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ በየቅርንጫፎቹ ለሠራተኞቹና ለደንበኞቹ ስለበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን የእጅ መታጠቢያ ቁሳቁሶችንና የፅዳት ዕቃዎችን እያቀረበ መሆኑን የገለጹት አቶ ክንዴ፣ በሥራ ቦታ ያለውን ጥግግትና አካላዊ ቅርርብ  ለመቀነስ ለሠራተኞቹ ፈቃድ በመስጠት፣ በተለይም ለነፍሰ ጡር ሠራተኞች ከዓመት ፈቃዳቸው የማይታሰብ ዕረፍት በመስጠት የሠራተኞቹን ደኅንነት ለመጠበቅ ባንኩ ተግቶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወጋገን ባንክ ደንበኞች ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች ሳይመጡ በሥራ ቦታቸው ወይም በቤታቸው ሆነው የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎቶችን በመጠቀም ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን አሠራርም መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት በአጋር ካርዳቸው በኤቲኤም ማሽን ብቻ በመጠቀም ወደሚፈልጉት ሰው ሒሳብ ገንዘብ መላክና በቀን እስከ 10,000 ብር ማውጣት የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ‹‹ስልክዎ ባንክዎ›› በተሰኘው የሞባይል ባንክ አገልግሎት በቀን እስከ 50,000 ብር ማስተላለፍ የሚቻልበት አሠራር መተግበር ጀምሯል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም በቀን እስከ 100,000 ብር፣ ድርጅቶች ግን የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ በኮርፖሬት ኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት አማካይነት ማስተላለፍ እንደሚችሉ ባንኩ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች