Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካው ግብርና መሥሪያ ቤት የስንዴ ምርት አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚደርስ ተነበየ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

8.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የበቆሎ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቋል

በአሜሪካ የግብርና መሥሪያ ቤት ዕውቅና የዓለም አገሮችን የግብርና ምርቶችና ተጓዳኝ ዘርፎች የሚያስቃኘው ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ የስንዴ ምርት አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚደርስ የሚያሳይ ትንበያ አውጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደባል የሆነው የአሜሪካው የግብርና መሥሪያ ቤት፣ እዚሁ በሚገኙ ባለሙያዎቹ አማካይነት የሚያጠናቅረው የግብርና ዘርፍ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በኢትዮጵያ የሚጠበቀው ከፍተኛ የስንዴና የሌሎች የሰብል ወይም የብርዕና አገዳ ምርቶች ዕድገት የመንግሥት የግብዓት አቅርቦት መሻሻል፣ መልካም የአየር ጠባይ ሁኔታ መታየቱ፣ በአብዛኛው የተስተካከለ የዝናብ ሥርጭት መመዝገቡ በእህል አምራች አካባቢዎች ተጨማሪ ምርት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

በዚህ ሳቢያ በዚህ ዓመት የሚጠበቀው የስንዴ ምርት መጠን አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚገመት ይፋ ያደረገው የግብርና መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት፣ 1.85 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በስንዴ እንደሚሸፈን፣ በሔክታር የሚገኘው ምርትም ወደ 2.76 ቶን እንደሚያድግ አስፍሯል፡፡ ከተስተካከለው የዝናብ ሥርጭትና የመንግሥት የግብርና ግብዓት አቅርቦት በተጓዳኝ፣ ከዚህ ቀደም ለስኳር ልማት ተከልለው የቆዩ እዳሪ መሬቶችን ለስንዴ ልማት መዋላቸውም ለምርቱ መጨመር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016/17 እስከ 2019/20 ባለው ጊዜ ውስጥ የስንዴ ምርት ጭማሪ እያደገ መምጣቱንና የሚታረሰው መሬትም በተነፃፃሪ ደረጃ ሳይስፋፋ በነበረው መጠን ልክ እንደቆየ ያወሳው የግብርና መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት፣ ስንዴ ከአገሪቱ የአገዳና የብርዕ ምርቶች የ18 በመቶ ድርሻ በመያዝ ሰፊ የምግብ ዋስትና ሚና እንዳለው አመላክቷል፡፡ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ማለትም በአርሲና ባሌ እንዲሁም በመካከለኛው የአገሪቱ ደጋማ አካባቢ በተለይም በሸዋና በጎጃም የስንዴ ምርት በሰፊው የሚታወቅና፣ እነዚህን አካባቢዎችንም የስንዴ ቀበቶ ያሰኘ ሰፊ ድርሻ አለው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2023 ኢትዮጵያን ከስንዴ ግዥ ነፃ ለማውጣት መንግሥት ዕቅድ ማውጣቱን ያስታወሰው የአሜሪካ የግብርና መሥሪያ ቤት፣ የግብርና ማሽነሪዎች ኪራይ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማቋቋም ከ190 ሚሊዮን ብር ወይም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ በጀት መመደቡንም አስታውሷል፡፡

ምንም እንኳ የአገር ውስጥ የስንዴ ምርት መጠን ወደ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያድግ ቢጠበቅም፣ የፍጆታ መጠንም ወደ 6.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያሻቅብ ትንበያው አመላክቷል፡፡ ካለፈው ዓመት አኳያ የፍጆታ ጭማሪው ከ35 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ያልበለጠ እንደሚሆን ሲጠበቅ የምርት ጭማሪው ግን 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደሚሆን አጣቅሷል፡፡ ይህ ግን ትንበያው አዳዲስ የገቡትን የስኳር ልማት የሸንኮራ ማሳያዎችና የቆላማ አካባቢ እርሻዎችን አስተዋጽኦ በሚገባ ማሳየት እንዳልቻለ ጠቋሚ ነው፡፡ 

የስንዴ ግብይትን በተመለከተ ሪፖርቱ ያሳፈረው ሀተታ እንደሚያሳየው፣ ዱቄት ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ድርጅት በኩል ከአገር ውስጥና ከውጭ በድጎማ ተገዝቶ የሚቀርብላቸው ስንዴ፣ ድጎማ ከማይደረግበት ምርት አኳያ 35 በመቶ የዋጋ ልዩነት እንደሚታይበት፣ ይህም ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲታይ ቆይቷል፡፡ ዳቦ ቤቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም በአራት በመቶ ብቻ መወሰኑ የመንግሥት የድጎማ ውጤት እንደሆነ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥም በአማካይ በየዓመቱ 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ እንደተገዛ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ ይህ መጠን 30 በመቶውን ፍጆታ እንደሚወክል ሲገለጽ፣ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የስንዴ ምርትም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ሪፖርቱ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

ከውጭ ከሚገባው ስንዴ ዩክሬን ከ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በማቅረብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ግዥ ከ76 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የስንዴ ምርት አቅራቢ አሜሪካ ስትሆን፣ ከ287 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለኢትዮጵያ በማቅረብ ከ108 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች፡፡ ሩሲያ ከ278 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በማቅረብ ሦስተኛዋ ስትሆን፣ 79 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏታል፡፡

ሩማንያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቱርክ፣ ግብፅ (36 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ታቀርባለች)፣ ሰርቢያና ቻይና በጠቅላላው 315 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከኢትዮጵያ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚገባውና ዕርዳታ ታክሎበት ከ315 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ያላነሰ ስንዴ ወደ አገር ውስጥ እየገባ በመሆኑ በጠቅላላው ከ1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የበለጠ ስንዴ ከውጭ እንደሚገባ መረጃው አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የበቆሎ ምርት ወደ 8.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያግድ ትንበያውን ያሰፈረው ይህ ሪፖርት፣ ካለፈው ዓመት የ8.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ትንበያ አኳያ ጭማሪውን መጠነኛ በማድረግ በ100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ገድቦ፣ እንደ ስንዴው ሁሉ ተመሳሳይ ትንበያ አቅርቧል፡፡ 2.34 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በበቆሎ ምርት እንደሚሸፈን ይጠበቃል፡፡

የምርት ጭማሪው የበረሃ አንበጣ አሳሳቢ ፈተና በጋረጠበት ወቅት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ለዚህ ምርት ዘመን ይህን ያህል አደጋ የሚያስከትል ጉዳት እንደማያመጣ ትንበያው ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በሌላ ጎኑ ግን አንበጣው በሰብል ምርት ላይ የሚያስከትለው ውድመት እንደሚያሳስብ በማመላከት፣ በዚህ ዓመት የተደረጉ የመከላከል ዕርምጃዎች ያመጡት ውጤት ግን በመጪው ምርት ዘመን ሊታወቅ እንደሚችል በመጠቆም ያልፈዋል፡፡   

በበቆሎ ምርት ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተሻለ አቅም ላይ እንደምትገኝ የሚጠቅሰው የአሜሪካ ግብርና መሥሪያ ቤት ሪፖርት፣ በሔክታር 3.5 ሜትሪክ ቶን ምርት መሰብሰብ የተቻለበት ደረጃ ላይ መድረሷን አመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች