[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ወደ ቢሮ እየሄዱ ነው]
- ምን ተሻለ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- በሽታው ነዋ፡፡
- እንዴት?
- እየጨመረ እኮ ነው፡፡
- መፀለይ ነው የሚያዋጣው፡፡
- እርስዎ ይፀልያሉ እንዴ?
- ለምን አልፀልይም?
- ያው በሥልጣንዎት ነው የሚያምኑት ብዬ ነዋ፡፡
- የሥልጣናችን ገደብማ ታየ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ይኸው የዓለም ታዋቂ ግለሰቦች ሳይቀር በበሽታው እየተጠቁ እኮ ናቸው፡፡
- እኔም ዜናውን ሰምቻለሁ፡፡
- የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሱ ከፍተኛ ሕክምና እየተደረገለት እኮ ነው፡፡
- በአንድ በኩል ግን በሽታው ደስ ይላል፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ሁላችንም እኩል መሆናችንን አሳየና፡፡
- እ. . .
- ክቡር ሚኒስትር በሽታው ጥቁር አይል ነጭ፣ ደሃ አይል ሀብታም ሁሉንም ነዋ የሚይዘው፡፡
- ተነፈስን እኮ አሁን፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ሥልጣናችንም ገደብ እንዳለው ተረዳና፡፡
- ምን ያደርጋል ታዲያ?
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ለሥልጣን ስትሉ አልነበር እንዴ ሕዝቡን ስትፈጁት የነበረው?
- መስሎን ነዋ፡፡
- አሁን ግን አንድ ነገር እየፈራሁ ነው፡፡
- ምን?
- ከኮሮናው በላይ ያስፈራኝ እሱ ነው፡፡
- ምንድነው?
- ኢኮኖሚው ነዋ፡፡
- እስኪ እሱን ተወው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በርካታ ሰዎች እኮ እየተቸገሩ ነው፡፡
- ገና ካሁኑ?
- አብዛኛው ሰው የዕለት ጉርስ ፈላጊ መሆኑን አይርሱት፡፡
- መቼ ጠፋኝ?
- ጣሊያን ውስጥ የማኅበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል አሉ፡፡
- ለምን?
- ሕዝቡ የሚበላው አጥቶ ነዋ፡፡
- ወይ ጣጣ?
- ክቡር ሚኒስትር እዚህም አገር እንዲህ ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
- ምን ይደረጋል ብለህ ነው?
- ከአሁኑ መዘጋጀት ነዋ፡፡
- የምን ዝግጅት ነው?
- ባለፀጋዎች መዘጋጀት አለባቸው፡፡
- በምንድነው የሚዘጋጁት?
- ሀብታቸውን ለማካፈል ነዋ፡፡
- ይሆናል ብለህ ነው?
- ካልሆነማ የሚጠብቃቸውን ያዩታል፡፡
- ምንድነው የሚጠብቃቸው?
- ሙሉውን ያጡታል!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይቅርታ አድርግልኝ፡፡
- ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ታውጇል አይደል እንዴ?
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ እንዴ?
- ኧረ የፀሎትና የምልጃ አዋጅ ነው እንጂ፡፡
- ታዲያ የምን ይቅርታ ነው?
- በቃ ፈርቻለሁ፡፡
- ምንድነው የሚያስፈራዎት?
- ኮሮና ነዋ፡፡
- ለእሱ እኮ መጠንቀቅ ነው የሚያስፈልገው፡፡
- እኔ ግን ውስጤ ፍርኃት ፍርኃት እያለኝ ነው፡፡
- ለምን?
- ብዙ ወንጀል የሠራሁ ሰው ነኝ እኮ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ቦታ ለመድረስ ያላደረግኩት ነገር የለም፡፡
- ምን አደረጉ?
- ያደረግኩትን ለማውራት ብጀምር ወራት አይበቁኝም፡፡
- ይኼን ያህል?
- አሁን ያስጠራሁህ እኮ ለዚያ ነው፡፡
- ኑዛዜ ሊያጽፉኝ?
- ኧረ ይቅርታ ለመጠየቅ፡፡
- ለምኑ?
- አንተን ምን ያልሠራሁህ ነገር አለ፡፡
- ኧረ ምንም አላደረጉኝም፡፡
- በየቀኑ እኮ ነው የማሴርብህ፡፡
- እኔ ላይ?
- እህሳ፡፡
- ለምን?
- ብዙ ሚስጥር ስለምታውቅ ነዋ፡፡
- ቢሆንም እኔም እኮ እርስዎን ለማንም አሳልፌ አልሰጥዎትም፡፡
- አሁን ግን ኮሮና አሳልፎ ሊሰጠኝ ነው፡፡
- ለምን ፈሩ ክቡር ሚኒስትር?
- መተኛት አልቻልኩም፡፡
- ለምን?
- በህልሜ ሁሉ ተይዤ ሲያበቃልኝ ነው የማየው፡፡
- ሞት ይፈራሉ እንዴ?
- ቆጭቶኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው የቆጨዎት?
- ለዚችው ነው እንዲያ በሴራ ሕይወቴን የጨረስኩት ብዬ ነዋ፡፡
- እ. . .
- ቀን ተሌት ሳሴር ነበር እኮ የማድረው፡፡
- ይኼን ያህል?
- እና ይኼን ሁሉ ሀብት ያከማቸሁትስ በዕውቀቴ ይመስልሃል?
- እሱማ በሥልጣንዎት ነው፡፡
- እዚህ ለመድረስ የብዙ ሰዎችን ሕይወት አበላሽቻለሁ፡፡
- አሁን መንቃትዎትም ጥሩ ነው፡፡
- ስለዚህ ይቅርታ አድርግልኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከእኔ በላይ ይቅርታ መጠየቅ ያለብዎት አካል አለ፡፡
- ማንን ይቅርታ ልጠይቅ?
- ሕዝቡን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሰላም አለ ብለህ ነው?
- ቁጥሩ እኮ እያሻቀበ ነው፡፡
- ምን ይደረግ?
- ሁሉም ነገር ተዘጋግቷል፡፡
- ሌላ አማራጭ አጥተን እኮ ነው፡፡
- ገና ከጅምሩ እንዲህ ከሆነ ወደፊት እንዴት ሊኮን ነው?
- እኔም ራሱ ጨንቆኛል፡፡
- ሥራ ለለመደ ሰው ቤት ውስጥ መታሸግ ከባድ ነው፡፡
- ሥራ ለለመደ አልክ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ ስርቆት እንጂ የምን ሥራ ታውቃለህ?
- እኔ እኮ ስርቆትን እንደ ሥራ ነው የማየው፡፡
- እንዲያ ከሆነ እንኳን ልክ ነህ፡፡
- እርስዎም ግን ከእኔ ብዙም አይለዩም፡፡
- እንዴት ማለት?
- ያው እዚህ ቦታ የደረሱት ብዙ ግፍ ፈጽመው ነዋ፡፡
- ለማንኛውም እኔ ያስቀየምኳቸውን ሰዎች እየደወልኩ ይቅርታ እየጠየቅኩ ነው፡፡
- ፈርተዋል ማለት ነው?
- ስማ እንደኛ ዓይነቱን እኮ በሽታው ክፉኛ ነው የሚያጠቃው፡፡
- ለነገሩ እኔም ኑዛዜዬን እየጻፍኩ ነው፡፡
- ለማን ነው የምትናዘዘው?
- ለልጆቼ ነዋ፡፡
- ቀልደኛ ነህ እባክህ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- የአንተ ሀብት የማን እንደሆነ አታውቅም?
- የማን ነው?
- የሕዝቡ ነዋ፡፡
- መቼም ቀልደኛ ነዎት፡፡
- የምን ቀልድ ነው?
- አንድ ነገር ግን ልንገርዎት፡፡
- ምን?
- ለካ ሱስ ነው፡፡
- ምኑ?
- መስረቅ፡፡
- እ. . .
- ይኸው አሁን እየተሰቃየሁ ነው፡፡
- ማለት?
- ምን ልስረቅ?
- እ. . .
- ቤት ውስጥ ታሽጌ ማለቴ ነው፡፡
- እኔን እንኳን ያስቸገረኝ ሌላ ሱስ ነው፡፡
- ምን?
- እንዲህ ያለ እሱ መኖር እንደማልችል አላውቅም ነበር፡፡
- የምን ሱስ ነው ያለብዎት?
- የስብሰባ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ አክቲቪስት ስልክ ደወለላቸው]
- እስከ መቼ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ?
- አገራችን የምትዘጋው፡፡
- አልገባኝም?
- ምርጫውንም አስተላለፋችሁት፡፡
- ሕዝብ ይለቃ ታዲያ?
- እኛም እኮ ሥራችንን ተቀማን፡፡
- ማን ነው የቀማችሁ?
- መንግሥት ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ሁሉን ነገር ማዘጋት የሚያምረው በእኛ ነበራ፡፡
- እ. . .
- ይኸው አሁን መንግሥት ሁሉን ነገር ቆላልፎት ቤት ተቀመጥን፡፡
- ለነገሩ ሌላ ሥራ ተፈጥሮላችኋል እኮ፡፡
- የምን ሥራ?
- ሕዝቡን አካላዊ መራራቅ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ ማስጨበጡ አስቸግሮናል፡፡
- ምን እያሉኝ ነው?
- በሽታውን ከሚከላከሉ ተግባራት መካከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ዋነኛው ነዋ፡፡
- ስለዚህ?
- እናንተ ዕርዱን፡፡
- ምን በማድረግ?
- ሕዝቡን በማራራቅ!