Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ተራሮች የተረሱት የምሥራቅ አፍሪካ እስትንፋሶች

በታፈረ ሕሉፍ ዓለሜ (ኢንጂነር)

ከሳምንት በፊት “ህዳሴ አዲሱ የአንድነታችን ምልክት” የሚል ጽሑፍ እዚሁ ሪፖርተር ላይ በሁለት ክፍል ማሳተሜ ይታወሳል፡፡ የጥቁር ዓባይ ፍሰትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት የህዳሴ ኃይል የማመንጨት አቅም ማሳደግ፣ የግድቡ ዕድሜ መጨመርና አጠቃላይ ተፋሰሱን አሁን ካለበት ሁኔታ መታደግ እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ መፍትሔ መኖሩም ይታወሳል፡፡ ይህንን መፍትሔ ይፈታዋል ተብሎ የታሰበው ችግር በአገር ደረጃ በእያንዳንዱ ዘርፍ ውስጥ ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ የድህነት ቀጥተኛ መንስዔ እንደሆነና መፍትሔውም በአገራዊ የልማት ፖሊሲ ደረጃ መታየት እንዳለበት በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት ይሞከራል፡፡

ኢትዮጵያ በአማካይ ኮረብታማና ተራራማ አገር መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ቦታዎች አገሪቱ በማዕከላዊነት ያረፈችበት ሲሆኑ ሁሉም የውኃ ምንጮች ከእነዚህ ቦታዎች እየተነሱ በአራቱም ማዕዘናት እያቋረጡ ወደ ጎረቤት አገሮች ይፈሳሉ፡፡ በአንጻሩ ግን አጠቃላይ የአገሪቱ ልማታዊ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ከዚህ አቅጣጫ አኳያ የተቀረጹ አይደሉም፡፡ እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ እውነታን ያላካተተ ፖሊሲ ዘላቂ ልማት ዕውን የማድረግ ዕድል አለው ወይ ነው ጥያቄው፡፡ መልሱ “የለውም” ነው፡፡ ምክንያቱም የመሬት የአየር ሁኔታ የሚገዛው በውቅያኖሶችና በተራሮች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ተራራ እንጂ ከውቅያኖስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የላትም፡፡ በመሆኑም ለዚች አገር ዋናዎቹ የምርታማነት ኃይሎች ተራሮችና ኮረብቶች መሆናቸው በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡

አሁን ላይ ቁጥራችን፣ ደካማነታችንና ችግራችን በዝቷል፡፡ ለተራሮች የተሰጠው ትኩረት ባለመኖሩ፣ የሰብል ምርታማነት ላይ በማዳበሪያና በምርጥ ዘር ላይ ብቻ ጥገኛ ሆናለች፡፡ የምርጥ ዘር ሳይንስ በሚገባ ሥር ባለመስደዱ በርካታ አገር በቀል አዝርዕት እየጠፉ ይገኛሉ፡፡ የሕዝቡ ብዛት ከምርቱ መጠን አኳያ ሲታይ በእጅጉ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰባችንን ይቀላቀላሉ፡፡ የስንዴ አገር ሆና እጅግ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ከውጭ ታስገባለች፡፡ ለተራሮች ከሚሰጠው ትኩረት አኳያ፣ መታረስ የማይገባው መሬት ሲታረስ መታረስ የሚገባው መሬት ደግሞ ላልሆነ አገልግሎት ሲውል ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም ዓለምን የሚቀልብ የሚታረስ መሬት ይዛ ከዘመን እስከ ዘመን ትራባለች ኢትዮጵያ!! የኢትዮጵያ ተራሮች መራቆት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮች መደህየትም ቀጥተኛ ምክንያት የመሆን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥ ድህነትን ከሥር መሠረቱ ለመንቀል ከተፈለገ የእነዚህን ተራሮች ልዩ ተፈጥሮ መጠቀም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ውጭ የተቀረጹት የአገራችን የልማት ፖሊሲዎች ግን እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ እውነታዎችን ያላካተቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትና ለዜጎች በጉዳዩ ላይ አቅጣጫ የሰጠ እንደሆነ በማሰብ ይህን ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጀሁ፡፡  

  1. የተራሮች ልማት፡ ከተባበሩት መንግሥታት የዕድገት አጀንዳ አኳያ

ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የዓለም አጠቃላይ ሁኔታዎች የሚገዙት ተራሮችና ውቅያኖሶች ናቸው፡፡ ተራሮች የባህልና የብዝኃ ሕይወት ማዕከል፣ የጥሬ ዕቃ መገኛዎች፣ የኢነርጂና የውኃ ምንጮች፣ የግብርና ምርታማነት መሠረቶች፣ የአየር ንብረት ዋና ሞተሮችና ወሳኝ የጎብኚዎች መዳረሻዎች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በዓለም ደረጃ ተራሮች ተጠንተው ካልተሰነዱ ሥርዓተ ምሕዳሮች ውስጥ ሲሆኑ ለሚሰጡት የማይተካ ግልጋሎትም ዕውቅናና እንክብካቤ ያልተቸራቸው የተረሱ መልክዓ ገፅታዎች ናቸው፡፡ ብዙ ተራራማ አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለው የመሬት መራቆትና አስፈሪ የድህነት ደረጃዎችንም ጨምሮ ብዙ ዓይነት ሥጋቶችና አደጋዎች የተጋረጠበት አካባቢ ነው፡፡ ተራሮች በብዙ ውስብስብና እርስ በርስ በተጠላለፉ ዓለም አቀፋዊ የለውጥ አምጪ ኃይሎች ተፅዕኖ ሥር ናቸው፡፡ ብዙ የተራራ ነዋሪዎች ገቢ ፍለጋ ወደ ዝቅተኛ ቦታዎችና ወደ ከተማ ማዕከላት ይሰደዳሉ፡፡ ወሳኙ የሰው ኃይል የተራራውን ሀብትና መሬት እየተወ  ይሰደዳል፡፡ ይህ ደግሞ የባህላዊ እሴቶች መጥፋትና ተራራው ላይ አደጋዎች እንዲበራከቱ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል የሚሉ ጥናቶች አሉ፡፡ 

ተራሮች ለአየር ንብረት ለውጥ በቀዳሚነት ተጋላጭ ከመሆናቸው ጋር ለአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው፡፡ አሁን ላይ የተራራማ አገሮች (ማኅበረሰብ) ፈተናዎች በእጅጉ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ በዓለም ውስጥ የከፍተኛ ድህነት መፈልፈያ መሆናቸውም የታወቀ ሆኗል፡፡ በዓለም ደረጃ የምድራችን 25 በመቶው በተራራ የተሸፈነ ቢሆንም 40 በመቶው የዓለም ተራሮች ያሉት በታዳጊ አገሮች ውስጥ ሲሆን ይኼው አካባቢ ከ300 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በረሀብ የሚገረፉበት የሰቆቃ አካባቢ ነው፡፡

የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ባለባት፣ የሕዝብ ብዛት እያሻቀበ በሚሄድባትና የአየር ሁኔታ ተፅዕኖዎች እየጨመረ በሚሄድባት ዓለም ውስጥ ተራሮች ለመጪው ዘመን ዘላቂ ተስፋ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡ አያሌ ጥናች ተደርገዋል፡፡ በዓለም ውስጥ ለግብርና ሥራዎች፣ ለዶሜስቲክ ግልጋሎቶችና ለኢንዱስትሪ ፍጆታዎች የሚውለው ከ60 እስከ 80 በመቶ ጨዋማ ያልሆነ ውሀ (fresh water) የሚገኘው ከተራሮች ነው፡፡ ከግማሽ በላይ የዓለም ብዝኃ ሕይወት በእነዚህ ተራሮች ሥር ይገኛል፡፡ አንድ ስድስተኛው የሰው ልጅ በቀጥታ በተራሮች በኩል የሕይወት ድጋፍ ያገኛል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ደግሞ ከተራሮች የተለያየ አገልግሎቶችን ያገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተራራማ ክልሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እያገኙ ይመስላሉ፡፡ ተራሮች ለዓለም አቀፋዊ ዘላቂ የልማት ዕድገት ቁልፍ መሠረቶች ሆነው ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ለላይኛውና ለታችኛው ተፋሰስ ነዋሪ ኅብረተሰቦች ተራሮች የማይተካ ሚና እንዳላቸው እየታወቀ በመምጣቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳነቱ በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ተራራማ አካባቢዎችን የማልማት፣ አሴቶችን የመጠበቅና የአካባቢው ምርታማነትን የማሻሻል አስፈላጊነት በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢና የዕድገት አጀንዳ 21 ጉባዔ (United Nations 1993) እንዲሁም የሪዮ+20 (United Nations 2012) ዶክመንቶች ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የሪዮ+20 ስብሰባ ከተራራማ አካባቢዎች የሚገኝ ትሩፋቶችን “essential for sustainable development” በሚል ለይቶ ማወቅ ችሏል፡፡ ለአገሮች የትብብር ትግበራ ጥሪም ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ በተራራማ አገሮች፣ ድርጅቶችና በማኅበረሰቦች የተደረገ ጥሪ ዓላማው የሚሌኒየም የልማት ግቦችን 2015 ላይ ጊዜ ሲያልፍባቸው ተራሮች በዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) እንዲጠቃለሉ የታሰበ ነበር፡፡    

ተራሮችና የከፍተኛ ዝቅተኛ ቦታዎች መስተጋብር ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችና ተሻጋሪ የትብብር መነሳሳቶች ርዕሰ ጉዳይ መሆን ከጀመሩ ዋል አደር ብሏል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ተራሮች አገር ተሻጋሪና ሁለተናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው ነው፡፡ ለዘላቂ ልማት የተራሮች ስትራቴጂካዊ ወሳኝነት ቢኖረውም አቀናጅቶ ማስተዳደርና ልማቱን እንዲስፋፋ ማድረግ የማይሞከር አድርጎ የመሣልና ከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚደረግ ልማት ምን ያህል አጠቃላይ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስገኝ ያለመገንዘብ በብዙዎች ዘንድ በመኖሩ ተፈጻሚነቱን ከባድ እንዳደረጉት ይገመታል፡፡ ይህም ብዙዎቹ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የውሳኔ መስጫ ማዕከላት ከተራሮች ርቀው ለዝቅተኛ ሥፍራዎች የቀረቡና በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኙ መሆናቸውም ሌላኛው እክል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህም በተለይ ከአገሮች ፖሊሲዎችና ከዕድገት ትብብሮች ውስጥ ተራሮችን ወደ ጎን ለመተው አስተዋፅኦ እንዳደረገ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥታት ትኩረት ማጣት፣ የኢንቨስትመንት እጥረት፣ የሳይንሳዊ አስተሳሰብ እጥረትና የከፍተኛ ቦታ ተፈጥሯዊ አስቸጋሪነት ጋር ተደማምረው ተራሮችና ኮረብቶች ለሕዝብ የድህነት ሥጋትና ለዘርፈ ብዙ ተጋላጭነት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በዓለም ደረጃ፣ ተራራማ አካባቢያዎችን ለመጠበቅና የአካባቢው ድህነት ለመቀነስ የተደረጉ ብዙዎቹ የተናጠል የልማት ተነሳሽነቶች በመንደር ደረጃ ውስን ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሆኖም የሰው ኃይልን፣ የአፈር ጥበቃ ሥራዎችን፣ የደን ጥበቃ ሥራዎችን፣ የዘላቂ ኃይል ልማቶችን፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ አቅምንና የተራራ አሴቶችን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ግን የተበታተኑ በመሆናቸው ያልተሳኩ መሆናቸው ያሳያል፡፡ ይህ በተለይ አስጨናቂ የሚያደርገው የአየር ንብረት ለውጥም ጨምሮ ዓለም አቀፋዊ ለውጦች በተራው ማኅበረሰብና በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ግፊት እየፈጠሩ ሲሆን ይህም በብዙዎቹ የዓለም ተራራማ ሥፍራዎች ላይ ወደ ዘላቂ ያልሆነ የመሬት አስተዳደራዊ ትግበራ እየመራው ይገኛል፡፡   

በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ከዓለም አቀፋዊ ለውጦች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በተናጠል ተነሳሽነቶች ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ በፖሊሲ ሽፋን ውስጥ በተለያዩ መዋቅራዊ እርከኖች በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራና በዘርፉ ልዩ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ተግባር ከመጀመር ጎን ለጎን የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መሥራትንም ጭምር እንደሚያስፈልግ የታመነበት ነው፡፡

  1. የኢትዮጵያ ተራሮች፡ የምሥራቅ አፍሪካ እስትንፋሶች

ተራሮቻችን ለዘላቂ አገራዊ ዕድገት ዋና ርዕሰ ጉዳይ ስለምን አልሆኑም ነው ጥያቄው፡፡ በአማካይ ኮረብታማና ተራራማ አገር ናት፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ኮረብቶችና ተራሮች አገሪቱ በማዕከላዊነት ያረፈችበት ሲሆን ከባህር ጠለል በላይ ከ1,290 እስከ 4,533 ሜትር ከፍታ አላቸው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ወንዞች ከእነዚህ ኮረብቶች ይፈልቁና ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያን እያቋረጡ ወደ ጎረቤት አገሮች ዝቅተኛ ቦታዎች ይፈሳሉ፡፡   

ከዓለም ከፍተኛ ቦታዎች ሁሉ የእኛ የሚለዩት አገር ተሻጋሪ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ተራሮቻችን ኢትዮጵያዊ ብቻ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስተው ኢትዮጵያ ውስጥ ያረፉ ሰንሰለታማ ተራሮቻችን አንድ ወቅት አስተማማኝ መከላከያዎቻችን ነበሩ፣ ጦር ጋሻዎቻችን ነበሩ፣ አገር ድንበርና ሕዝብ ጠባቂዎች ነበሩ፣ የማይደፈሩ የአንበሳ ምሽጎች ነበሩ፡፡ አሁን ዘመኑ ተለውጧል፡፡ እኛ ቁጥራችንና ደካማነታችን በዝቷል፡፡ ተራሮቹም ራቁታቸው ቀርተዋል፣ በጎርፍና በሰው ሠራሽ ችግሮች በየወቅቱ እየተራቆቱ ይገኛሉ፡፡ ለግንባታ ሥራዎች ሲባል ያለምንም ገደብ ይቆፈራሉ ይቆረጣሉ፣ ሽፋናቸው እየተገፈፈ መዓዛቸው እየተጠረገ ክብራቸው እየተናደ ወደ ጎረቤት አገሮች በየወቅቱ ይነጉዳል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እስከ 140 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አፈር በጉባ ወረዳ (ህዳሴ ግድብ ያለበት) በኩል አድርጎ ወደ ሱዳንና ግብፅ እንደሚጓዝ ይታወቃል፡፡ ይህ አፈር የህዳሴ ግድብን ዕድሜ የማሳጠር አደጋም ጭምር የያዘ ነው፡፡ በቀሪዎቹ ተፋሰሶች በኩልም እንዲሁ ቁጥር ሥፍር የሌለው አፈር ያለማቋረጥ ከኢትዮጵያ ተጠርጎ ወደ ጎረቤት አገሮች ይጓጓዛል፡፡ በእርግጥ የሚጓጓዘው የተራሮቹ አካል ብቻ አይደለም፣ የመጪው ትውልድና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ እንዲሁም የአያቶቻችን አካላትም ጭምር እንጂ፡፡ 

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በአገር ደረጃ የተዘነጋ አንድ ጉዳይ የምናገኘው፣ የተራሮች/ኮረብቶች ልማት!!! ኢትዮጵያ እንደ ሱዳን፣ እንደ ግብፅ፣ እንደ ጅቡቲ፣ እንደ ሶማሊያና እንደ ኬንያ ሜዳማ አይደለችም፡፡ ‹‹የአፍሪካ ጣራ›› (Roof of Africa) እስከመባል የደረሰች ተራራማና ኮረብታማ አገር ናት፡፡ ይህ ማለት የዝርዝር ጥናት አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሁሉም የሕይወት መልኮች መኖር የቻሉት ከተራሮቹ ቀጥተኛ ድጋፍ መሆኑን በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡

እነዚህን ከፍተኛ ቦታዎች ሳይለሙ እንዴት ዘላቂ ልማት በዚች አገር ላይ ማምጣት ይቻላል? አዲሱ የግብርና የልማት ትኩረት ደግሞ “የቆላ ግብርና” ነው፡፡ በእርግጥ መስኖ ጋር በተያያዘ የቆላ ግብርና ላይ ቢሠራ ዘላቂ መፍትሔ ባይሆንም መነቃቃትን ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የቆላው ምርታማነት በተራሮች ሁኔታ የሚወሰን በመሆኑ የከፍተኛ ቦታዎች እየተራቆቱ ባሉበት፣ የቆላው ልማት በዘላቂነት ስኬታማ የሚሆንበት ዕድል ግን ፈጽሞ የለም፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋዎች ተራሮቿ ናቸው፡፡ ኮረብቶቿ ናቸው፡፡ የቆላውም ሆነ የደጋው ምርታማነት በተራሮቹ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ የብዝኃ ሕይወት ዕጣ ፈንታም በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ የዕፀዋቱ ዕጣ ፈንታ በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ የተፋሰሱ ዕጣ ፈንታ በተራሮቿ ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን፣ የውኃ አካላት ዕጣ ፈንታ በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ የአየር ሁኔታም በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ የግብርና ምርታማነትም በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተራሮቿ ሁኔታ ላይ የሚወሰን መሆኑን በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላለች በቀጣናው ብቸኛ ተራራማ አገር፣ ከተጠቀምንባቸው እውነተኛው ገዢ ኃይሎች ተራሮቹ ናቸው፡፡ ድህነትን ከሥር መሠረቱ ለመንቀል የእነዚህን ተራሮች ልዩ ኃይል መጠቀም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ ተራሮች ውብ የተፈጥሮ ገፅታ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ተራሮች ግን እስካሁን መካን ናቸው!! ትኩረት የተነፈጉ እንደ ሀብት የማይታዩ ቆሞ ቀሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በጥሩ ይዞታ ላይ የነበሩ የስሜን ተራሮችና የባሌ ተራሮችም በየጊዜው ሲቃጠሉ ማየት ደግሞ በእጅጉ ያማል፡፡

ለተራሮች የተሰጠው ትኩረት ባለመኖሩ፣ አገሪቱ የሰብል ምርታማነት ላይ በማዳበሪያና በምርጥ ዘር ላይ ብቻ ጥገኛ ሆናለች፡፡ ያም ሆኖ የሕዝቡ ብዛት ከምርቱ መጠን አንፃር በእጅጉ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ የስንዴ አገር ሆና እያለ እጅግ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ከውጭ ማስገባቷ የተሳሳተ ፖሊሲ አንዱ ምልክት ነው፡፡ ዓለምን የሚቀልብ የሚታረስ መሬት ይዛ እያለ ከዘመን እስከ ዘመን ትራባለች ኢትዮጵያ!!

ከምርጥ ዘር ጋር በተያያዘ በሚያሳዝን ሁኔታ አገር በቀል የአዝርዕት ዓይነቶች እየተመናመኑና እየጠፉም ይገኛሉ፡፡ ይህም በአጠቃላይ ሳይንሱን የራስ ማድረግ ላይ የመስነፋችን ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም አዳዲስ ሳይንሳዊ አሠራሮችን መፈተሽ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። እዚህ ላይ ተራራማ አገር ይዘን ተራራን ማዕከል ያላደረገ የግብርና ልማት እየተከተልን አገር ለማሳደግ መሞከር ከንቱ ልፋት መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ዝርዝር ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም የተፈጥሮ ዑደቱ ይኼው ስለመሆኑ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡

በመሆኑም የሕዝብ ቁጥራችንም በእጅጉ እየጨመረ ስለሆና የተትረፈረፈ የሰው ኃይልም ስላለን፣ በቀጣይነት የሚከናወን በተራሮች/ኮረብቶች ልማት ላይ የተቀናጀ አገራዊ ዘመቻ ቢታወጅ ዘላቂ ለውጥ ማስመዝገብ እንደምንችል አያጠያይቅም፡፡ ይህ ደግሞ ባልተጋነነ ወጪ ከአጋር አገሮች ጋር በመተባበር በዓመታት ውስጥ አስገራሚና ዘላቂ ውጤት ማግኘት ያስችላል፡፡ ለተሞክሮ ስዊዘርላንድ ተራራማ አገር ሆና ዘላቂ የተራራ ልማት ላይ የተረጋገጠ ስኬት ማስመዝገቧን ማየት ይቻላል፡፡ ይህቺው አውሮፓዊት አገር በዘርፉ ለመተባበር ተፈጥሯዊ ፍላጎት እንዳለትም ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ባለድርሻ አካላት፣ የፌዴራል አካላት፣ የምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ጭምር አስተባብሮ ከኅብረተሰቡ ጋር መሥራት የሚያስችል የፖሊሲ ድጋፍ ያለው ልዩ መዋቅር መገንባት ያስፈልጋል፡፡

አሁን ላይ እንዲህ ዓይነት ማሣ ዓለም ላይ ማግኘት የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ምንም ቢቸግር ተራራ ሊታረስ አይገባም፣ ከለማ በኋላ እንደሁኔታው ለአትክልት ልማት ይውል እንደሆነ እንጂ፡፡

ማሳያ (የአዋሽ ተፋሰስ ገመገሙ፣ የራያ ሰንሰለታማ ተራሮች)

ከድፍን ኢትዮጵያ የአዋሽ (ምሥራቅ) ተፋሰስን ነጥለን እንመልከት፡፡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሽቅብ ወደ ሰማይ 1000 ሜትር የሐሳብ ከፍታ ላይ እንውጣ፣ በዚህ ምናባዊ ከፍታ ላይ ተቀምጠን በዘመኑ ቴሌስኮፕ ረዳትነት ወደ ሰሜን የአገራችን ክፍል እንመልከት፡፡ እዚህ ላይ የስምጥ ሸለቆ ገመገሙን ተከትለን በቆላውና በደጋው መካከል ከሸዋ እስከ ኤርትራ ጫፍ ድረስ እንደመቀነት የተዘረጋውን ተዳፋት መሬትን እናስተውላለን፡፡ ይህ ተዳፋት ወሽመጥ ቁጥቋጦ እንኳን የሌለው የተራቆተና በጎርፍ የተላጠ በመሆኑ ጠፍ መሬት በሚመስልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከማሀል አገር እስከ ሰሜን ጫፍ ድረስ የተዘረጋው ይህ የተራቆተ መሬት በዝርዝር ተጠንቶ፣ በተሟላ ደረጃ ዝርዝር የልማት ዲዛይን ተሠርቶለት፣ እንደ መነሻ የልማት ሐሳብ ለአጋር አገሮች ወይም ድርጅቶች ቢቀርብ እንኳን ቢሊዮን ዶላሮች ይዞ እንደሚመጣ ብዙ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ አስተማማኝ ዘላቂ ልማት የሚያስገኝና ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት አንፃርም ፋይዳው ትልቅ እንደመሆኑ ተቀባይነቱም በዛው ልክ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ መሬት ሳይንስ በሚፈቅደው ደረጃ በትክክል ቢለማ አፋር ክልልን የበረሀ ገነት እስከማድረግ፣ የደጋው ገመገሙ ደግሞ የብዝኃ ሕይወት መኖሪያ የወንዞችና የምንጮች መፍለቂያ ከማድረጉም በላይ የገበሬው ጥረትም እጅግ ፍሬያማ ማድረግ እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡

ከአዋሽ (ምሥራቅ) ተፋሰስ ወጥተን በዚህ መንፈስ ወደ ገናሌ ተፋሰስ፣ ወደ ኦሞ ተፋሰስ፣ ወደ ተከዜ ተፋሰስና ወደ ዓባይ ተፋሰስ ፊታችን ስናዞር ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገሪቱ በእውነት መልማት የምትችልበት ሐሳብን በምናብ ማየት እንጀምራለን፡፡

በአዋሽ ተፋሰስ መልክዓ ምድራዊ ተረተር ላይ አንድ ጠለቅ ያለ አብነት የሚሆነን የራያ ሰንሰለታማ ተራሮችን (የተሻለ መረጃ በመገኘቱ) እንውሰድ፡፡ የግራካሱ ተራራ የራያ ሰንሰለታማ ተራሮች አንዱ አካል ሲሆን፣ እነዚህ ተራሮች ቆላውን ወደ ምሥራቅ እየተዉ፣ ኮረም የምትባለዋን ጥንታዊት ከተማና ታሪካዊው የሀሸንጌ ሐይቅን በግራና በቀኝ በኩል እያካለሉ ወደ ሰሜን የአገራችን ክፍል የሚያቀኑ ሰንሰለታማ የምድር ገጽታዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ተራሮች በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመነ መንግሥታት በተነጻጻሪ ያልተራቆቱ ተራሮች ስለነበሩ አያሌ ብዝኃ ሕይወትን በውስጣቸው የያዙ፣ እንደአሁኑ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ግብዓት ሳያስፈልግ የራያ ምድር ምርታማነት በእጅጉ አስተማማኝ ከማድረጋቸውም በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብን እጅግ ሀብታም ማድረግ ያስቻሉ ተራሮችም ነበሩ፡፡ ለዚህም የ1977ቱ ኢኒኖ—ወለድ አገር አቀፍ የረሃብ ሰቆቃ ያልነካው ምርታማነት በዚያ አካባቢ እንደነበረ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት በመላው አገሪቱ በተለይ በወሎና በትግራይ ክፍለ አገሮች ውስጥ አሰቃቂ ድርቅ በነበረበት እንኳን የኮረም ከተማ ዙሪያ ምርታማ የነበረበት ምስጢርም በእነዚህ ሰንሰለታማ ተራሮች ጤንነት ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የአካባቢው ሕዝብ ብዛት በአጠቃላይ ከ150 ሺሕ ያልበለጠበት ወቅት ቢሆንም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ በድርቁ ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ያስጠለለ ታላቅ ገድል እናገኛለን፡፡ ታዋቂው ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን ሰቆቃውን ቀርጾ ለዓለም ሕዝብ ያሠራጨውም ከዚሁ አካባቢ ነበርና በዚህም በአገሪቱ እጅግ ትልቁና ታሪካዊው የዕርዳታ ካምፕ ኮረም ላይ እንዲሠራ ምክንያት ሆነ፡፡

ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የእነዚህ ሰንሰለታማ ተራሮች ይዘት እየተራቆተ መጥቶ አሁን ላይ በሚያሳዝን ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመንግሥት ደረጃ ተራሮቹን ላልተገባ አገልግሎት ማዋልና ተገቢ ትኩረት መንፈግ ብቻ አይደለም፣ አጠቃላይ የገበሬውን ምርታማነት የሚያቀጭጭና ዛፎችን የሚበላ ችቡድ ፋብሪካ በመትከልም ጭምር ነው አካባቢው የተዳከመው፡፡ ምርቱን ጉድጓድ ውስጥ ለዘመናት በማኖር ይታወቅ የነበረው የራያ ገበሬ፣ ተራሮቹ ከመራቆታቸው ጋር አሁን በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ ብቻ ጥገኛ በመሆኑ የራያ ምድር ምርታማነት አደጋ ላይ ሲወድቅ በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ደግሞ በወቅትና ሁኔታዎች የሚወሰን ሳይሆን በባለሥልጣናት መልካም ፈቃድ የሚወሰን በመሆኑ ገበሬው በማይወጣው ዕዳ ውስጥ ገብቶ ንብረቱን እየሸጠ ዕዳ መክፈልና ልጆቹን ወደ ዓረብ አገር መላክ እንደ ባህል የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ የራያ ወጣቶች በየበረሃው ፀሐይ በልቷቸው፣ በየውቅያኖሱ ውኃ በልቷቸውና በሰው አገር ተገፍተውና ወድቀው ሲቀሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ይህ ጉዳት ከኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ ብዛት አንጻርም መግለጽ ይቻላል፡፡ በ1987 እና በ1999 ዓ.ም. በተደረጉ ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራዎች ሁሉም የትግራይ ከተሞች በሦስት እጥፍ አካባቢ ሲጨምሩ የራያዋ ኮረም ከተማ ሕዝብ ብዛት ግን በ53.84 በመቶ (ከ24,000 ወደ 15,600) በመቀነስ ማሽቆልቆሉም ይታወቃል፡፡ ለምን ቢባል የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢውን በመለቀቅ ጤነኛ ኢኮኖሚ ወዳላቸው ሌሎች አካባቢዎችና ወደ ዓረብ አገሮች ስለተሰደዱ ነው፡፡ ይህም በግራካህሱ ተራራ ላይ የነበረው ጣሊያን የሠራው መንገድ በኢሕአዴግ ዘመን እንዳይሆን ተደርጎ እንደገና በመሠራቱ የዚያ አካባቢ ማኅበረ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማፈናፈኛ በማጣቱ የመጣ ቀውስ ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህን ተራሮች ያራቆተው አስተሳሰብ ቁጥር ስፍር የሌለው በደሎች በነዋሪው ሕዝብ ላይ በማድረሱም ጭምር ነበር የስደቱ መንስዔ፡፡  

የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 3 አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ “የልማት እንቅስቀሴ ዋና ዓላማ የዜጐችን ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶች ማሟላት ይሆናል” የሚለውን መብት ሙሉ በሙሉ ዓላማውን ስቶ የልማት እንቅስቃሴ ቀዳሚ ዓላማው የመጨቆኛ ዋና መሣሪያ ሲሆን ግራካህሱ ተራራ ላይ የተደረገው በታሪክ ውስጥ ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የግራካህሱ መንገድ ለኮረም ከተማ እንዲሁም ለኦፍላ ወረዳ ብቸኛው በር ነው፡፡ ጣሊያን ከአዲስ አበባ አስመራ የሚዘልቀው መንገድ በሠራበት ወቅት የመንገድ አመራረጡ በኮረም በኩል ሀሸንጌ ሐይቅን አቋርጦ እንዲያልፍ ያደረገበት ቀዳሚ ምክንያት የመንገድ ልማት ዋና አስፈላጊነቱ ማኅበረ ኢኮኖሚውን ማሳለጥ በመሆኑ ነበር፡፡

በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ግን የልማት ዋነኛ ዓላማ ፖለቲካ ብቻ በሚመስል መልኩ የግራካህሱ መንገድን በማበላሸት የራያ ማኅበረ ኢኮኖሚ ላይ አሁን ድረስ ሳንካ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለሥልጣን “የአቀበት የምህንድስና ስታንዳርድ” በሚፈቅደው መሠረት ግራካህሱ ላይ መንገድ ባለመገንባቱ፣ ትልቁ የራያ ኢኮኖሚን የሚይዘው የኦፍላ (ኮረም) ኢኮኖሚ ከሌላው ራያ ተቆርጦ እንዲቀር ሆኗል፡፡ ከመላው አገራዊ ኢኮኖሚ ወረዳዋ እንደ ደሴት ተቆርጣ እንድትቀር ምክንያትም ሆኗል፡፡ በመሆኑም በኮረም በኩል የሚያልፍ ማጓጓዣ ይቅርና ራሳቸው ነዋሪዎቿ እንኳን ከወረዳው ለመውጣትና ለመግባት አጋጣሚ መጠበቅ ዕጣ ፈንታቸው ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢው ከልማት ውጭ ከመሆኑም በላይ ከከተማነት ወደ መንደርነት የወረደች ከተማ ኢትዮጵያ ውስጥ ብትኖር (በአሰብ መንገድ ላይ ከሚገኙ ከተሞች ውጭ) ኮረም ብቻ መሆኗ እርግጥ ሆነ፡፡ የግራካህሱ መንገድ የአስፋልት መንገዶች በማይሠሩበት ዲዛይን፣ ለአደጋ በሚያጋልጥ ዝቅተኛ ስንታንዳርድ በመሠራቱ “የሞት ጎዳና” እስኪባል ድረስ እጅግ አያሌ ወገኖች በመኪና አደጋ በየጊዜው ለ15 ዓመታት አልቀዋል ተጎድተዋል እየተጎዱም ይገኛሉ።

በራያ ምድር ላይ የተንሰራፋው ችግር ሀሸንጌ ሐይቅንም የነካ ነው፡፡ በእርግጥ የራያ ሰንሰለታማ ተራሮች በመራቆታቸው ሀሸንጌ ሐይቅ አደጋ ላይ መውደቁ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ያለው፣ በሰሜንና በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነ ሐይቅ፣ ለራያ ሕዝብ ልዩ ስጦታና እጅግ ልዩ በሆነ መልክዓ ምድር ላይ የሚገኝ ሐይቅ ቢሆንም እንደ ሀብት ተቆጥሮ አያውቅም፡፡ በአገር ደረጃ አያሌ ሰው ሠራሽ ሐይቆች በሚሠሩበት ዘመን ላይ የክልሉ ብቸኛው የተፈጥሮ ሐይቅ የሆነው ሀሸንጌ ግን እንደ የጠላት ሀብት እንዲጠፋ የተፈረደበት ይመስላል። የልማት ምልክት እንዳይዞርበት ተደርጎ የከብቶች መጠጫ ብቻ ሆኖ በከፊል ጭቃ እስከመሆን መድረሱ ያሳዝናል። በእርግጥ ይህን ሐይቅ በቀላሉ መከላከል ሲቻል አሁን አብዛኛው ክፍል መድረቁና እንደ ሀብት አለመቁጠሩ ሳያንስ ከታሪክና ከካርታ እንዲሰረዝ መደረጉ ደግሞ ሌላው አሳዛኝ ገጽታው ነው፡፡ ይህም የድሮ ካርታዎችና የአሁን ካርታዎችን በማነጻጸር ማረጋገጥ ይቻላል። በሀሸንጌ ጉዳይ አሁን ላይ እጅግ አሳሳቢው ነገር ደግሞ የክልሉ መንግሥት ሐይቁን የመታደግ ሥራን በማስቀደም ፈንታ ኢንቨስትመንት በሚል የይዞታ ቅርምት ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩ ነው።

ይህ የአዋሽ ተፋሰስ፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የመላው አገሪቱ የልማት ስትራቴጂና የሀብት አጠቃቀም ኢሳይንሳዊነት ማሳያ ተደርጎ የተወሰደ ቢሆንም በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ከዚህ የባሰ ጉዳት ስለመኖሩ የሚያሳዩ ጅምር ጥናቶች አሉ፡፡  

  1. ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ተራሮች መራቆት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮች መደህየትም ቀጥተኛ ምክንያት የመሆን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ተራሮች ልማት ማለት የመላው ምሥራቅ አፍሪካና የሀገረ ግብፅ ልማት ተደርጎ ቢወሰድ ምክንያታዊና ሳይንሳዊ ነው፡፡ 

(ሀ) ድህነትን ከሥር መሠረቱ ለመንቀል፡- ድህነት ለአንድ ኅብረተሰብ የሁሉም መጥፎ ነገሮች ምንጭ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ የተራራ ሕዝቦች የመጨረሻ ደሃ ከሚባሉ ሕዝቦች መካከል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የከተማ ጎዳናዎች ላይ እየለመኑ የምናገኛቸው ዜጎች አብዛኞቹ ከከፍተኛ ቦታዎች የአገራችን ክፍል የመጡ ናቸው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ከተማ የሚፈልሰው የኅብረተሰባችን ክፍል ከዚሁ የአገራችን ክፍሎች የተሰደዱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይህ ለተራሮች/ኮረብቶች የተሰጠውን ትኩረት ያለመኖሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ድህነትን ከሥር መሠረቱ ለመንቀል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የምግብ ዋስትናና ዘላቂ ምርታማ የግብርና ሥራዎችን በቀላሉ ለማስፋፋት ኮረብቶችንና ተራሮችን ማልማት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም የቆላውም ሆነ የደጋው ምርታማነት በዘላቂነት እንደሚያሻሽለው የተረጋገጠ ነው፡፡ በተጨማሪም 20 በመቶ ላይ ያለው የሚታረሰው የመሬት ስፋትም በበለጠ ማስፋፋት ያስችላል፡፡

(ለ) ውኃ፡- የውኃ እጥረት የዓለም አቀፍ ሥጋት መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡ የሕዝብ ብዛት ዕድገት፣ የተጨናነቀ የመሬት አጠቃቀምና የአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ቦታዎች የውኃ ይዘት ላይ እጥረትን ያባብሳል፡፡ ይህ ደግሞ ለግብርና፣ ለኃይል ምንጭነት፣ ለኢንዱስትሪ ሊውል የሚችለውን የውኃ ሥርዓት ያዛባዋል፡፡ ሐይቆችና ወንዞችም የመድረቅ አዝማሚያ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። በመሆኑም ቢያንስ ለልማት አመቺ የሆኑ ተራሮችን በዘላቂነት በማልማት ተፋሰሶችንና ሥርዓተ ምኅዳሩን እንዲሻሻል በማድረግ የአገሪቱን አጠቃላይ ምርታማነት ማሻሻል ይቻላል፡፡

(ሐ) ኢነርጂ፡- በተለያዩ አገሮች ተራሮች ለአቅራቢያ ከተሞች ዘላቂ የኢነርጂ ምንጮች ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ተራሮች እንደ የውኃ ኃይል፣ የፀሐይ ኃይልና የንፋስ ኃይል ዓይነት የኢነርጂ ምንጮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋ ተራራማ ምኅዳር ካላቸው አገሮች ውስጥ አንዷ በመሆኗ የዘላቂ ኢነርጂ ድርሻን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ ተራሮቿን ማልማት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ተጨማሪ የመስኖና የኃይል ግድቦች ለመሥራትና ነባር ግድቦችም የውኃ ጉድለት እንዳያጋጥም ከተፈለገ ተራሮች ሊለሙ ግድ ነው፡፡ ይህም ወደ ኢንዱስትሪያል የሚያሻግር ኢኮኖሚ ለመገንባት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይኼው ዘላቂ ኢነርጂ ለተራራማ ማኅበረሰቦቻችንም ጭምር ተደራሽ በማድረግና ተራሮች የልማት ማዕከል በማድረግ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማሻሻል ይቻላል፡፡

(መ) ደኖች፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕይወት አስፈላጊ ነገር ሁሉ ከተራሮቹ ጋር የተገናኘ ቢሆንም እንደ ጣውላ፣ ነዳጅ፣ የሽቶና የሕክምና ዕፀዋት፣ የእንሰሳት መኖና የሰዎች ምግብ በቀጥታ ከተራራ ደኖች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ደኖች ካርቦን ዳይኦክሳይ (የኢትዮጵያ ተራሮች የተረሱት የምሥራቅ አፍሪካ እስትንፋሶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርየኢትዮጵያ ተራሮች የተረሱት የምሥራቅ አፍሪካ እስትንፋሶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር ) በመቀነስና መሬትን የከበበው የኦዞን ርብርብ አየርን በማጠናከር ተፈጥራዊ አደጋዎችን በመከላከል ምድርን ይጠብቃሉ፡፡ ለድህነታችን አንዱ መንስዔ የሆነው የአፈር መሸርሸርን ይከላከላሉ፡፡ የከርሰ ምድር የውኃ መጠንን ያሻሽላሉ፡፡ ብዝኃ ሕይወትን አቅፈው ይይዛሉ፡፡ የአካባቢው የእርሻ ማሳዎች ምርታማነትም በእጅጉ ይጨምራሉ። ስለዚህ ተራሮቻችን በደኖች በመሸፈን በዘላቂ የደኖች ጥበቃ ማዕቀፍ ሥር እንዲሆኑ በማድረግ ብቻ እንደ አገር ምርታማነትን መጨመር እንችላለን፡፡ አሁን ላይ እንደሚደረገው፣ ያለምንም ጥናት በዘፈቀደ ሁሉም ዓይነት ተክሎችን የትም መትከል ግን ልማት እንዳልሆነና ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መታወቅ አለበት፡፡    

(ሠ) የአየር ንብረት ለውጥ፡- ካርባን ዳይኦክሳይድ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በአየር ውስጥ መጠኑ መጨመሩን እ.ኤ.አ. የ2019  ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ይህ አደገኛ የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ እየገባን ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ የተራራ ሥርዓተ ምኅዳር ደግሞ በአየር ንብረት ለውጦች በቀላሉ እንደሚረበሽ ይታወቃል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የመሬት መራቆትና የደኖች መመንጠር እያባባሰ ለአዝርዕት የሚሆነው የመሬት ስፋትን በቀጣይነት እንዲሽመደመድ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የተራራ አካባቢ መራቆትን በዘላቂ ልማት በማሻሻል የምኅዳሮች አገልግሎትን መጨመርና ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅ አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው፡፡ በውኃና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ዙሪያም መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡   

(ረ) ብዝኃ ሕይወት፡- ተራሮች የብዝኃ ሕይወት መኖሪያ ናቸው፡፡ ቁልፍ ለሆኑ አዝርዕትና የእንስሳት ወሳኝ ጀነቲክ የተፈጥሮ ሀብቶችን ይይዛሉ፡፡ የመሬት አጠቃቀም ለውጥና የአየር ንብረት ለውጥ ለተራራ ነክ አሴቶች እጅግ አስጊ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተራሮች ቢለሙ ከብዝኃ ሕይወት የሚገኘውን ጥቅምና እሴት ማስጠበቅ ይቻላል፡፡

(ሸ) ቱሪዝም፡- ተራሮች ቢለሙ ውብ የመሬት ገጽታዎች ናቸው፡፡ መጪው የቴክኖሎጂ ሁኔታ ተራራን እንደ ልብ የሚያንሸራሽር እንደሚሆን የታመነ ነው፡፡ በመጪው አሥር ዓመታት ውስጥ ተራሮች የቱሪዝም ዋነኛ መዳረሻ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይህ ደግሞ ለዜጎች ትልቅ የገቢ ምንጭ፣ ለመንግሥትም የምንዛሪ ምንጭ በመሆን ኢኮኖሚው ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ በእርግጥ ሳይንስና ጥቂት ጥበብ መጠቀም ከቻልን፣ ማንኛችንም ከምናስበው በላይ እጅግ ውብ አገር ናት ኢትዮጵያ!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሳይንስ ጸሐፊና በኢንጂነሪግ ዙሪያ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles