Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰብዓዊነት ይለምልም!

ሰላም! ሰላም! ‘ግርግር ለሌባ ያመቻል’ ቢልም የአገሬ ሰው፣ አሁን ግን ሌብነትም ሆነ አጭበርባሪነት በተባበረ ድምፅ እየተወገዙ መሆናቸው ደስ ያሰኛል፡፡ በአንድ ወቅት ተነግሮ የተረሳው የደመወዝ ማሻሻያ የመንግሥት ሠራተኛውን ልብ አቁሞ የሰነበተው አልበቃ ብሎ፣ አንዳንዱ አጭበርባሪ ነጋዴ የኮሮናን አጋጣሚ ካልተጠቀምኩ በማለት ጭራ ሊያስበቅለን ሲያደባ ተጋለጠ። ሰብዓዊነት አውሬነትን በለጠ፡፡ በስንቱ ጭራ አብቅለን የስንቱ ጭራ እንደምንሆን እንጃ፡፡ አሁን ደግሞ ሰብዓዊነት ውስጣችን እየዘለቀ ይመስላል፡፡ ይገርማችኋል በቀደም ዕለት ውዷ ማንጠግቦሽ ደውላልኝ፣ “በርበሬ አልቆብኛል!” አለችኝ። ድለላ ድርቅ መቶት አልቋል የማያልቅባት ማንጠግቦሽ ደግሞ፣ አንዳንዴ ለሰው ማሰብ ብሎ ነገር አታውቅም። ‹‹ሚስቶች ብዙ ጊዜ የባሎች ኪስ ባሻቸው ሰዓት ቢዝቁት የማያልቅ የአፍሪካ መንግሥታት ካዝና መስሎ ይታያቸዋል መሰለኝ፤›› የሚለኝ አንድ ጓደኛ ነበረኝ። እንግዲህ ትዳር እንደ ተጣማሪው ነው ብላችሁ እለፉት። ደግሞ ይኼንንም ነገር ብላችሁ አደራ በ‘ፌስቡክ’ ገጻችሁ ላይ ሥራ እንዳትፈቱበት። እንኳን ሰበብ አግኝቶ ይኼ ‘ፌስቡክ’ የሚሉት ምትኃታዊ የቴክኖሎጂ ሰሌዳ እንዲሁም እንዲሁ ነው፡፡ እኛም እንዲያው ነን!  

ታዲያ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹በዚያው ስትመጣ በርበሬውን ገዝተህልኝ እንድትመጣ፤›› አለችኝ። ቀጭን ትዕዛዝ ይሏችኋል ይህች ናት። ወዲያው ወደ አንዱ የባልትና መደብር ሄድኩ። በፊትም ከማውቃቸው የመደብሩ ባለቤት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠን ስናበቃ፣ ለወትሮው በ100 ብር የምገዛውን በርበሬ 180 ብር አሉኝ። ‹‹ምነው ይኼን ያህል ጭማሪ?›› ስላቸው ምንም ሳያፍሩ (የዕድሜን ክብርና ትህትና ሳይቀር ገንዘብ ሰለበው እኮ እናንተ?) ምንም ሳይሸማቀቁ፣ ‹‹አንበርብር ግድ የለም! እኔና አንተ አንቀያየምም። ይኼ ግርግር ሲያልፍ ተመልሰህ መጥተህ በለመድከው ሒሳብ ትወስዳለህ፤›› አይሉኝ መሰላችሁ? ሕዝብ አዳምን እያሸበረ ያለውን ኮሮና አጅሬው ግርግር ብለው የናቁት ምን ተማምነው እንደሆነ እንጃ፡፡ እሳቸውንም ሞት የማይጎበኛቸው ይመስል የት ሆነው ለመብላት እንዳቀዱም ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ በተለይ አዘውትራችሁ ጎራ የምትሉለት ባለመደብር፣ ፊት ለፊት በአደባባይ ዘረፋ ላይ መሆኑን አሳስቆ ሲያጫውታችሁ ቅምም አይለው። እንዲህ ዓይነቱ ነው እንግዲህ ዓይንህ ላፈር እየተባለ ያለው፡፡  አልጠግብ ባዩን አለፍ ብዬ ከወደ ጥጉ ዘንድ ያሉት ባለመደብር ጎራ ስል፣ እንደ እናት በስስት የሚያዩ ባለመደብር ሸቀጣቸውን ቅናሽ በቅናሽ አድርገው አገኙሁዋቸው፡፡ ‹‹ምነው እማማ ይኼ ሁሉ ቅናሽ? ከማለቴ ሳይቸግረኝ፣ ‹‹አንበርብር በዚህ ጊዜ ካልተረዳዳን መቼ ልንረዳዳ ነው? እኔስ ወገኖቼ እየተቸገሩ ከጉሮሮዬ የሚወርድልኝ ይመስልሃል?›› ሲሉኝ ዕንባዬ ከየት መጣ ሳልለው ዱብ ዱብ አለ፡፡ ራሴን ጭምር እየታዘብኩኝ እንዲህ ነው እንጂ የሚያምርብን ማለቴ የታወቀኝ፣ ሌሎች ሸማቾች እኚህን እናት በምርቃት ሲያወድሷቸው ነው፡፡ ከመረገም መመረቅ ምን ያህል የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ እኚህ እናት ዓይን ውስጥ አየሁት፡፡ አለማየት እንዴት ይቆጭ ይሆን!

‹‹እንዲያው ግን እኛ በሽንኩርቱም፣ በቲማቲሙም፣ በዴሞክራሲውም፣ በብሔሩም፣ በምርጫውም… እንተዛዘባለን እንጂ፣ የቁርጡ ቀን ሲመጣ እኮ የወጣልን ሰዎች ነን፤›› የሚሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ልጃቸው ደግሞ በፈንታው፣ ‹‹ቁርጡ ሲመጣ ብንተባበርም የቁርጡን ቀን ሰብዓዊነታችን በደህናው ቀን ምን እንደሚወጠው እንደገረመኝ አለሁ፤›› ሲለኝ ነበር የሰነበተው። ወይ መተሳሰብ? እያልኩ በልቤ እኔም ዝም ብዬ አዳምጥላችኋለሁ። እኔማ አንዳንዴ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እኛ መተሳሰብ ስንጀምር ይነሳል ተብሏል እንዴ እያልኩ እተክዛለሁ። እዚህ መሀል የተሰነቀሩ እሾኮችን ሳልረሳ ማለት ነው፡፡ እንደፈረደብኝ የደላላ ጭንቅላቴን ሳሠራው አንዳንዴ ይኼ ቫይረስ ሊፈጀን ቢነሳም፣ በሌላ በኩል ከውስጣችን ጠፍቶ የነበረውን መተሳሰብ ይዞ ከተፍ ያለ ይመስለኛል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢያቱ በዝቶ እብሪት ሲወጥረው፣ የሚያስተነፍስ ነገር ሲያገኝ ይበርድለት እየመሰለኝ አስባለሁ፡፡ እናንተንም እንደ እኔ ያሳስባችሁ ይሆን? ለማወቅ ያህል ነው!

መተሳሰብና መረዳዳት አይሆንልንም ሲባል ታዲያ ‘ምን እሱ!’ ‘ምን እሷ!’ እየተባባልን ስለማያገባን ሰው ማንነት ስንሰለቅጥባቸው የነበሩትን የባከኑ ጊዜያት ለማስታወስ ያህል ነው። እንዴ! በዚህች በዚህችማ መቼ እንታማለን? ትንሽ ዙሩን አክረን እንጫወት መሰለኝ። ይኼውላችሁ እንዴት መሰላችሁ? ጥሎብን አንዴ እንኳ መልኩን አይተን ስለማናውቀው ሰው የግምት ሐተታ መተርተር፣ የግምት ማንነትና ሰብዕና የመለጠፍ ‘ሆቢ’ እንደነበረን አይዘነጋም። ሰውን ሳናውቀው መውደድና መጥላት ማለቴ ነው፡፡ መቼም ይኼ ለእናንተ እንግዳ አይደለም፡፡ ጠልቀን ነገር የመመርመርና የማጤን ትዕግሥት ስላልፈጠረብን ደስ ያለንን ቅፅል ስም እየለጠፍን ያለ ስሙ ስም የምንሰጠው ሰው ብዛቱን አትጠይቁኝ። መቼም በደህና ነገር መተሳሰብ አይቀናንም ነበር፡፡ በግልብ ሒስና ሽሙጥ ጥሩ ትስስር አለን። አያችሁልኝ? የእኛ መተሳሰብ ፍሬ አልባ ሽሙጥና ሹክሽክታ ነበር። ማን ነበር፣ ‹‹ይህ ኅብረተሰብ የተሳሰረው በሐሜትና በወሬ እንጂ በጠንካራ የወንድማማችነት መንፈስ አይደለም፤›› ብሎ የነበረው? እውነቱን እኮ ነው፡፡ አሁን ግን ወሳኙ ጊዜ ሲደርስ ይህ አባባል መቀየሩ አይቀርም፡፡ ለምን ብትሉኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ፣ ኮሮና ቫይረስ የወደፊቱን ዓለም ሥርዓት እንደሚለውጥ ምልክቶች ስለታዩ ነው፡፡ የተማረ ይግደለኝ እንዳልል ከተማረ የማይሻሉ ዙሪያችንን ብዙ አሉ!

እንዲያው ለአዲስ ነገር መደንገጥ የሰው ልጅ ፀባይ ሆነና ኮሮና ቫይረስ አስደነገጠን እንጂ፣ ዘመን ያስቆጠረው ቫይረስ ያለው እዚሁ እኛ ዘንድ ነው ይባላል። የምሬን ነው! ለዚያም ይመስለኛል የአሁኑን ነቄ ነኝ ባይ ትውልድ ጨምሮ እርስ በርስ ስንናከስ የኖርነው፡፡ እናላችሁ ከአንድ ወዳጄ ጋር እንዲህ ስለሰው የግል ኑሮ መፈትፈት ባህላችን እያወራን ቆየንና ይሉኝታ ጋ ስንደርስ ምን አለኝ መሰላችሁ? ‹‹አንበርብር ይሉኝታችንም ቢሆን ጊዜና ሥፍራ ካለመምረጡ የተነሳ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው የሚሠራው፡፡ በዚህ ጥንቃቄ በሚያስፈልግበት ጊዜ ተው መጨባበጥ ቀርቷል ያልከው ወዳጅህ ያኮርፍሃል፤›› አለኝ። “እንዴት?”  ስለው፣ ‹‹ምን እንዴት አለው? በይሉኝታ የምንታማውን ያህል እውነት  ቢሆን ኖሮ ይኼን ሁሉ ዘመን በሥልጣን ይገባኛል፣ በሀብት ይገባኛል፣ በታሪክ ይገባኛ፣ በመሬት ይገባኛል. . .ያ ሁሉ ደም ይፈስ ነበር?” አይለኝ መሰላችሁ? በበኩሌ የደም ታሪክ ሲነሳብኝ አልወድም። ሥርዓት ባልጣሰ ጤናማ የደም ዝውውር ምክንያት ቆሜ መሄዴን እያወቅኩት፣ ሕግና ሥርዓት የሚጥሰው የዚህች መከረኛ ምድር የደም ታሪክ ሲነሳብኝ ቃንዛ (የደም ሥር ሕመም) ይይዘኛል፡፡ አለመታደል አትሉም ታዲያ!

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል። ምን ሆነ መሰላችሁ? ዘመናዊ ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤት ለማከራየት ተፍ ተፍ እያልኩ እንቅስቃሴ ተገታ፡፡ ላንኖርበትና ላንኖርለት የምንሮጥለት ጉዳይ ብዛቱ እኮ! ከቤታችሁ ሆናችሁ ሥሩ በሚባለው ማበረታቸወ መሠረት፣ በስልክ ብዙ ከባዘንኩ በኋላ አንድ ደንበኛ አገኘሁ። ሰውዬው ቤቱን በቪዲዮ አይቶ ሲያበቃ  ሊከራይ መወሰኑን አስታወቀ። ውል መፈራረሚያው ሰዓት ደረሰ። ውሉ ግን እንዴት ነው የሚፈረመው? ለጊዜው ምንም አማራጭ ስለሌ እንደ ምንም ተብሎ ውሉ ሊፈረም ሲቃረብ ስልኩን አውጥቶ ለባለቤቱ ደወለ። ጠቀም ባለ ገንዘብ ስለሆነ ቤቱ የተከራየው ጫን ያለ ‘ኮሚሽን’ ኪሴ ሊገባ ስለሆነ ብዬ ፏ ብያለሁ። በጠፋ ሥራ ያልታሰበ ሲሳይ ሲገኝ የደላላ ፋሲካ እኮ ማለት ይኼ ነው፡፡ አፍታ ሳይቆይ ደስታዬ ወደ ሐዘን ተገለበጠ። ተከራዩ፣ ‹‹የአንድ ዓመት ውል ተፈራርመናል፤›› ብሎ በስልክ ለባለቤቱ ሲናገር አከራዩ ሰማው። ስልኩን እንደ ዘጋ፣ ‹‹ይቅርታ የተፈራረምነው ውል የስድስት ወር እኮ ነው የሚለው፤›› አለው። ተከራዩ፣ ‹‹የለም ለአንድ ዓመት ነው መከራየት የምፈልገው፤›› አለ። ‹‹የምትፈልገው እንዲያ ሊሆን ይችላል በበኩሌ ውል እንድናድስ የምፈልገው በየስድስት ወር ነው፤›› አለ አከራዩ። በፍላጎትና በተጨባጭ ሀቁ መሀል ቆሞ ለመፍረድ ውሉ ሲታይ ለስድስት ወር ይላል። በዚህ ተጣልተው ውሉ ፈረሰ። ድንጋጤዬ ትኩሳቴን ጨምሮት ኳረንቲን ሊያስገባኝ ምንም አልቀረውም፡፡ ድንጋጤዬን ያየ አምቡላንስ ቢጠራ አይቀርልኝም ነበር፡፡ ነበር ባይኖር ምን እንሆን ነበር!

እኔም አላለልኝም ሌላ ተከራይ ፍለጋ መማሰን ስጀምር ድንገት ምሁሩን የባሻዬን ልጅ መንገድ ላይ አገኘሁት። ስለሥራ ስናወራ የሆነውን ብነግረው፣ ‹‹እንኳን ይኼንን የምንበላውን ምግብ ‘ኤክስፓየር ዴት’ የማናነብ እኮ ነን፤›› ብሎኝ ሳቀ። የባሻዬ ልጅ ብዙ ነገሮች ላይ ሲበሳጭ እንደ እኔ ቅርብ ሆኖ የታዘበው የለም። በደካማ የማንበብ ባህላችንና በጠንካራ የሥነ ምግባር ባህላችን ላይ ግን ዛሬ ዛሬ ከመበሳጨት መሳቅን እየመረጠ ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቻችንም ብንሆን ከቁጭትና ብስጭት ያተረፍነው ነገር ስላጣን፣ ሳቅ ፈልጎ መዝናናት አማራጫችን ሆኗል። በነገራችን ላይ ልማት ከድህነት መውጫ ብቻኛ አማራጭ ነው እየተባለ፣ ከመንገድና ከከተማ ልማት በታች የአዕምሮ ልማት ጉዳይ መታየቱ እስከ መቼ በይደር ይታያል? እኛስ ለስንቱ አሳዛኝ አካሄዳችን የዕዝን ተሸክመን እየኖርን ትከሻችን ይጎብጣል? ይኼ ትከሻችን የማይችለው የለም ማለት ነው!

በሉ እስኪ ደግሞ እንሰነባበት። የዘንድሮ ወበቅ ያው የእኛን ፀባይ ወርሶ ነው መሰል፣ ልባችን ቀጥ ማለት እስኪቀረው ያነፍረናል። ቅዝቃዜ የኮሮና መደበቂያ ነው፣ ሙቀት ደግሞ አመድ ያደርገዋል የሚለውን ወሬ ባላምንም፣ ለበጎ ነው ብዬ ተመሥገን ማለቴ አልቀረም፡፡ መቼም ይህቺ ምድር አንዴ ሲሠራት የጥድፊያ አድርጓት የለ? ታዲያላችሁ ሥራዬን ጨራርሼ ወደ ቤቴ ከመግባቴ በፊቴ አንድ ሁለት የምልባት የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ትዝ አችለኝ። የዛሬውን አያድርገውና ግሮሰሪያችን ጢም ብላ ትሞላለች። የሙላቷን ያህል የዘለሰኛና የእንጉርጉሮ ግጥሞች ያጥለቅልቋታል። ‘የባቲን ባሻገር ይሉታል አምባሰል፣ እህል እየበሉ ሰው ወዶ መሰልሰል’ ሲል ዘፈኑ አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹ኧረ ዘንድሮስ እህሉም አልተገኘ እንኳን የናፈቁት፤›› ይላል። ‘የአምባሰል ዝንጀሮ ሲሄድ አጎንብሶ፣ ሲመለስ ቀና አለ የልቡን አድርሶ፤›› ሲል አንዱ ከወዲያ፣  ከወዲህ ደግሞ ታዳሚዎች እየተቀባበሉ፣ “ዝንጀሮ እንኳ ባቅሙ የልቡ ይደርሳል፣ መቼ ይሆን እኛስ የልባችን የሚደርሰው?” ይባባላሉ። “አንድ ቀን!” ይላል ጥጉን የያዘ ሰካራም። ይኼ ነገር የበላ ጠጪ አሁን ቤት አድቦ ምን እያደረገ ይሆን የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ልብ አድርጉ ትዝታ እየቀሰቀስኩ አይደሁም!

ተመስጦ፣ ትካዜና ትዝታ ወሮኝ በቆምኩበት የባሻዬ ልጅ ገና ከመምጣቱ፣ ‹‹ዛሬስ የጤና አትመስልም እንዴት ነው ነገሩ?›› አለኝ። ‹‹ምን ታደርገዋለህ የምንሰማውና የምናየው ሁሉ ያስፈራል፡፡ በሥልጣኔ መጥቀናል ያሉት አልቻልነውም ያሉት ይኼ ጉድ ከስንት ነገራችን አፈናቀለን እኮ. . .›› ስለው፣ ‹‹አልገባኝም?›› አለኝ፡፡ ሳስበው የነበረውን እየነገርኩት በአካል መራራቃችን እስከ መቼ ይሆን የሚቀጥለው ስለው፣ ‹‹ይኼውልህ አንበርብር እኛ ይህንን ያህል ዘመን ምድር ላይ ስኖር ከሐሳባችንና ከፍላጎታችን ይልቅ፣ በተጨባጭ የሚታየው ኑሮአችን እኮ በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረ ነው። ዛሬም በግልጽም በሥውርም ጦርነት ላይ ነን፣ ዛሬም ድህነት ይጫወትብናል፣ የማስገበርና የአለመገበር ፖለቲካ እባቦችን ካብ ለካብ እያስተያየ እያፋጀን እዚህ አድርሶናል፤›› አለኝና ትክ ብሎ አየኝ። ጥቂት ትንፋሹን ሰብስቦ ሲያበቃ፣ ‹‹ዛሬ ድረስ የምግብና የመኖሪያ ቤት ዕጦት እየተጫወተብን፣ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ከስግብግብነት ግጭት ፈቀቅ አንል ማለታችን ነው የዚህ ሁሉ ትርጉም፤›› በማለት ወደ ሰማዩ ጠቆመኝና አይኖቹ ዕንባ አቀረሩ። እኔም እሱን ተከትዬ የአካባቢዬንና የአገሬን ኬላ ወጥቼ የሰው ልጅ ሕመም ተሰማኝ፡፡ ትንፋሽ አጥሮአቸው ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ እያሉ ዓይናቸው የሚንከራተቱ የሰው ልጆች ሥቃይ ተሰማኝ፡፡ በእነሱ ሕመም ውስጥ ራሴን በማግኘቴ በሐሳቤ ጭልጥ ብዬ የእነሱ አስታማሚ ሆንኩ። ሰብዓዊነት ይለምልም አትሉም ታዲያ! መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት