Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቤቶች ኮርፖሬሽን ከ18 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተከራዮች ባደረገው የኪራይ ቅናሽ 60 ሚሊዮን...

ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ18 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተከራዮች ባደረገው የኪራይ ቅናሽ 60 ሚሊዮን ብር እንደሚያጣ አስታወቀ

ቀን:

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለ18,153 ተከራዮቹ 50 በመቶ የኪራይ ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ በዚህም ቅናሽ በወር 60 ሚሊዮን ብር አጣለሁ አለ፡፡

በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ከተሞች 6,293 የንግድ ድርጅቶችንና 11,860 መኖሪያ ቤቶችን በማከራየት ላይ የሚገኘው ቤቶች ኮርፖሬሽን ባደረገው ግማሽ የኪራይ ዋጋ ቅናሽ፣ በአንድ ወር ውስጥ 60 ሚሊዮን ብር እንደሚያጣ፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ሞቱማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከቤቶቹ ኪራይ በወር ያገኝ የነበረው 120 ሚሊዮን ብር እንደሆነም አክለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ከ60 ብር እስከ 220 ሺሕ ብር ድረስ፣ እንዲሁም የንግድ ድርጅቶችን ከ4,000 ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በሚደርስ ዋጋ እንደሚያከራይ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ ኪራይ ከሚከፍሉት ድርጅቶች መካከል በውጭ ምንዛሪ ጭምር ግብይት የሚፈጽመው ድል ገበያ ሱፐር ማርኬት፣ እንዲሁም ሐራምቤ ሆቴል የመሳሰሉት መሆናቸውንም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለተከራዮቹ ቅናሽ ያደረገው ከሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ፣ የወረርሽኙ ሁኔታ እየታየ እንደ ሁኔታው ሊቀጥል ወይም ሊቀር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የ50 በመቶው ቅናሽ የሚያዝያ ወርን ብቻ የሚመለከት መሆኑን አስታውቀው፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በደንበኞች ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በየወሩ በመገምገም የሚቀጥሉትን ወርኃዊ ክፍያዎች መጠን በሚዲያ ያሳውቃል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሁን ባደረገው ቅናሽ ከግለሰብ ተከራዮች በተጨማሪ ሆቴሎች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ መጋዘኖች፣ ወርክሾፖች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ካፊቴሪያዎች፣ ቢሮዎችና በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ረሻድ አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት (ኪቤአድ)፣ ከዚያም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በመባል ይጠራ የነበረው ቤቶች ኮርፖሬሽን በቅርብ ዓመታት በ30 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንደገና መደራጀቱ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ቤቶች እየገነባ ለመንግሥት ሹማምንት፣ እንዲሁም ለነዋሪዎች በኪራይ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ በ1967 ዓ.ም. የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ለማድረግ በወጣው አዋጅ 47/67 የተመሠረተው የቀድሞው ኪቤአድ የአሁኑ ኮርፖሬሽኑ፣ ከድርጅቶችና ከግለሰቦች ላይ በተወረሱ ቤቶች በደርግ የመጀመርያ የሥልጣን ዘመን ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ምንም እንኳን የሚያስተዳድራቸውን የቀበሌ ቤቶች ተከራዮች ላይ ቅናሽ ማድረጉን ባያስታውቅም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ባደረጉት ጥሪ፣ በርካታ የግል መኖሪያ ቤትና ድርጅቶች አከራዮች ለተከራዮቻቸው እስከ ሦስት ወር የሚደርስ የኪራይ ቅናሽ ሲያደርጉ፣ ሙሉ በሙሉ ኪራዩን የተው ግለሰቦችም አሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ግን ራሱ እያከራያቸው በሚገኙት የቀበሌ ቤቶችና ድርጅቶች ላይ ቅናሽ እንዲያደርግ እየተጠየቀ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...