ከፊት ቢዘጉም ከኋላ ክፍት መሆናቸውን ገልጿል
ዓለምን እያናወጣት የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መኖሩ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በተለይ ሰዎች ይሰባሰቡባቸዋል ከተባሉት ውስጥ ከሺሻ ማስጨሻዎች፣ ከጫት መቃሚያዎችና ከመጠጥ ቤቶች ፖሊስ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት እያጋጠመው መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ እንደገለጹት፣ ይህ አደገኛ የሆነ ገዳይ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን በማስተማርና በማስገንዘብ የአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም፣ ፈታኝ ሁኔታዎች እያጋጠሙ ነው፡፡
መንግሥት መመርያ በማውጣት ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸውን ቦታዎች ማለትም የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች፣ የጫት ማስቃሚያዎችና የመጠጥ ቤቶች ለጊዜው ሥራ እንዲያቆሙ መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን ስለወረርሽኙ ግንዛቤ ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው ሰዎች ሺሻ ሲያጨሱባቸውና ሲቅሙባቸው የነበሩ ቤቶች ከፊት ለፊቱ ‹‹ታሽጓል›› የሚል ማስጠንቀቂያ የተለጠፈባቸው ቢሆንም፣ እነሱ በኋላ በር በኩል ከፍተው በማስገባት እንዲያውም ከበፊቱ በበለጠ ብዙ ተጠቃሚዎች እንደሚስተናገዱ እንደ ተደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡
የወረርሽኙን አይምሬነት በሚገባ የተገነዘቡ ሰዎች ከሺሻ ቤት ወይም ከጫት መቃሚያው ቦታ ወደ ሕዝቡ የሚቀላቀሉት ወገኖች በቫይረሱ የተጠቁ ቢሆኑ፣ ምን ያህል ሕዝብ እንደሚጎዱ በመረዳታቸው ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ኮማንደር ፋሲካ እንዳብራሩት፣ ለምሳሌ ያህል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ግቢ አካባቢ በሦስት የቀበሌ ቤቶች ውስጥ 431 ሰዎች ሺሻ ሲያጨሱና ጫት ሲቅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በአንድ ቤት ውስጥ ከ140 በላይ ሰዎች መከማቸታቸውን ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በአጋጣሚ በቫይረሱ የተጠቁ ቢሆኑና ወጥተው ቢበክሉ፣ ምን ያህል ወገኖች በወረርሽኙ ሊጠቁ እንደሚችሉ ለማወቅ ነብይ መሆን እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን ሰዎቹ በቁጥጥር ሥር ቢውሉም ማሰር እንደማይቻል የተናገሩት ኃላፊው፣ የንግድ ቤቶቹን ባለቤቶች ለጊዜው በማሰርና ወረርሽኙን በተመለከተ የመንግሥትን መመርያ መጣስ አግባብ እንዳልሆነ በመምከር መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሌላ ደረቅ ወንጀል የታሰሩ ግለሰቦች በመኖራቸውና መንግሥት ከእስር እየፈታ ባለበት ሁኔታ፣ እነዚህን ሰዎች ማሰሩ ተገቢ ነው የሚል እምነት ስላልነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የጀመረውን ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ በመተላለፍ በተጠቀሱት ቦታዎች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ቦታዎች ሕገወጥነቱ በመቀጠሉ ለፖሊስ ተግዳሮት ቢሆንም፣ ለሕዝብ ደግሞ አደገኛ መሆኑን ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል፡፡
አሁን መንግሥት ሁኔታውን በማጤንና ዕርምጃም መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ጥሩ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሕዝብ ጤና በማይጨነቁና የመንግሥትን መመርያና ማሳሰቢያ የሚተላለፉ አፈንጋጮች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመው፣ ከፖሊስ ጎን የሚቆሙ ወገኖች ትብብራቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ ሌሎችም የጤና ባለሙያዎችን ምክር፣ የመንግሥትን መመርያዎችና በአጠቃላይ ለወረርሽኙ ትኩረት ሰጥተው የመከላከያ ማሳሰቢያዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ እንዲተባበሩና ከሕገወጥ ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡