Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትኮቪዲ 19 እና ስፖርት

ኮቪዲ 19 እና ስፖርት

ቀን:

ዓለም በማስክና መሰል ጨርቆች አፏን ሸፍናለች፡፡ ዓይኖቿ በበርበሬ የታጠኑ ይመስል ቀልተው ዕንባ አቅርረዋል፡፡ ጆሮዎቿ ክፉውን ላለመስማት በጥጥ ብትደፍናቸውም በሁሉም የዓለም ክፍሎች ሳያቋርጥ የሚደመጠው የአምቡላንስ ጩኸት መሸበሯ ግን የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እግርና እጆቿ አገር ሲያምስ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ ወንበዴ ተጠፍረዋል፡፡

ከፈጣሪ ቀጥሎ በሀብታቸውና በዕውቀታቸው አይነኬ የሚባሉ ታላላቅ አገሮችና መንግሥታት ኮሮና ቫይረስ ወይም በምህጻረ ቃሉ ኮቪዲ 19 እያስከተለ ላለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔ ተስኗቸው እርስ በርሳቸው መወነጃጀል የዕለት ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ዓለም በአጠቃላይ አየር እንደበዛበት ኳስ በጭንቀት ተወጥራለች፡፡

ለአንድ ነገር እጇን የሰጠች ይመስላል፣ ጭንቅላቷን በትኩሳት ሲያነዱ የነበሩ ችግሮቿና ጉሮሮዋን ሲከረክሩ የነበሩ ክስተቶች፣ አላስተነፍስ ያሏት መከራዎቿ ሁሉ በአንድ ቋት ተጠቃለው በኮሮና ተወክለዋል፡፡ የበለፀገውም ሆነ ያልበለፀገው፣ የወፍራሙም ሆነ የቀጭኑ፣ የሕፃኑም ሆነ የአዋቂው፣ የጥቁሩም ሆነ የነጩ የሁሉንም በር እኩል እያንኳኳ ያለው ኮዲቪ 19 ማነህ የሚለው ጠፍቶ የሰው ልጆች የጋራ ጠላት ከሆነ ወራትን ማስቆጠር ጀምሯል፡፡

- Advertisement -

ቫይረሱ የዓመታት ፀበኞቹን አሜሪካና ኢራንን ፍልስጤምና እስራኤል እንዲሁም ባላቸው ዕውቀትና በሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ ዓለም ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት የሆኑት አሜሪካና ቻይና፣ ሊቢያ፣ ሶርያና አፍጋኒስታን የሰላም አየር እንዲነፍስባቸው አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ የዓለምን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር እንደ ሱናሚ ድንገት የቀየረ ክስተትም ሆኗል፡፡

ይህ መጥፎ ወረርሽኝ የጥፋት እጁን ካሳረፈባቸውና ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ስፖርቱ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ በማይታየውና በፈረጠመው ጡንቻው አንቀርቅቦ ዘርሮታል፡፡ በዓለም ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችን የለከፈው፣ ቁጥሩ በየደቂቃውና በየሰዓቱ የሚጨምር መሆኑ እንደተጠበቀ አሁን ላይ ግን ወደ 100,000 ግድም ሰዎችን እየቀጠፈ የሚገኘው ወረርሽኝ፣ በስፖርቱ ዓለም በጉጉት ይጠበቅ የነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል፡፡

ውሳኔው በተለይ ለአዘጋጇ አገር ጃፓን ከምንም በላይ የከበደ ለመሆኑ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቢ፣ ‹‹በብዙ ፈተናዎች ያለፈውና የዓለም ሕዝቦችን በማቀራረብ እንዲሁም ለዓለም ሰላምን የሚሰብከው ውድድር እንዲራዘም ስንጠይቅ ከልብ እያዘንን ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ለፍተንበታል፣ ብዙ ገንዘብም አውጥተንበታል፣ ይሁንና ክስተቱ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን ሲገለጽ፣ የብርሃኑ ሻማ ለኳሽ ኦሊምፒክ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፤›› በማለት ነበር ዕንባ እየተናነቃቸው የዝግጅቱን መራዘም ዜና ይፋ ያደረጉት፡፡

ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በዚሁ ስያሜው ከአንድ ዓመት በኋላ በዛኑ ቀንና ወር እንደሚካሄድ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሰው ልጆች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በፈጠሩት የአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት 1916፣ 1940 እና 1944 ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ ሳይካሄድ መቅረቱ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ሌላው የዓለምን ሕዝብ ቀልብ መሳብ ብቻ ሳይሆን በተለይም ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየጎዳቸው በሚገኙት የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ፋይናንስ እየፈሰሰበት የሚገኘው እግር ኳሱም የዚሁ ምሕረት የለሽ ወረርሽኝ ሰለባ ሆኗል፡፡ በችግሩ ብዙዎቹ አገሮችና የዘርፉ ተዋንያን ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል፣ አንዳንዶቹ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው ወርኃዊ ክፍያ መክፈል አቅቷቸው በመንገዳገድ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ሊጎቹ ስለመካሄዳቸውና አለመካሄዳቸው የክለቦቹ ባለቤቶች የሚያውቁት አንዳች ነገር የለም፡፡ በየጊዜው የተለያዩ ሐሳቦች ቢነሱም ውኃ የሚያነሳና የሚጨበጥ ምንም ነገር መፍጠርም ሆነ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በሰኔ አልያም በሐምሌ ወር ይካሄድ ከሚለው ሐሳብ ጎን ለጎን ሁሉም ክለቦች በየአገራቸው በአንድ ካምፕ ውስጥ ገብተው ውድድራቸውን በዝግ ስታዲየም ያድርጉ የሚሉና ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባትና በቁጥጥሯ ሥር ባዋለችው ወደ ቻይና በመጓዝ ውድድሮችን እናካሂድ እስከሚለው ድረስ ብዙ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ሁሉም ማረፊያ እንዳጣች ወፍ ለመሆናቸው በግልጽ የሚያመላክት ሆኗል፡፡

ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እየፈሰሰበት የሚገኘውን ይህን ሊግ የሚመራው የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የሚያደርገው ቢያጣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና የኢሮፓ ሊግ ቀሪ ጨዋታዎችን በነሐሴ ወር የማካሄድ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል፡፡ እስካሁን ግን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳልቻለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እንዳሉ በሌላ ወገን የሚደመጡ አስተያየቶች ናቸው፡፡

በዕቅድ ደረጃ ከሆነ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርም ሆነ የየአገሮቹ የሊግ አመራሮች የመጨረሻ ይሆናል ያሉት ሁሉንም ውድድሮች በሰኔ ወር ማካሄድ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ደግሞ የሰኔው ካልተቻለ በሐምሌ ወር እንዲሆን የሚል ነው፡፡ ሁለቱ አማራጮች የማይሆኑ ከሆነ ደግሞ የ2019 እና የ2020 የውድድር ዘመንን መሰረዝ የሚለው ይጠቀሳል፡፡

የዓለም የእግር ኳስ አመራሮች በዚሁ መፍትሔ አልባ ወረርሽኝ ምክንያት እስትንፋስ ላጠረው እግር ኳስ ነፍስ ለመዝራት መሯሯጣቸው ግን አልቀረም፡፡ ከትልልቆቹ ባልተናነሰ የደቡብ አሜሪካውያኑ ኮፓ አሜሪካ፣ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ሌሎችም ምርጥና አፍ የሚያስከፍቱ ጨዋታዎች ወደ 2021 ተሸጋግረው ለአንድ ዓመት ተራዝመዋል፡፡

ከእግር ኳሱ ባልተናነሰ የአትሌቲክስ ውድድሮችም የዚሁ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሰለባ መሆናቸው ሐቅ ሆኗል፡፡ በርካታ ረብጣ ዶላሮችን ከሚያስገኙት መካከል የለንደን ማራቶን ከሚያዝያ ወር ወደ ቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ተዘዋውሯል፡፡ የቦስተን ማራቶን በተመሳሳይ ወደ መስከረም ወር፣ የአምስተርዳም፣ የፓሪስ፣ የባርሴሎና፣ የኒዎርክና ሌሎችም ውድድሮች የገጠማቸው ዕድል ተመሳሳይ ሆኗል፡፡

ወረርሽኙ ተከስቶ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓለምን ሳያዳርስ የተካሄደውና ከ300,000 በላይ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ የሚታወቀው የቶኪዮ ማራቶን ወረርሽኙን በመፍራት ከ200 የማይበልጡ አትሌቶች ብቻ ተሳትፈው ፍጻሜ ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡ የአትሌቲክሱ ዓለምም ልክ እንደ እግር ኳሱ ድንገተኛ ዱብ ዕዳ ወርዶበት ዕጣ ፈንታውን ለመወሰን የሚቻል አልሆነም፡፡

በዚህ ሳያበቃ ምርጡ የዓለም የመኪና ውድድር ፎርሙላ ዋን የመራዘም ዕጣ ፈንታ ገጥሞታል፡፡ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ምንም ዓይነት የመኪና ውድድሮች እንደማይኖሩም ተነግሯል፡፡ የአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ የምታስተናግደው ምርጡ የዓለም የመኪና እሽቅድድም ግምታዊ በሆነ ውሳኔ ወደ ሰኔ ወር ተራዝሟል፡፡

ወረርሽኙ ያልነካው ስለሌለ በሁሉም አገሮች እንደ አውስትራሊያው ጂፒ የመሳሰሉ ውድድሮች ተወዳዳሪዎቻቸው የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው እየተረጋገጠ መርሐ ግብሮቻቸውን ማራዘም ግድ ብሏቸዋል፡፡ እንደ ግራንድ ፕሪክስ፣ ቬትራን ግራንድ ፕሪክስና ሌሎችም ሆላንድ፣ ስፔንና ሞናኮ ላይ የሚደረጉ ውድድሮች በሙሉ ቢያንስ እስከ ሰኔ ወር የመራዘም ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡

የሞተር ሳይክል ውድድሮችም እንደ ፍራንስ ሞተር ጂፒ የመሳሰሉት ላልተወሰ ጊዜ ተራዝመዋል፡፡ የሜዳ ቴኒስ ፍራንስ ኦፕን ውድድሮች፣ የካሊፎርኒያው ቢኤን ቢ እንዲሁም በእስያውያን ዘንድ ከሚወደዱት ስፖርቶች ቴኒስ ቴብልና ሌሎችም ውድድሮች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ሌላው በእንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐር አዲሱ ስታድየም ሊካሄድ የታሰበውና ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው የሁለቱ ቡጢኞች የእንግሊዙ አንቶኒዮና የቡልጋሪያው ኩበርት ፍልሚያ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ታውቋል፡፡

የባድሜንተን፣ የፈረስ ውድድር፣ የራሊ ውድድሮችና የክብደት ማንሳት እንዲሁም የባስኬት ቦልና የመሳሰሉት ውድድሮች በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ውስጥ ከገቡት ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ እስከ አሥር ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማድረሱ የሚነገርለት የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ አሁን ባለው ሁኔታ የጥፋት ጡንቻውን ያላሳረፈበት ዘርፍ የለም፡፡

ወረርሽኙ ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋቲኖ ከዚህ በኋላ እግር ኳሱን ጨምሮ ስፖርቱ ለሁለት ተከፍሏል፣ ‹‹ከኮሮና በፊትና ከኮሮና በኋላ›› በማለት በኮሮና ሁሉም ነገር መለወጡንና ምናልባት የማይለወጠው ነገር ቢኖር ጎል ሲቆጠር የሰዎች ጩኸት ብቻ ሊሆን እንደሚችል ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...