Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኮሮና ከኃያላኑ መካሰሻ የሴራ ንድፈ ሐሳብ ማድሪያ እስከ ሐሰተኛ መረጃ መፈብረኪያ?

ኮሮና ከኃያላኑ መካሰሻ የሴራ ንድፈ ሐሳብ ማድሪያ እስከ ሐሰተኛ መረጃ መፈብረኪያ?

ቀን:

በያሬድ ንጉሤ

‹‹ጅማሬውን ከቻይና ያደረገው ኮሮና ቫይረስ እየመጣ ነውና ሺያኦሚ ሞባይል ስልካችሁን ጣሉት! ያለበለዚያ ግን በድምፅ መቀበያና ማስተላለፊያዎቹ ውስጥ እንዲሁም በመረጃ ሥርዓቱ በኩል ቫይረሱ ይተላለፍባችኋል!››፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ በዋትስአፕ የመልዕክት ማስተላለፊያ መተግበሪያ ለብዙዎች እንዲዳረስ የተደረገ ነው፡፡

ይኸው አስደንጋጭ መልዕክት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ‹‹ሕይወታችሁ ከምንም ነገር በላይ በእጅጉ ጠቃሚያችሁ ስለሆነ ሺያኦሚ ስልካችሁን ብትጥሉት ይበጃችኋል፤›› ሲል ያብራራል፡፡ ይህንን ጽሑፍ ያነበበ ምናልባትም ጽሑፉ በየትኛው ሥፍራ እንደተለቀቀ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ይህ ዘረኛና በብዙኃኑ ላይ የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተነገረለት ጽሑፍ የተለቀቀው ኢንዶኔዥያ ውስጥ ነው፡፡ በቻይና የኮሮና ቫይረስ እንደተከሰተ በተነገረበት ወቅትም አገሪቱ ከቻይና የምታስገባውን ተንቀሳቃሽ ስልክ ዜጎቿ እንዲጥሉ መልዕክት ተሠራጨላቸው፡፡ በኢንዶኔዥያ የሚገኙ ቻይናውያንንም ‹‹በበሽታው ምክንያት እንዳትቀርቧቸው›› የሚል ጽሑፍም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሚሊዮኖች እንዲዳረስ ሆነ፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጽሑፎች የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የበሽታ ወረርሽኞችና ራስን የማጥፋት ሙከራዎች እንደተደረጉ ሆነው ተቀናብረው በዓለም አቀፍ ደረጃ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከሚተላለፉት ሐሰተኛ መረጃዎችና የሴራ ንድፈ ሐሳብ ኃልዮቶች (Conspiracy Theories) ጎራ ተርታ የሚመድቧቸው አሉ፡፡

‹‹የኮሮና ቫይረስ የሰው ልጆችን ቁጥር ለመቀነስና ሆን ተብሎ በላቦራቶሪ የተፈበረከ ነው፤›› የሚል የሴራ ንድፈ ሐሳብ መላምትም አለ፡፡ ምንም እንኳን እስካሁን አሳማኝና ተጨባጭ ማስረጃ የሚያቀርብበት ባይገኝም ቅሉ፡፡

ከወደ አሜሪካ የማዕከላዊ የስለላ ተቋም (CIA) ያወጣው መረጃ ደግሞ ለነጩ ቤተ መንግሥት ሹማምንት ቻይና መጀመርያ ላይ ለበሽታው የሰጠችው ትኩረት አነስተኛና ማቃለል የበዛበት እንደሆነ፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ መሆኑን የሚናገር መረጃ የተበራከተበት እንደሆነ ስለመናገሩም ተወራ፡፡ የቻይና ባለሥልጣናትም ‹‹ቸልተኛ›› በመባል ተወረፉ፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎችም ቻይናን ያጥለቀለቀው ቫይረስ ‹‹በዩናይትድ ስቴትስ የበሽታና መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የተፈጠረ ነው፤›› አሉ፡፡ ለዚህም የማዕከሉ ኮሮና ቫይረስ ዘረመል አቀማመጥ የፈጠራ መብትን (Patent Right) በመጥቀስ ሞግተው ከ4,000 በላይ ዕይታን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሲያገኙ፣ በርካቶችም ጽሑፉን ለራሳቸው በመውሰዳቸውና በየገጾቻቸው በመለጠፋቸው ሚሊዮኖች እንዲያዩት ተደረገ፡፡ የአሜሪካ ‹‹ፋክት ቼክ›› ድረ ገጽ በበኩሉ ይህንን መረጃ ‹‹የተሳሳተ ነው››  ሲል አስታወቀ፡፡

በአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት ተጠንቶ በዋሽንግተን ፖስት የተዘገበ መረጃም፣ ‹‹ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ የትዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች ኮሮና ቫይረስ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉና በሽታው የባዮሎጂ ጦርነት ነው የሚሉ የሴራ መረጃዎች የተንሸራሸሩባቸው ስለመሆናቸው፤›› ወቅቱም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በነበሩት ሦስት ተከታታይ ሳምንታት እንደነበረ ያስረዳል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ አርቲ በሚባለው ታዋቂ የመንግሥት ሚዲያ በኩል፣ ‹‹የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊዎች ኮቪድ-19 አሜሪካ ኢራንንና ቻይናን ሆን ብላ ለማጥቃት የሠራችው ጅምላ ጨራሽ የቤተ ሙከራ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩትን ዜና በስፋት አስነበበ፡፡ ‹‹የአሜሪካ ወታደሮች በላቦራቶሪ ውስጥ ፈጥረው ያስፋፉት ቫይረስ›› እንደሆነም የሚያብራሩ ሪፖርቶች ብቅ ብቅ አሉ፡፡

ዋሽንግተን ታይምስ ደግሞ ቫይረሱ፣ ‹‹በቻይና ውሃን ግዛት ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ተዋህስያን ቤተ ሙከራ ተቋም ውስጥ እንደተነሳ›› ጠቀሰ፡፡ ይኸው መጣጥፍ ምክንያቱን ሲያብራራም፣ ‹‹ኮቪድ-19 በቤተ ሙከራው ውስጥ ወታደራዊ መተግበሪያዎች ላይ ምርምር ሲደረግ የተነሳ ወረርሽኝ በሽታ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት›› ማካተቱ አልቀረም፡፡ ዋሽንግተን ታይምስ ለአመክንዮው ማጠናከሪያ ያቀረበው ብቸኛው መከራከሪያ የእስራኤል የቀድሞው የስለላ መኮንንና የባዮሎጂ (የጅምላ ጨራሽ በሽታ) ጦርነት አዋቂ እንደሆኑ የተነገረላቸውን ዳኒ ሾሃም የተናገሩትን ነው፡፡ እኚሁ ‹‹አዋቂ›› እንዳብራራሩት ከሆነ፣ ‹‹በተቋሙ ውስጥ ያሉት በርካታ ቤተ ሙከራዎች ቫይረሱን በመፍጠርና በማስፋፋት ድርሻ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡››

በሌላ በኩልም የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ቻርለስ ሌይበር፣ ‹‹የኮሮና ቫይረስን በላቦራቶሪ ውስጥ በመፈብረክ ሸጠዋል ተብለው እንደታሰሩም›› በወሬ ደረጃ መነገሩ በእርግጥም ከቫይረሱ ይበልጥ በፍጥነት የተዛመተው የሴራ ንድፈ ሐሳብ ትንታኔ፣ የአገሮች በተለይም የቻይናና የዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ እሰጥ አገባና ፕሮፓጋንዳ ማትረፊያ እንደሆነ ክቡድ ማሳያ ተደርጎ ቀረበ፡፡ ቆየት ብሎ ደግሞ ወሬው ሐሰተኛ መረጃ ስለመሆኑ በሬውተርስ ዜና አገልግሎት ተነቧል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህና መሰል የሴራ ንድፈ ሐሳብ ትንታኔዎችን ጎዶሎ የሚያደርጓቸው ጥያቄዎችን ማንሳት ይገባል፡፡ ለመሆኑ ቫይረሱ ቻይና ውስጥ ተሠራ ቢባል እንኳን፣ መልሶ ቻይናን የሚጎዳ ቫይረስ እንዴት በቻይና ቤተ ሙከራ ውስጥ ሊሠራ ይችላል? ማንን ጎድቶስ ማንን ለመጥቀም የተሸረበ ሴራና የጅምላ ጨራሽ በሽታ ይሆን? ተብሎ በአንክሮ ቢታሰብበት አጥጋቢና አርኪ ምላሽ ማግኘት እንደሚከብድ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ቫይረሱ አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራ ተሠራ ቢባልስ ለምን እዚያው ቀድሞ አልተከሰተም? አሜሪካስ የገዛ ዜጎቿን የሚጨርስ ቫይረስን በማምረት ምን የምታገኘው አንዳች ጉልህ ጥቅም አለ? የሚሉት ወሬውን የሚፈበርኩትን ጨምሮ እስካሁን የሚያብራራ አልተገኘም፡፡ ለዚያም ይመስላል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የሴራ ትንታኔዎች በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክሙና ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ናቸው ብለው መናገራቸው፡፡ ድርጅታቸው ከበሽታው እኩል አግባብነት የሌላቸውና ሴራ የተሞላባቸውን አሳሳች መረጃዎችን አብረን እየተዋጋ እንደሆነ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡

በቻይና ሆንግ ኮንግና ቼንግዱ ግዛቶች ውስጥ የተነዛው ፕሮፓጋንዳ ደግሞ፣ ይበልጡን ግራ አጋቢና ዓይን ያወጣ ነው፡፡ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ሐሙስ ሚያዝያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.  ምሽት ባሠራጨው ዘገባ መሠረት፣ አፍሪካውያን በታዩባቸው የግዛቶቹ አካባቢዎች ውስጥ ‹‹ቫይረሱ ከአፍሪካ ነው የመጣው፣ ከቻይና አይደለም›› በማለት አፍሪካውያንን የማግለልና እነሱን ሲያዩ የመረበሽ ችግር ውስጥ እየገቡ ናቸው፡፡

በዘገባው መሠረትም የቫይረሱ መነሻ እንደሆነች በተነገረላት ውሃን ግዛት በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ይማር የነበረ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ከግዛቲቱ እንደመጣ በመታወቁ ብቻ፣ በሌላ አካባቢ ምን ያህል መገለል እንደ ደረሰበትና አሁን በሌላ ከተማ ዩኒቨርሲቲ በሚማር ወዳጁ አማካይነት ያለ ዩኒቨርሲቲው ይሁንታ መኝታ ቤት ተጋርቶና እዚያው ውሎ ለማደር እንደተገደደም ራሱ ተማሪው ተናግሯል፡፡

ስለኮሮና ቫይረስ መከላከያ መላዎች የተነገሩ መድኃኒቶችም አስገራሚና ብዙዎች ሲደለሉባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ከዚህም ውስጥ ለአብነት በአገራችን ውስጥ ‹‹ከገዳም አባቶች የቫይረሱ መከላከያ እንዲሆን የተነገረ ነው፤›› ተብሎ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር አማካይነት ብዙዎች የተቀባበሉት መረጃ ከሐሰተኛና በሳይንስ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ውስጥ ይመደባል፡፡ ያ ሲባል ግን ባህላዊ ሕክምናና ሃይማኖታዊ የፈውስ መንገዶች አያስፈልጉም በሚል ስሁት አረዳድ ተደርጎ እንዳይወሰድ ጸሐፊው አበክሮ ያሳስባል፡፡

የኮቪድ-19ን መስፋፋት ተከትሎም በአንዳንድ ሥፍራዎች ‹‹ሐሰተኛ ነቢያት›› ችግር ፈጣሪዎች ሆነው እንደነበርም ሲነገር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ብዬ ነበር፣ አስቀድሜ ተናግሬ ነበር በማለት በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች እንደ አሸን የበዙበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከልም በዘመኑ የተነሱና ሳይሆኑ ራሳቸውን ‹‹ነቢያት›› በማለት የሚጠሩቱ፣ ቅድሚያውን ይወስዳሉ ብንል እብለት አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው እነዚሁ ‹‹ነቢያት›› ለአብነትም የአገራችን የቅርብ ጊዜ ኹነቶች ውስጥ ብንመለከት እንኳን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደሚሞቱና ምክትላቸው ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን እንደሚይዙ፣ አስቀድመን በራዕይ ዓይተን ነበር ሲሉ መናገራቸውን አንዳንድ ሚዲያዎች ከትበውት ተነቧል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄን ለማንሳት መገደዳችን አይቀርም፡፡ ለመሆኑ ትንቢት አስቀድሞ ታይቶ ነበር ከተባለ ለምን ቀድሞ አይነገርም? መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ቅዱስ ቁርዓንን መሠረት አድርጎ መነጋገር ቢያስፈልግ እንኳን፣ ነቢያቱ ትንቢት የሚናገሩለት ዓብይ ክስተት ከሺሕ ዓመታት አስቀድሞ የተነገረና በጽሑፍም የሰፈረ ሆኖ ሊገኝ የሚችልባቸው ዕድሎች አሉ፡፡ እንደ ነቢይ ሼሕ ሁሴን ጅብሪል ያሉ ነቢያትም ትንቢታቸውን የተናገሩት፣ ይከሰታሉ ያሏቸው ኹነቶች ከመሆናቸው ዓመታት በፊት መሆኑ በገሃድ ይታወቃል፡፡ ታዲያ የአሁኑን ዘመን ከየትኛው መሠረት ተነስተን ነው ትንቢት ብለው በድፍረት የምንናገረው? ትንቢት በራሱ ትንቢት ለመባልና ራዕይ ዓይቼ ነበር ለማለት ድርጊቱ ከመደረጉ ዓመታት ወይም ወራት አስቀድሞ መነገርና መታወጅ፣ ወይም በይፋ መለፈፍ የለበትም ወይ? የሚለው ነጥብ በትክክል ሊመለስ ግድ ይላል፡፡

እነዚሁ ነቢያት ‹‹ፈጣሪ የናጠጠ ሀብታም እንደምትሆን/እንደምትሆኚ ነግሮኛል፤››፣ ‹‹ስለአንተ/አንቺ ራዕይ አሳይቶኛል፤››፣ ‹‹ባለቤትና ባለፀጋ ትሆናላችሁ››፣ ወዘተ. ሌሎችንም ማረጋገጫ የማይቀርብባቸውን ትንቢቶች በመናገር የብዙዎችን ሕይወት አመሰቃቅለዋል፡፡ የሌላን ሰው ንብረት በማናለብኝነት አስነጥቀዋል፡፡ ሀብት እናበዛላችኋለን ብለው የሰዎችን ንብረት ወስዶ እስከ መሰወር የደረሱ ሐሰተኛ መነኮሳትና ራሳቸውን ‹‹የሃይማኖት አባቶች›› ነን የሚሉ ሰዎች መበራከታቸው መሬት የረገጠ ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት የመንፈስ ውጥረት ውስጥ ገብተው ሳሉ፣ አንዳንድ ሐሰተኛ ነቢያት ግን ‹‹ቫይረሱን በእጃችን ይዘን አፈራረስነው›› ዓይነት ቧልት መሰል ንግርታቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሠራጩ መታየታቸው አስገራሚም አስደንጋጭም ሆኖ ከርሟል፡፡ ይኸው ክስተት ግን ራሳቸው ሰዎቹን እንጂ ሃይማኖቶችን እንደሚወክል ተደርጎ መቅረብ አይገባውም፡፡

በአፍሪካም፣ ‹‹አፍሪካውያን ላይ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ሊሞከርባቸው ነው፤››፣ ‹‹ጥቁር ሻይ መጠጣት በሽታውን ይከላከላል፤››፣ ‹‹ወንዶች ቫይረሱን ለመከላከል ፂማቸውን ሙልጭ አድርገው ይላጩ፤›› የሚሉ አሳሳች መረጃዎች የበሽታውን መከላከል ፈተና ውስጥ ጥለውት እንደነበርም በስፋት ሲነገር ሰንብቷል፡፡ በኢራን ‹‹ኮሮናን ይከላከላል›› ተብሎ በተነገረ ሐሰተኛ መረጃ ደረቅ የቁስል አልኮል (ሜታኖል) በመጠጣታቸው፣ ከ600 የሚበልጡ ኢራናውያን እንደሞቱ ታንሲም የተባለው የአገሪቱ የዜና ኤጀንሲ የዘገባ ሽፋን ሰጥቶት ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረስ አዲስና ከዚህ ቀደም ሲል ዓለም ከገጠሟት ወረርሽኞች የተለየና በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ለአብነትም ቫይረሱ ገና በርካታ ያልታወቁና ተለዋዋጭ ፀባያት ያሉት መሆኑ፣ አዲስ በተደረገ ጥናትም በበሽታው የተያዘ ሰው ምልክት ሳያሳይ እስከ 25 ቀናት ድረስ የሚቆይ መሆኑ መታወቁ፣ ለከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀትና መረበሽ የሚያጋልጥ መሆኑም ይበልጡኑ አሳሳቢነቱ እንዲንር አድርጎታል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል ዓይነተኛው መንገድ ከቤት አለመውጣት ነው ቢባልም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገሮች ከእጅ ወደ አፍ በሆነና የዕለት ገቢውን በማግኘት ኑሮውን የሚገፋ ሕዝብ ባለባቸው አገሮች፣ አዋጭነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑ አንድ እውነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችም የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት የሚኳትኑ መሆናቸው፣ በአንድ በኩል መንግሥት ለእያንዳንዳቸው ምግብና መሠረታዊ ፍላጎት ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የማዳረስ ሙሉ አቅም ላይ አለመገኘቱ፣ በሌላ በኩል አዲስ አበባንም ሆነ አገሪቱን ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት ከበሽታው  ለማገገም ያለውን አማራጭ የሚመከር እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ መንግሥት ባስታወቀው መረጃም እስከ ዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን ረፋድ ድረስ በበሽታው የተያዙት ዜጎች 56 መሆናቸውም ያነሳነውን ዕርምጃ ለመውሰድ፣ ጉዳዩን አጣዳፊ እንደማያደርገው እንደ ማስተማመኛም ሊቀርብ ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ረቡዕ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥታቸው ቫይረሱን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ እንዳወጀ፣ የበሽታውን ቁጥጥር ለመግታትም የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሊወስድና ክልከላዎችን ገቢራዊ ሊያደርግ እንደሚችል ፍንጭ ቢሰጡም፣ የአዋጁ ዝርዝር ክልከላዎች ግን ይኼ ጽሑፍ ለኅትመት እስከተዘጋጀበት ወቅት ድረስ ይፋ አልተደረጉም፡፡ እስካሁን ማወቅ የተቻለው ሀቅ ቢኖር የሚወጡትን ድንጋጌዎች ትዕዛዛት የሚጥስ ከተገኘ የሦስት ዓመታት እስራትን ጨምሮ፣ ከአንድ ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት የተገለጸውን ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...