Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ አደረገ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ተፅዕኖ በመመልከት ለባንኩ ደንበኞች የወለድ ምጣኔና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ላይ ማሻሻያዎች እንዳደረገ አስታወቀ፡፡

ባንኩ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ የኮሮና ቫይረስ በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በንግድ እንቅስቃሴና በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ያግዛሉ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያስቀመጣቸውን ለውጦች ይፋ አድርጓል፡፡ ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ በደንበኞቹ ላይ የበለጠ እንዳይጎላ ለመቀነስና ሸክማቸውን ለመካፈል፣ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ብሎም የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብታዊ ሚዛን አስጠብቆ ለማስኬድ በማሰብ፣ ባንኩ የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ ካደረገባቸው መካከል የብድር ወለድ ቅናሽ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ማሻሻያ መሠረት በሁሉም የቢዝነስ ዘርፍ ላይ ከ0.25 በመቶ እስከ 3.45 በመቶ የሚደርስ ጊዜያዊ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ አድርጓል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኰንን እንዳስታወቁት፣ ቀደም ሲል የወሰዱትን ብድር ከሚጠበቅባቸው  የአከፋፈል ሥርዓትና የመክፈያ ጊዜ ቀድመው በሚከፍሉ ደንበኞች ላይ ይጣል የነበረው ቅጣት (Commitment Fee) እንዲነሳ ተወስኗል፡፡ በብድር ወለድ ቅናሹ ላይ የ3.45 በመቶ ከፍተኛ የወለድ ቅናሽ የተደረገባቸው የአበባ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ናቸው፡፡

በወረርሽኙ አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ብድራቸውን በተቀመጠላቸው የአከፋፈል ሥርዓት መክፈል ለተቸገሩ ደንበኞችም የዕፎይታ ወይም የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እየሰጠ እንደሚገኝ የገለጸው ባንኩ፣ ከብድር መክፈያ ጊዜ ማሻሻያና ማራዘሚያ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ያስከፍል የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ በጊዜያዊነት እንዳነሳ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡  

የቫይረሱ መስፋፋት የዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ላይ ባስከተለው መስተጓጎል ያመጣው መዘዝ አስመጪዎች ላይ ጫና አሳድሯል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አስመጪዎች ለደረሰባቸው የባንክ መተማመኛ ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት ማራዘሚያ የአገልግሎት ክፍያ ወይም ኮሚሽን ቀደሞ የነበረውን 3.55 በመቶ ክፍያ ወደ 2.62 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

አካላዊ መራራቅን በማበረታታት ለኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ቁጥጥር በጎ አስተዋጽኦ ለማጎልበትና ማኅበረሰቡን ከዘመናዊ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር ለማቀራረብ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ከአገልግሎት ክፍያ ነፃ መደረጉን ባንኩ አስታውሷል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአዲስ አበባ ሕዝብ በብዛት በሚዘዋወርባቸው አራት ዋና ዋና አደባባዮች ላይ ባለ 1,000 ሊትር የውኃ ታንከሮችን በማስቀመጥ እጅ ለማስታጠብ ከሚያገለግሉ የንፅህና መጠበቂያ ፈሳሽ ሳሙናዎች ጋር ማቅረቡን የገለጸው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ብሔራዊ እንቅስቃሴ የድጋፍ ጥሪ በመደገፍ ለብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አምስት ሚሊዮን ብር መለገሱን ባንኩ ጠቅሷል፡፡  

እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎችን መውሰዱ በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ቢያሳጣውም፣ ማሻሻያዎቹ በጊዜያዊነት የተደረጉት የንግድ ሥራዎች ወደ ነበሩበት መደበኛ ሁኔታ እስኪመለሱ ድረስ መጠነኛ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ አቶ ተፈሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን የብድር ወለድ ለውጣችን እስከ 3.45 በመቶ ድረስ በመሆኑ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ነገር ግን እኛም፣ የንግድ ማኅበረሰቡም ላይ ጫናው እኩል ያረፈብን በመሆኑ፣ መደጋገፍ አለብን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በሌላ በኩል ግን የባንኩ ባለአክሲዮኖች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ከዓመት ዓመት ከባንኩ የሚከፈላቸውን የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ክፍፍል ጠብቀው የሚኖሩ በርካታ ባለአክሲዮኖች ስላሉ ለእነሱም መጠንቀቅ ስለሚያስፈልገው ሁኔታዎች ወደ መስመር ሲመለሱ የሚያሻሽላቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

‹‹ለማንኛውም ይኼ ክፉ ቀን ይለፍልን፡፡ ገንዘብና ሌላው ቁሳዊ ነገር በኋላ ይገኛል፡፡ ዋናው ነገር የሰዎች ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ማንነት ሳይጎዳ አደጋውን ከተሻገርን እንደገና እንነሳለን፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

በወረርሽኑ በንግድ እንቅስቃሴውና በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ስለሚታየው ተፅዕኖ እንዲያብራሩ በተጠየቁ ጊዜም በዓለም ላይ እንዲተገበር የሚቀርበው የጥንቃቄ መርህ ቤት ዋሉ፣ ከቤት አትውጡ የሚል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ቤት ዋሉ ከተባለ ቤት ለመዋል የምንቸገረው ቁጥር አንድ እኛ ነን፤›› በማለት የፋይናንስ ዘርፉን የሚፈትን አጣብቂኝ ሁኔታ መከሰቱን አቶ ተፈሪ አውስተው፣ ‹‹የገንዘብ ዝውውር ከቆመ ሰው ይሞታል፡፡ ባንክም የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ነው፡፡ ግብይት ካለ ባንክ መኖር አለበት፤›› በማለት በሽታው የህልውና ፈተና መጋረጡን አመላክተዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ገርበብ አድርገን ከፍተን፣ ዲጂታል ባንኪንግን ተጠቅመንም ቢሆን አገልግሎት መስጠት ግድ ነው፤››  ብለዋል፡፡

‹‹ኢኮኖሚያችን ባይሰምጥም ባለበት ሊቆም ይችላል፡፡ ምክንያቱም ዓለም በሩን ዘግቶ እሳት በማጥፋት ላይ ነው፡፡ የምንልካቸው ውስን የወጪ ንግድ ምርቶችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንኳ ቢኖር አገሮች በራቸውን ስለዘጉ ምርቶቹ እየተላኩ አይደሉም፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችም ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የንግድ አውታሩ ተጎድቷል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ችግር የአቅርቦና የፍላጎት አለመጣጣምን ፈጥሯል፤›› በማለት በሽታው ያስከተለውን ጫና አብራርተዋል፡፡ ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ግሽበት ምክንያት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ እውነታ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ሊፈጠር ይችላል ብለው ከጠቀሱት ውስጥ፣ የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መቀነስ አንዱ ነው፡፡ ይህ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል ሲያብራሩም፣  እሴት የሚጨምረው የንግዱ ማኅበረሰብ በአብዛኛው ከምርትና ከአቅርቦት ሰንሰለት እየወጣ ቤት ለመዋል እየተገደደ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ግን ፍጆታ እየጨመረ ስለሚሄድ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ልዩነቱ እየሰፋ ምርትና አቅርቦቱ እያነሰ ፍላጎት እየጨመረ እንደሚሄድ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ድጋፍ በሚያደርግባቸው ምርቶች ላይም ቢሆን የብድር ፍላጎት እየቀነሰ እንደመጣ አቶ ተፈሪ ይጠቅሳሉ፡፡ ብድር ይጨምራል የሚል ምልከታ ቢኖርም ፕሬዚዳንቱ አይስማሙበትም፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ‹‹ሥራ ካልተሠራ፣ ብድር አራዝሙልኝ፣ ወለድ ቀንሱልኝ በሚባልበት ወቅት ተጨማሪ ብድር የሚጠይቅ ደንበኛ ላይመጣ ይችላል የሚል መነሻ አላቸው፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ብድር ስጡኝ ብሎ ይመጣል ማለት ከባድ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የገንዘብ እጥረትና የቁጠባ መጠን መቀነሱ የብድር ፍላጎት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል ከሚሉ ሐሳቦች ጋር የማይስማሙት አቶ ተፈሪ፣ ‹‹ቀደም ብሎ የገንዘብ እጥረት ባለበት ወቅት ቢሆን ልቀበለው የምችለው ሐሳብ ነው፡፡ አሁን ግን ኢኮኖሚው እየተሽከረከረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ብድር የምከፍለው ለምድነው ይላሉ፡፡   ስለዚህ ብድር የሚጠይቅ ደንበኛ ይቀንሳል፤›› በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ባይሆን እንደ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማኮሮኒና መሰል የምግብ ሸቀጦችን በማምረት ሥራ ላይ የሚያተኩሩ ደንበኞች የብድር ጥያቄ ቢያቀርቡ ትክክል ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የወቅቱ የፍጆታ ሁኔታ ከእነዚህ የምግብ ምርቶች ጋር የተያያዘ አካሄድ እንዳለው በማብራራት ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ለፋብሪካ ግንባታ ብድር የሚጠይቅ አለያም የካፒታል ዕቃ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ ተበዳሪ፣ አንደኛ ዕቃዎቹን ማስመጣት የሚችልበት አገር ዝግ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ቀውስ ወቅት የብድር ጥያቄ የበለጠ እየቀነሰ እንደሚሄድ አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች