Friday, September 22, 2023

ፓርላማው በአገር  አቀፍ  ደረጃ  እንዲፈጸም ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይዘትና ፖለቲካዊ አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኖ የላከለትን ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተሠራጨና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ፣ በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የታወጀ ነው።

የወረርሽኙን ሥርጭት በመደበኛ የመንግሥት አሠራር ሥርዓት መከላከልና መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑ፣ ሥርጭቱን ለመግታትና ለመቀነስ መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች በተቀላጠፈና በተቀናጀ መንገድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው በመታመኑና ከቫይረሱ ሥርጭት ጋር ተያይዞ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስና ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት እንዳስፈለገ የአዋጁ መግቢያ ያስረዳል።

ፓርላማው የቀረበለትን ይኼንን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ በጠራው ስብሰባ ምክንያት አባላቱ ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ በማሰብ፣ ከመሰብሰቢያ አዳራሹ ውጪ በመውጣት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኝ ሦስት ሺሕ ተሰብሳቢዎችን ማስተናገድ በሚችል ሰፊ አዳራሽ ያካሄደ ሲሆን፣ አዋጁም ከሁለት ሦስተኛ በላይ በሆነ አብላጫ ድምፅ መፅደቁ ተገልጿል።

ይህንን አዋጅ የማፅደቅ ሒደትን እንዲከታተሉ ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለት የመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ ሲሆኑ፣ የዚህ ምክንያቱም በቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ጥንቃቄ ለማድረግ ሲባል ብቻ እንደሆነ ሪፖርተር ከፓርላማው ምላሽ አግኝቷል።

ፓርላማው ያፀደቀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ገጾች የተዘረዘሩ በስምንት አንቀጾች የተከፈሉ ድንጋጌዎችን በመያዝ አንቀጽ አንድ የአዋጁን መጠሪያ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በቀጣዩ አንቀጽ ሁለት ደግሞ ትርጓሜዎች የቀረቡበት ክፍል ነው። የአዋጁ ዋና ይዘት ከአንቀጽ ሦስት እስከ ስምንት ባሉት ክፍሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከታች ባለው መልኩ ቀርቧል።

የአዋጁ ዋና ይዘቶች

 – አንቀጽ 3 – የተፈጻሚነት ወሰን

  1. ይህ አዋጅ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ ይሆናል።
  2. ይህ አዋጅና በዚህ በአዋጅ መሠረት የሚወጡ ደንቦች በኢትዮጵያውያንም ሆነ በአገሪቱ በሚኖሩ ወይም በሚያልፉ የውጭ ዜጎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ።
  3. ከዚህ አዋጅና በአዋጁ መሠረት ከሚወጡ ደንቦች ጋር የሚቃረን ማንኛውም የፌደራልም ሆነ የክልል ሕግ፣ አሠራር ወይም ውሳኔ ይህ አዋጅ ፀንቶ በሚቆይበት ወቅት ተፈጻሚነት አይኖረውም።

አንቀጽ 4 – የመብት ዕገዳዎችና ዕርምጃዎች

  1. የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወረርሽኙ ሥርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስና ለመከላከል የመብት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሀ) እና (ለ) መሠረት ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚያወጣቸው ደንቦች ይደነግጋል።
  2. የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች፣ በማንኛውም ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸውን ድንጋጌዎች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም።

አንቀጽ 5 – አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነት

  1. የመብት ዕገዳዎቹና ዕርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል።
  2. ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ መሠረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባላቸው አካላት የሚሠጥ ሕጋዊ ትዕዛዝና መመርያ የመፈጸም ግዴታ አለበት።
  3. የፌደራልና የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማትና ሌሎች በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ይፋ የተደረጉ የመብት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን ያስፈጽማሉ።

አንቀጽ 6 – የወንጀል ተጠያቂነት

  1. በወንጀል ሕግ የተካተቱ አግባብነት ያላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በዚህ አዋጅ መሠረት የተደነገጉ የመብት ዕገዳዎችን፣ ዕርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመርያ ወይም ትዕዛዝን የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺሕ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።
  2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ(1) የማስፈጸም ኃላፊነት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በፌደራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚሰጥ ውክልና መሠረት የክልል ዓቃቤ ሕጎች ወይም አቻ ተቋማት ነው።

አንቀጽ 7 – ማሳወቅ

  1. በዚህ አዋጅ መሠረት የሚደነገጉ የመብት ዕገዳዎችና ዕርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በስፋት ለሕዝብ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ይገለጻሉ።
  2. ሁሉም አካባቢያዊ፣ ክልላዊም ሆነ አገር አቀፍ የሥርጭት አድማስ ያላቸው የግል፣ የመንግሥት ወይም የማኅበረሰብ የመገናኛ ብዙኃን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 7(1) መሠረት የሚሰጡ ገለጻዎችን፣ ተያያዥ ማብራሪያዎችንና መልዕክቶችን ያለ ምንም ክፍያ የሚዲያ ተቋሙ በሚሠራበት ቋንቋ ሁሉ ብሮድካስት የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

አንቀጽ 8 – አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

  1. አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል።

የአዋጁ ፖለቲካዊ አንድምታና የክልሎች መብት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመብት ዕገዳዎችን የሚጥል ቢሆንም፣ የመብት ዕገዳ እንደሚጣል የሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽ አራት ግን የሚጣሉትን የመብት ዕገዳዎች፣ ወይም የሚወስዱትን ዕርምጃዎች ሳይዘረዝር ይኼንን የማድረግ ሥልጣንን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እንዲታወጅ ውክልና ይሰጣል።

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የዚህን ድንጋጌ ተገቢነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና የፖለቲካ መብቶች የሚገድብ በመሆኑ ለአዋጁ መታወጅ አስፈላጊነት ያላቸውን የመብት ክልከላዎች ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት በሚቆጣጠረውና ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ለተሰጠው ፓርላማ ብቻ መተው እንዳለበት ይሞግታሉ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማው ጥብቅ ክትትል ውስጥ መተግበር እንዳለበት የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ ሕገ መንግሥቱም አንድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ አዋጁን የሚያስተገብረው አስፈጻሚው መንግሥት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጽም ከአዋጁ መፅደቅ ጎን ለጎን ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተል መርማሪ ቦርድ እንዲቋቋም አስገዳጅ ድንጋጌ ያስቀመጠው፣ አስፈጻሚው መንግሥት አዋጁን ተገን አድርጎ በዜጎች ላይ በደል እንዳያደርስ መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎች ውስጥ ምንም ዓይነት ገደብ ሳይጣል፣ ነገር ግን ገደብ እንደሚጣል ደንግጎ የሚጣሉትን ገደቦች አስፈጻሚው መንግሥት እንዲያወጣ በውክልና ሥልጣን መስጠት፣ በሥራ አስፈጻሚው መንግሥትና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መካከል ምንጊዜም ታሳቢ የሚደረገውን ዝምድና አለመረዳት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያረቀቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከረቂቅ ሰነዱ ጋር አባሪ አድርጎ የላከው ማብራሪያ በበኩሉ የሚጣሉት ገደቦች ምን እንደሆኑ ሳይገለጽ፣ ጥቅል ድንጋጌ የተቀመጠበትን ምክንያት ያስረዳል። ኮቪድ 19 ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባለፈ የሚከሰቱ የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገልጸው ማብራሪያው፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከሚወሰዱ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ባለፈ እነዚህን ተጓዳኝ ተግዳሮቶች ለመወጣት፣ መንግሥት ከወትሮው የላቀ ሥልጣንና ሕጋዊ አቅም እንዲኖረው ማድረግ የዚህ አዋጅ አንዱ ዓላማ እንደሆነ ይገልጻል።

በመሆኑም ሊያጋጥም የሚችልን የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ፣ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስና ማኅበራዊ ውጥንቅጥ ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ እንዲህ ያለ ችግር ካጋጠመም ከተለመደው አካሄድ ወጣ ባለ መንገድ ተጨማሪ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነና ይህን ለማድረግ አስቻይ የሆነ የሕግ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ያስረዳል።

‹‹እነዚህን የመብት ገደቦችና ዕርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው፣ አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦችና ዕርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜና በአገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው። እንደ ወረርሽኙ ሥርጭት የስፋት አድማስ፣ እንደሚያስከትለው ጉዳት አስፈላጊ የሆኑት ገደቦችና ዕርምጃዎች ሊለዋወጡ ይችላሉ። አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልጉት ክልከላዎችና መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች ተለዋዋጭነት ሊኖራቸው ስለሚችል፣ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ በመገምገምና ስለቫይረሱ ሥርጭትም ሆነ ባህሪ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን፣ የሕዝብ ጤና ባለሙያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት የመብት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስልፈጋል። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝርዝርና ቋሚ የመብት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ፣ እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ (Flexible) በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን እንዲደነግግ ሥልጣን የተሰጠበት ምክንያትም ይኸው ነው፤›› ሲል ያስረዳል።

ሆኖም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠው የመብት ዕገዳዎችንና ዕርምጃዎችን የመደንገግ ሥልጣን ገደብ የለሽ የሆነ ሥልጣን እንዳልሆነ የሚገልጸው ማብራሪያው፣ የሚጣሉት ገደቦች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ላይ በየትኛውም ወቅት ጥበቃ የሚደረግላቸው እንደሆኑ ተዘርዝረው የተቀመጡትን መብቶች እንደማይነካ ያክላል።

እነዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓውድ ውስጥ እንኳን ቢሆን ሊታገዱ የማይችሉ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች የሚባሉት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 1 የተቀመጠው የመንግሥት ስያሜ፣ በአንቀጽ 18 የተቀመጠው የኢሰብዓዊ አያያዝ መከልከል፣ በአንቀጽ 25 የተቀመጠው የእኩልነት መብትና በአንቀጽ 39 (1) እና (2) የተካተተው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብቶች ናቸው።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ የተፈጻሚነት ወሰኑ ሲሆን፣ አንዳንድ ክልሎች በተለይም የትግራይ ክልል የቫይረሱ ሥርጭትና ተጓዳኝ ጉዳዮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአስተዳደር ክልሉ ውስጥ የሚፈጸም የራሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ፣ በፌዴራል መንግሥት የታወጀውም ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውልና ተፈጻሚነቱም በመላ አገሪቱ መሆኑ፣ ከሁለቱ አዋጆች ቀዳሚ የተፈጻሚነት የሚኖረው የቱ ነው የሚል ክርክር አስነስቷል። ይህንንም በተመለከተ የአዋጁ አባሪ ሰነድ ማብራሪያ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (1) (ለ) ላይ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣል መብት እንዳላቸው በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ይህ ድንጋጌ ታሳቢ የሚያደርገው አገር አቀፍ ያልሆኑ፣ በተለይም በአንድ ክልል ውስጥ የተፈጥሮ አደጋ ወይም የሕዝብ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሆነ ያስረዳል።

ነገር ግን ኮቪድ 19 ከአገር አቀፍ አልፎ ዓለም አቀፍ ወረርሽን በመሆኑ እንደ አገር የተቀናጀና የተሳለጠ የመከላከል፣ የመቆጣጠር ዕርምጃዎችን ለመውሰድ በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሠረት አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተገቢ እንዳደረገው ይገልጻል።

በመሆኑም ማንኛውም ሰው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሰጥ ሕጋዊ ትዕዛዝና መመርያ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት፣ ከዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕጎች፣ መመርያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ያስረዳል።

ፓርላማው የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካፀደቀ በኋላ፣ የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል ሰባት አባላት የያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን ሰይሟል። በዚህም መሠረት የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት የምክር ቤቱ አባል አቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበት ሲሆኑ፣ ሌላኛው የምክር ቤቱ አባልና የሰላምና የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመዋል። የመርማሪ ቦርዱ አባል ሆነው የተሰየሙት ሌሎቹ የምክር ቤት አባላት ወ/ሮ ፋንታዬ ወንድሙ፣ አቶ ሽኩሪ ማዕለ፣ ብሩክ ላጵሶ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ሞሚና መሐመድና አቶ በሻዳ ገመቹ ናቸው።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -