Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ተርሚናል የአፍሪካ ዕርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል እንዲሆን መረጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በአፍሪካ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የአፍሪካ ዕርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል እንዲሆን መረጠ፡፡

የተመድ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት አፍሪካ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ የሚቀርቡትን የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ለአፍሪካ አገሮች ለማከፋፈል፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ተርሚናል በማዕከልነት እንደተመረጠ አስታውቀዋል፡፡ ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ተርሚናል ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት ዘመናዊ አውሮፕላኖችና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል ለአፍሪካ የሚመጡ የሕክምና ቁሳቀሶችን ለማከፋፈል ብቁ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ስቲቨን ኦማሞ እንደተናሩት፣ አዲስ አበባ የሕክምና መሣሪያዎችን ማከፋፈያ ማዕከል ሆና የተረመጠችው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጭነት የማስተናገድ አቅም በመገምገምና የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየው ፈቃደኝነትና መልካም አቀባበል ታይቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ አገሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት አማካይነት የሚላኩትን የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችን፣ ለአፍሪካ አገሮች እንደሚያከፋፍል ሚስተር ኦማሞ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕክምና መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ማጓጓዝ እንደሚችል አረጋግጠናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ላሳየው ፈቃደኝነት እናመሠግናለን፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ሚስተር ቦሬማ ሳምቦ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት  በርካታ የአፍሪካ አገሮች በሮቻቸውን በመዝጋታቸው ምክንያት፣ የሕክምና መሣሪያዎች ማጓጓዝ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ ሕይወት አድን የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች ማከፋፈያ ኮሪደር ሆና በመመረጧ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከጃክማ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ አገሮች የተለገሱትን የሕክምና ዕቃዎች አየር መንገዱ ያከፋፈለበትን ፍጥነት ተመልክተናል፡፡ አሁንም የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጣ እርግጠኞች ነን፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍፁም አባዲ የተመድ ኃላፊዎች የሌሎች አፍሪካ አገሮች ኤርፖርቶችና አየር መንገዶች መጎብኘታቸውን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ማዕከል ባሉት ዘመናዊ የጭነት አውሮፕላኖችና ለሕክምና መሣሪያዎችና ለመድኃኒቶች ማቆያ ምቹ የሆኑ መጋዘኖች ተመራጭ ሊሆን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ገና በዝግጅት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በሥራ ላይ ያለ ዘመናዊ የካርጎ መሠረተ ልማት ያለው እንደሆነ በመመልከታቸው የማከፋፈያ ማዕከል አድርገው መርጠውታል፤›› ያሉት አቶ ፍፁም፣ ከጃክማ ፋውንዴሽን የተለገሱትን 100,000 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የሕክምና መሣሪያዎች በስድስት ቀናት ለ51 አገሮች በማከፋፈል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ያለውን ብቃት ማስመስከሩን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጃክማ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ አገሮች በሁለተኛ ዙር የተላኩ የሕክምና መሣሪያዎችና ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኙ 160,000 ኪሎ ግራም የሕክምና ቁሳቁሶችንና መድኃኒቶችን ከሚያዝያ 6 ቀን ጀምሮ ለ54 የአፍሪካ አገሮች ማከፋፈል እንደጀመረ ታውቋል፡፡ ኤርትራ ከዚህ ቀደም የተላከላትን አልቀበልም በማለቷ፣ ድርሻዋ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አሥር ቦይንግ 777 እያንዳንዳቸው 105 ቶን ጭነት ማንሳት የሚችሉ አውሮፕላኖች፣ እንዲሁም ሁለት ቦይንግ 737-200 እያንዳንዳቸው 22 ቶን ጭነት ማንሳት የሚችሉ አውሮፕላኖች አሉት፡፡

የካርጎ ተርሚናሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሥጋ፣ መድኃኒትና ደረቅ ጭነትን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ምክትል ዳይሬክተር  አህመድ ኡማ (ዶ/ር) ይህ የነፍስ አድን ትብብር ከኮቪድ-19 ባለፈ መዝለቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹ከኮቪዲ-19 በኋላም ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ይህ የነፍስ አድን ትብብር መቀጠል አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ የተመድን የዕርዳታ ጭነቶች በማጓጓዝ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊያገኝ እንደሚችል ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች