በሰለሞን ይመር
ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የበረሃ አንበጣ መንጋ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት በተለያዩ ክልሎች አንድ ሚሊዮን ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውንና አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ይህንን መረጃ ይፋ ያደረገው በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመለየት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደን የዳሰሳ ጥናት መሠረት አድርጎ መሆኑን በማስታወቅ ነው፡፡ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 390 ሺሕ በሶማሌ፣ 360 ሺሕ በኦሮሚያና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ 100 ሺሕ በአፋር፣ 72 ሺሕ በአማራ፣ 43 ሺሕ በትግራይ፣ እንዲሁም 13 ሺሕ ደግሞ በደቡብ ክልል እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ፋኦ፣ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዩ ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉበት ይህ ጥናት የበረሃ አንበጣ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የበረሃ አንበጣው በአካባቢዎቹ በሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትና ላይ ያደረሰውን ጫና በመለየት የጉዳቱን ዝርዝር አስታውቋል፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ ቀደም ባሉት ወራት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ወደ 200 ሺሕ ሔክታር የሚጠጋ የእርሻ ቦታ ላይ ጉዳት ሲያደርስ፣ ከ356 ሜትሪክ ቶን በላይ እህል እንዳወደመ ታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሰብል ውድመት ከደረሰባቸው ክልሎች አንዱ በመሆኑ 123 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል በአንበጣ መንጋ ጉዳት ሲደርስበት፣ በሶማሌ ክልል 100 ሺሕ፣ በትግራይ 84 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆን ሰብል በአንበጣ መንጋው መውደሙ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የአንበጣ መንጋው 1.3 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ የግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡ በሶማሌ ክልል 61 በመቶ፣ በአፋር 59 በመቶ፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በደቡብ ክልል 35 በመቶ፣ በኦሮሚያ 31 ከመቶ የሚሆን የእንስሳት ግጦሽ መቀነስ እንዳጋጠመ የዳሰሳ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ የአንበጣ መንጋው በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ በሚኖሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ በጥናቱ ሰፍሯል፡፡
አገር አቀፍ የአንበጣ መንጋ ቅድመ ትንበያና ቁጥጥር ሥርዓት በማበጀትና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን በማጎልበት፣ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መከላከል የሚቻልበት መንገድ መከተል እንደሚገባ ጥናቱ ያሳስባል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል፣ አስቀድሞ መከላከል ካልተቻለ በቀጣናው አገሮች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያስከትል ፋኦ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ምንም አንኳን ቀደም ሲል የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ የነበረው ሥርጭት መቀነስ ያሳየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከወራት በፊት ተከስቶ ከነበረው በ20 እጥፍ የሚበልጥና ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም ተብሏል፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እንደተከሰተና በመስፋፋት ላይ እንደሆነ ፋኦ ከቀናት በፊት አስታውቋል፡፡