Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኮሮና ምክንያት በመንግሥት ሲደገፉ የነበሩ የተረጂዎች ቁጥር ወደ 30 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ...

በኮሮና ምክንያት በመንግሥት ሲደገፉ የነበሩ የተረጂዎች ቁጥር ወደ 30 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ ይፋ ተደረገ

ቀን:

የዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚ የዕድገት ትንበያ ወደ ስድስት በመቶ ዝቅ ብሏል

ከ700 ሺሕ በላይ ሥራዎች ሊታጡ እንደሚችሉና ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ከአነስተኛ ሥራዎቻቸው ውጪ እንደሚሆኑ ተገምቷል

ግብርና በዚህ ዓመት ከጉዳት ነፃ መሆኑ ተገልጿል

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በምግብ ለሥራና በገንዘብ የሚደገፉትን ጨምሮ በመንግሥት ዕርዳታ ይቀርብላቸው የነበሩ 15 ሚሊዮን ዜጎች፣ አሁን በወረርሽኙ ሥጋት ምክንያት የኑሮ ሁኔታቸው ተገላጭ ለሆኑ ተጨማሪ 15 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ይፋ ተደረገ፡፡ በጠቅላላው የምግብ ድጋፍ የሚያስልጋቸው ዜጎች 30 ሚሊዮን ደረሱ፡፡ የፕላንና ልማት ኮሚሽን እያካሄደ ባለው ጥናት መሠረት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖዎችንና መወሰድ ያለባቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎችን መነሻ በማድረግ እየተወሰዱ ከሚገኙት መካከል የድጎማና የዕለት ደራሽ የምግብ አቅርቦት ይጠቀሳል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በተለይ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት፣ የወረርሽኙ ተፅዕኖ በጤና ሥርዓቱ ላይ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ጫና በተጨማሪ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካቾች ላይ ማለትም በሥራ ሥምሪት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በክፍያ ሚዛንና በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ የውጭ ሐዋላ ገቢን በመቀነስና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲቀንስ በማስገደድ ከሚያደርሰው ጫና በመነሳት፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲቀንስ የማድረግ አቅም እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት መደበኛ ባልሆነው የሥራ መስክ የተሰማሩና ወደ ድህነት በቀላሉ ሊንሸራተቱ የሚችሉ ዜጎችን ጨምሮ፣ በከተማ ሴፍቲኔት ታቅፈው የሚደገፉ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች፣ እንዲሁም ከሥራ ገበታቸው ሊቀነሱ የሚችሉ በጉልበት ሥራ የተሰማሩና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ቢያንስ በምግብ እንዳይጎዱ ለመደገፍ ተጨማሪ በጀት መመደቡን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮችም በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንዲሁም ለመጠባበቂያነት ከተቀመጠው የምግብ ክምችት በተጨማሪ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ከውጭ መጠየቁን ኮሚሽነሯ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆነው እየገባ እንደሚገኝ፣ በጠቅላላው 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች የምግብ ድጋፍ የሚያገኙበት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ ከአገሪቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ እንደሚጎላ ከሚገለጹት አንዱ፣ በሥራና በሠራተኞች ሁኔታ ላይ የሚያስከትለው ጫና ተጠቃሽ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. በከተሞች የሥራና ሠራተኛ ሁኔታ ላይ በተደረገው ጥናት መሠረት፣ በከተሞች 7.5 ሚሊዮን ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተቀጥረው በሚያገኙት ደመወዝ ይተዳደራሉ፡፡ ከሥራው ዘርፍ አኳያ ሲተነተን ከ70 በመቶ በላይ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ተቀጥረው እንደሚተዳደሩ ጥናቱ ሲያመላክት፣ ከ20 በመቶ በላይ ደግሞ በኢንዱስትሪ መስክ በአብላጫውም በኮንስትራክሽን መስኩ ተሰማርተዋል፡፡

በመሆኑም ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ይረዱ ዘንድ በአስገዳጅነት እየተቀመጡ የሚገኙ የጤና አጠባበቅ መመርያዎች አብዛኞቹን የአገልግሎት ዘርፍ ሥራዎች ተፅዕኖ ውስጥ እየከተቷቸው መሆኑን ያብራሩት ኮሚሽነር ፍፁም (ዶ/ር)፣ ‹‹ኮቪድ-19›› ለመከላከል የወጡ መመርያዎች ማለትም አለመነካካት፣ ርቀትን መጠበቅና ሌሎችም ያለ ምንም ጥርጥር የአገልግሎት መስኩን ተፅዕኖ ያሳድሩበታል፤›› በማለት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎችን ጨምሮ እየገጠማቸው ያለውን የገበያ ዕጦት ማሳያ በማድረግ የችግሩን ስፋት አብራርተዋል፡፡ 

በመደበኛ የሥራ መስኮች ከተሰማሩት በተጨማሪ ሦስት ሚሊዮን ያህል ዜጎችም በርከት ባሉ በአገልግሎት፣ በአነስተኛና በጥቃቅን መስኮች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፡፡ በጠላ ንግድ፣ በጉልት ችርቻሮ፣ በፀጉር ቤት ሥራና በሌሎችም መስኮች የተሰማሩ እነዚህ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል፡፡

‹‹የኮቪድ-19 ተፅዕኖ ለሦስት ወራት ይቆያል ከሚል ዕሳቤ ብንነሳ በደመወዝ ተቀጥረው ከሚሠሩ 7.5 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ወደ 705 ሺሕ ሥራዎች አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሦስት ሚሊዮን ዜጎች የተሰማሩባቸው የሥራ መስኮችም በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳሉ፡፡ ይህ ግን ምንም ሳናደርግ ብንቆይ ነው፤›› ሲሉ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ኮሚሽነሯ አመላክተዋል፡፡

ዓመቱ ሲጀመር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2012 ዓ.ም. በዘጠኝ በመቶ ያድጋል ተብሎ ትንበያ እንደተሠራ አስረድተው፣ ይሁን እንጂ ከሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ሳምንታት ጀምሮ በአገልግሎት መስኮች ላይ የታየውን ጨምሮ፣ በኢንዱስትሪው በተለይም በአምራቹና በግንባታ ንዑስ ዘርፎች ላይ በታየው ጫና ሳቢያ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀድሞ ከነበረው ትንበያ ወደ ታች ዝቅ እንደሚል አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በኮቪድ-19 ምክንያት ካቀድነው ከ2.8 እስከ 3.8 በመቶ ዕድገቱ እንደሚንሸራተት፣ ይህም ማለት ዕድገታችን በአምስትና በስድስት በመቶ መካከል እንደሚሆን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ አኃዝ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና ሌሎችም ካስቀመጧቸው ትንበያዎች ጋር ተቀራራቢነት እንዳለው ተብራርቷል፡፡

አንዳንድ ጸሐፍት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 3.5 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል ትንበያዎችን እያስቀመጡ ነው፡፡ ባለፈው ዕትም በወጣው ዘገባ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በሠራው ጥናት ወረርሽኙ ለስድስት ወራት ቢቆይና በዚህ ጫና ሳቢያ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዎችን ብታግድ፣ የ200 ቢሊዮን ብር ወይም የአሥር በመቶ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያጋጥማት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) እንደሚችል ትንበያ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ሁኔታ በከፊል ከተወሰዱት ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ዕገዳና ክልከላ በቀር ሙሉ ለሙሉ የመዝጋትና የመግታት ዕርምጃዎች፣ ሊያስከትሉ ከሚችሉት መጠነ ሰፊ ጉዳት አኳያ እንደማይወሰዱ ኮሚሽነር ፍፁም (ዶ/ር) ገልጸው፣ የማኅበሩ ትንበያ ያስቀመጠው የይሆናል ሥሌት በአብዛኛው አካዴሚያዊ ዕሳቤ እንጂ በተጨባጭ ሊያጋጥም የሚችል እንደማይሆን ሞግተዋል፡፡

ከኢኮኖሚው ክፍሎች በተለይ የአገልግሎት ዘርፉ ክፉኛ ጫና ውስጥ መግባቱ እየታየ እንደሚገኝ ያስረዱት ኮሚሽነሯ፣ ቱሪዝም፣ ሆቴልና ሬስቶራንት፣ ትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ እንዲሁም ሲኒማ ቤቶችን የመሳሰሉ መዝናኛ ቦታዎችን ጨምሮ በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ሥራዎች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ዜጎች በስፋት ጫና ውስጥ እንደሚወድቁ ገልጸዋል፡፡ በኢንዱስትሪው መስክ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበርክት በመሆኑ፣ መንግሥት ጣልቃ ካልገባ በቀር በከፍተኛ መጠን ሊጎዳ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ መስኩም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልገው ሲሆን፣ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች፣ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ አቅርቦቶች ላይ የተጣሉ ገደቦችና ክልከላዎች የአቅርቦት ሰንሰለቱን ሊረብሹት ስለሚችሉ የጎላ ተፅዕኖ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

ግብርና በዚህ ዓመት በፍፁም ከጉዳት ነፃ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፣ የመኸር ወቅት ድኅረ ምርት መረጃዎችም ይህንኑ እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል፡፡ የአየር ፀባይ ሁኔታው ከተሠሩ ሥራዎች ጋር ተዳምሮ ጥሩ የምርት መጠን አስገኝቷል ያሉት ፍፁም (ዶ/ር)፣ በመኸር ወቅት ከተቃደው ከ329 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የዋና ዋና ሰብሎች ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የምርት መጠን የመስኖና የሰፋፊ እርሻዎችን ምርቶች ሳይጨምር እንደሆነም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...