Friday, September 29, 2023

ከመካከለኛው ምሥራቅ እንዲወጡ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መበራከት ለኢትዮጵያ ፈተና መደቀኑ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሳዑዲ የመጡ ሦስት ሺሕ ያህል ስደተኞች በአዲስ አበባ በተዘጋጀ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል

የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች በተለይም የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በግዛታቸው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በገፍ ማስወጣት መጀመራቸው፣ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል ላይ ፈተና መፍጠሩ ተገለጸ።

ባለፋት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 2,963 ኢትዮጵያውያንን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በአውሮፕላን በማጓጓዝ ወደ አዲስ አበባ ያመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ ኃይል እነዚህን ተመላሽ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ተጓዦች ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ተብለው በተዘጋጁ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲቆዩ አድርጓል።

ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የቫይረሱን ሥርጭት አስመልክቶ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በማኅበራዊ ትስስር ገጽ የቪዲዮ ውይይት ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከጂቡቲ እንዲወጡ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ፣ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ ተግዳሮት ይዞ እንደመጣ ገልጸዋል።

እነዚህን ዜጎች በኳራንቲን (በመለያ ማዕከል) ለይቶ ለማቆየት ከባህልና ቱሪዝም፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ እንዲሁም ከሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በትብብር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 ከተጠቀሱት አገሮች እንዲመለሱ የተደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ መደረጉን፣ ከብዛታቸውም የተነሳ አስቸጋሪ ሁኔታ በቅጥር ግቢው እንደሚታይ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ለይቶ ማቆያ በተጨማሪ በሲኤምሲ የሚገኘው ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ተመላሽ ስደተኞችን ለማስጠለል ተዘጋጅቶ፣ የተወሰኑ ተመላሾች ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

ከሳዑዲ ዓረቢያ የልዑላን ቤተሰቦች መካከል 150 የሚሆኑት በቫይረሱ እንደተጠቁ የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ናቸው፡፡ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ብዛት ከ5,000 በላይ ሲሆኑ፣ 73 ያህል ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡  

የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መረጃ እንደገለጸው በሳዑዲ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ናቸው። ፋይናንሺያል ታይምስ ለተባለው ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባልደረባ፣ በአንድ በረራ ከሳዑዲ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ከተደረጉ 308 ኢትዮጵያውያን መካከል ሰባቱ በቫይረሱ ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ እንደተወሰዱ ተናግረዋል። በዚህ ሁኔታም በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭትን ከቁጥጥር ውጪ እንዳያደርገው መሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ (ዶ/ር) ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲመለሱ እየተደረጉ ያሉት ስደተኞች ቅድመ ምርመራ ሳይደረግላቸው ተፋፍገው እየተላኩ መሆኑን ገልጸው፣ ቁጥሩን በትክልል ባያስታውሱትም የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው ተመላሽ ስደተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስም ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰድ የጀመረች ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት ስደተኞችን አስገድዳ ለመመለስ ዝግጅት ማድረጓን የአገሪቱ ሚዲያዎች ሰሞኑን ዘግበዋል። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው ይፋ ከተደረጉት ሰዎች መካከል 75 በመቶ ከዱባይ ወይም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የተመለሱ መንገደኞች ናቸው።

በዚህ ሁኔታ ላይ የተጠየቁት ሚኒስትሯ ሊያ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ የኤምሬትስ አየር መንገድ ከመጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መንገደኞችን ለማመላለስ፣ ወደ ዱባይም ሆነ ወደ አዲስ አበባ እንዳይበሩ መታገዳቸውን ጠቁመዋል።

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በዚህ ወቅት ስደተኞችን አስገድደው ማስወጣት መጀመራቸው የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር በቂ አቅም ለሌላቸው አገሮች አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥርና ስደተኞቹንም ለአደጋ የሚያጋልጥ ስለሆነ እንዲቆም ጠይቋል።

የቫይረሱ ሥርጭትን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ስደተኞች ባሉበት እንዲቆዩና ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ፣ መመለሳቸው የግድ ከሆነም በቅድሚያ መላሽ አገሮች ስደተኞቹ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብሏል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -