Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየስፖርቱ ማኅበረሰብ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገውን ድጋፍ ቀጥሏል

የስፖርቱ ማኅበረሰብ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገውን ድጋፍ ቀጥሏል

ቀን:

አትሌቶች ስለ ወረርሽኑ የተገቢ አካላት መረጃን እንዲከተሉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ከታወቀበት ከመጋቢት መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በቡድንም ሆነ በተናጠል ለወረርሽኙ መከላከያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡ ከሰነበቱት ተቋማት መካከል የስፖርቱ ዘርፍ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች አሠልጣኞች እንዲሁም የስፖርቱ ሙያተኞች በተናጠል ያሰባሰቡትን አንድ ላይ በማድረግ በድምሩ 120,000 ብር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) አስረክበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተና ሌሎችም አስተባባሪነት የኢትዮጵያ አሠልጣኞች ማኅበር በበኩሉ ከአባላቱ ያሰባሰበውን 125,000 ብር የገንዘብ ድጋፍ በተመሳሳይ ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸው ታውቋል፡፡

ገንዘብ ከማሰባሰቡ ጎን ለጎን ከሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የተሰባሰቡ ደጋፊዎችና ታላላቅ የስፖርት ሙያተኞች በጋራ “ወገን አድምጠኝ ልብህን ስጠኝ” የሚል ዜማ በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ ከወረርሽኙ ራሱን እንዲጠብቅ የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞና የአሁን ተጫዋቾች (ከሁለቱም ፆታ) በሚኖሩባቸው ከተሞችና አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ከወረርሽኙ ራሱን እንዲጠብቅ የበኩላቸውን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

እግር ኳሳዊ በሆነው የተቀናቃኝነት ስሜት (ደርቢ) ለዓመታት የሚታወቁት የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ስታዲየምና አካባቢው በጎዳና ተዳዳሪነት ለሚታወቁ ወገኖች ምግብና አልባሳት በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡     

በሌላ በኩል የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፡፡ ለወትሮ ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ በቡድን እየሆኑ ጨዋታ የሚደረጉባቸው አውራ ጎዳናዎች ጨምሮ ሌሎችም ቦታዎች አሁን ላይ ሰው አልባ የሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይሁንና የሕክምና ሙያተኞች በበኩላቸው ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ምክንያት የሆነው ኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም አካላዊ እንቅስቃሴ ግድ እንደሚል ይናገራሉ፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱና ሌሎችም ሙያተኞች፣ ኅብረተሰቡም ሆነ ተጫዋቾች ችግሩን በመፍራት ከቤታቸው ዝም ብለው እንዳይቀመጡ ሙያዊ ምክር ይሰጣሉ፡፡ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸውን ቦታና ጊዜ ማለትም ነፃና ገለልተኛ ቦታዎችን በመምረጥ ከተለመደው የዕለት ዕለት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያለባቸው ስለመሆኑ ጭምር ይመክራሉ፡፡ በተለይ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከአካላዊ እንቅስቃሴው በተጨማሪ አመጋገባቸው ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩልም ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ “ኮቪዲ 19” ይፋ ከሆነበት ቀን እስከ አሁን ወደ ማኅበረሰቡ የሚወርዱ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን መለየት ለማይችል የማኅበረሰብ  ክፍል ከባድ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሚሆኑት መካከል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ አድማሱ ሳጂ ከመደበኛው ሙያቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ከየአቅጣጫው በየቀኑ ብቻ ሳይሆን በየሰዓቱና በየደቂቃው የሚደመጡ ተደጋጋሚ መረጃዎችና ማስረጃዎች በተለይም መረጃዎች እንዴትና በምን አግባብ እንደሚወጡ መለየት ለማይችል የማኅበረሰብ ክፍል ከወረርሽኙ ገዳይነት ባልተናነሰ ከባድ ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ወረርሽኙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍባቸው መንገዶች እጅግ ውስብስብ እንደሆነ የሚያምኑት አቶ አድማሱ፣ “ወረርሽኙን ተከትሎ የሚወጡ መረጃዎች በአጠቃላይ ስለሚኖራቸው ይዘትና ምንነት ላይ ኅብረተሰቡ የዳበረ ልምድና አቅም ሊኖረው ይገባል፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና የሚኖሩበት የማኅበረሰብ ክፍል በዚህ ረገድ ክፍተት ስላለባቸው ግንባር ቀደም የችግሩ ተጠቂ እንደሚሆኑ እንገነዘባለን፤” ይላሉ፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙኃን ከሳምንት ሳምንት ከኮቪዲ 19 ውጪ ሌላ ወሬ እንደሌላቸው የሚናገሩት የፌዴሬሽኑ አመራር፣ “አንዱና ዋነኛው ችግር ሁሉም ሚዲያ የመረጃውና ማስረጃው ምንነት እንዲሁም ተዓማኒነቱ ጭምር ሳይጣራ የሰማውንና ያየውን ሁሉ ያሰራጫል፡፡ በዛ ላይ ወረርሽኙ ከገዳይነቱ ባሻገር የሚተላለፍበት መንገድ ረቂቅ መሆኑ እንደተጠበቀ በተለይ ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው አትሌቶች ብቻ ሳይሆን ጤነኞቹ ጭምር የሥነ ልቦና ችግር ውስጥ ይገባሉ፣ ምክንያቱም ብዙዎቹ አትሌቶች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የሚደጉሙበት ብቸኛ ሙያቸው በመሆኑ ነው፤” በማለት ያስረዳሉ፡፡

አሁን ላይ በዕውቀታቸውም ሆነ በሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ የላቁት አገሮች እንኳ ቫይረሱ መቼና እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኝ የሚያውቁት አንዳች እንደሌለ የሚናገሩት አቶ አድማሱ፣ “ይህ በተለይ እንደ ኢትዮጵያውያን ላለው የማኅበረሰብ ክፍልና የዚሁ አካል ለሆኑት አትሌቶች እጅግ አስቸጋሪና ከባዱ ነገር ነው፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማሳያ ደግሞ ከሥልጠና ጋር ተያይዞ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሁን አሁን እንደሚነገረው ሳይሆን፣ ከአመጋገባቸው ጭምር ልምምድ የሚሠሩት በጋራ ነው፣ መለያየቱ እውነት የሆነው አሁን ላይ ነው፣” በማለት ምን ያህል የሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

መፍትሔውን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ አመራር፣ “አትሌቶች ወረርሽኙን በሚመለከት ከጤና ባለሙያና ከሌሎች ትክክለኛ አካላት የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ እየሰሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው፣ ቫይረሱ እንዳለ አምኖ ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ገዳይ መሆኑን ማመን፣ መረጃ ምንጮችን መለየትና መጠንቀቅ፣ በተረጋጋ መንፈስ ወሳኝና አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ማድረግ ለሚችሉት ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ ለዚህም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፤” ይላሉ፡፡

በመጨረሻም አትሌቶች እንደ ልብስ ማጠብ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችንና መጽሐፍ ማንበብ የመሳሰሉትን ቢያዘወትሩ አዎንታዊ የሆኑ አስተሳሰቦች በቀላሉ እንደሚገነቡ የዘርፉ ሙያተኞች ምልከታ መሆኑን ጭምር በመግለጽ ይመክራሉ፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...