Friday, December 1, 2023

ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተቀመጠውን ገደብ የማንሳት አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከቻይና ውሃን ከተማ ተነስቶ ዛሬ ላይ ዓለምን ያካለለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አራት ወራት ቢያስቆጥርም፣ የሚያዙ ሰዎችም ሆነ የሞት ቁጥር ሲያሻቅብ እንጂ በቁጥጥር ሥር ሲውል አልተስተዋለም፡፡ የወረርሽኙ የመጀመሪያ ተጠቂ የሆነችው ቻይና፣ በሽታውን በቁጥጥር ሥር አውላ በሰዎች መንቀሳቀስና መሥራት መብት ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ ቀስ በቅስ እያነሳች ነው፡፡

ቻይና፣ ይህንን ለማድረግ ግን ከሦስት ወራት በላይ በሽታውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ተረባርባለች፡፡ የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ‹‹በሰው ልጆች ላይ የተከፈተ ጦርነት›› ብለው የገለጹትን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ልትቆጣጠር የቻለቸውም፣ በሰው ልጅ ታሪክ ረዥም ጊዜ የተባለውን ቤት ውስጥ የመቀመጥ ግዴታ ከ50 ሚሊዮን በሚበልጡ ዜጎቿ ላይ ጥላ ነው፡፡ ቫይረሱ በርካቶችን በሚይዝበት ወቅት የተጣለው ገደብ፣ በርካቶችን ከወጡበት ሳይመለሱ እንዲቆዩ ቢያደርግ፣ የብዙዎችን ሕይወት ግን ታድጓል፡፡

ትምህርት ቤቶች፣ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጭምር ለሁለት ወር ያህል ከእንቅስቃሴ መታገዳቸው በቻይና የሟቾች ቁጥር ከ3,400 እንዳይልቅ አድርጓል፡፡ 84,393 በቫይረሱ የተያዙ ቢሆንም፣ 78,877 እንዲያገግሙ አስችሏል፡፡ የቻይና የጤና ሥርዓት በሽታውን መቆጣጠር የቻለውም፣ በአገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሉ ምክንያት በቫይረሱ የሚጠቁትን ቁጥር መቀነስ በመቻሉ ነው፡፡

ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተቀመጠውን ገደብ የማንሳት አንድምታ

 

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዙዎሎጂ ተጋባዥ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ዳይ፣ በሳይንስ ጆርናል ላይ ያሰፈሩትን ጥናት ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፣ በቻይና ቫይረሱ በተገኘ በ50ኛው ቀን በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር 30,000 አካባቢ ነበር፡፡ ቻይና በሽታው መጀመርያ የተነሳበት ውሃን ከተማን ሙሉ ለሙሉ ባትዘጋ፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ባትገድብና በአገር አቀፍ ደረጃ ገደቦችን ባታስቀምጥ ኖሮ ቫይረሱ በተገኘ በ50ኛው ቀን 30,000 ሰው ሳይሆን ከ700,000 ሰው በላይ በቫይረሱ ይጠቃ ነበር፡፡ ሆኖም ገደቡ ለሁለት ወራት ያህል መዝለቁ ቻይና ቫይረሱን እንድትቆጣጠር አስችሏል፡፡

 ቻይና ገደቦቿን ቀስ በቀስ እያነሳች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በሽታውን በቁጥጥር ሥር ያላዋሉ አገሮችም ገደብ እንደሚያነሱ እያስታወቁ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ግን ጥንቃቄ ያልታከለበት ገደብ ማንሳት ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ብሏል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ አገሮች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የጣሉትን ገደብ ለማንሳት የሚያሳዩት ፍላጎት ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ገደቦች ላላ እንዲሉ ይፈልጋል ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የሚደረግ የገደብ መነሳት የቫይረሱን ገዳይነት እንደሚጨምረው፣ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የቫይረሱ ሥርጭት እየቀነሰ መምጣቱ የሚያበረታታ ቢሆንም፣ በአፍሪካ በ16 አገሮች የታየውና ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ሥርጭት አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የትኛውም አገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት አለኝ ሊል አይችልም፣ ራሱን መከላከልም አይችልም፣ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት መሥራት አለብን፡፡ ከወረርሽኙ መማር አለብን፣ ይህ ላደጉ አገሮችም መልዕክት ነው፡፡ የነበሩብንን ክፍተቶች መሙላት ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አሁን ላይ ኮቪድ 19ን ለመግታት በየአገሮች የተጣሉ ገደቦችን ያለ ጥንቃቄ ማንሳት ጊዜው አይደለም ቢልም፣ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ገደብ ማንሳት ላይ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ጠቅላላ የተጣለውን ገደብ የማንሳት አቅም እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከግዛት አስተዳዳሪዎችና ከሕግ ባለሙያዎች የተቃረነ ቢሆንም፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ተብሎ በስፋት የተዘጋውን ኢኮኖሚ መልሶ ለማንቀሳቀስ አስተዳደራቸው ዕቅዱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ ገደቦች ሊነሱ እንደሚችሉ፣ አሁን አላስፈላጊ ጉዞ፣ ከአሥር በላይ ሆኖ መሰብሰብና ምግብ ቤቶችን መዝጋትን ጨምሮ በአገሪቱ የተጣሉት ገደቦች በሚያዝያ 30 ሊያበቃ እንደሚችል ፍንጭ ተሰጥቷል፡፡

በአሜሪካ ከ40 በላይ ግዛቶች ሕዝቦቻቸው ቤት እንዲቀመጡ ገደብ ጥለው የነበረ ሲሆን፣ ከአሥር በላይ የሚሆኑት ገደቡን ለማንሳት ማቀዳቸውን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

በቫይረሱ ክፉኛ የተመታችው ኒውዮርክ ከተማ አስተዳዳሪ አንድሪው ኩሞ፣ በግዛታቸው ክፉው ጊዜ እያለፈ ስለመሆኑ ጠቁመው፣ የሕዝቡ ጤናም ሆነ ኢኮኖሚው ቀዳሚ አጀንዳ ናቸው ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አሁን ላይ የተጣሉ ገደቦችን ለማንሳት መቻኮል ከባድና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ኢኮኖሚያዊ ውድመት ያስከትላል ሲል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም፣ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የጣሉትን ገደብ ለማንሳት ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ በየአገራቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መቀነስን መሠረት በማድረግ ብዙም አስፈላጊ ያልሆኑ ሱቆችና የውበት ሳሎኖች እንዲሁም ሌሎችንም ከግንቦት 1 ጀምሮ ለመክፈት አቅደዋል፡፡

ኦስትሪያ፣ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ቀስ በቀስ እንደሚከፈቱ ስታሳውቅ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የባይስክልና የግንባታ ዕቃዎች መሸጫ ሱቆችን ከፍታለች፡፡ ዴንማርክ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላትና እስከ አምስተኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ስታደርግ፣ እስከ ግንቦት 10 ቀን ደግሞ የውበት ሳሎኖች፣ ምግብ ቤቶች፣ የሰውነት ማጎልመሻ ሥፍራዎችና ሌሎችም እንዳይከፈቱ ወስናለች፡፡ ኖርዌይ፣ ቡልጋሪያ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔንና አየርላንድ ቀስ በቀስ ገደቦችን በከፊል እያላሉ እንደሚሄዱ አስታውቀዋል፡፡

የፖሊሲ መላ አፈላላጊ (ቲንክ ታንክ) የሚባለው የአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲትዩት በቅርቡ በለቀቀው ሪፖርት፣ አገሮች ገደቦችን ለማንሳት አራት ደረጃ ያስፈልጋቸዋል ብሏል፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንዳይኖሩ መሥራት ሲሆን፣ ለዚህም ርቀትን መጠበቅ፣ ትምህርት ቤትን መዝጋትና ሰዎች ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ማመቻቸት ይገባል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የመመርመር ብሎም ለይቶ የማቆየት አቅም መገንባት ወሳኝ ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ ክትባት ሲገኝ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዝቦች በሽታውን መቋቋም ሲችሉ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ገልጾ፣ በአራተኛ ደረጃ አሁን ያለው ወረርሽኝ ሲያበቃ በቀጣይ ለሚወጣው ወረርሽኝ በቂ ጥናትና ዝግጅት ማድረግ ሲቻል እንደሆነ አሳውቋል፡፡

ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተቀመጠውን ገደብ የማንሳት አንድምታ

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -