Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የትንሳዔን በዓል በቤትዎ››

‹‹የትንሳዔን በዓል በቤትዎ››

ቀን:

የትንሳዔ በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ የክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ የዓለም አገሮች ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት ከሚከበሩት መንፈሳዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሆኖም የአከባበሩ ዕለት የሚለያይበት፣ አልፎ አልፎም በአንድ ቀን የሚውልበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር የጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠር የሚከተሉት የዘንድሮ ትንሳዔ በዓል ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና የጁሊያን አቆጣጠር የሚከተሉት ምሥራቃውያን ደግሞ ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ያከብራሉ፡፡

የመጀመርያዎቹ አክባሪዎች በዓሉን ያከበሩት ለመጀመርያ ጊዜ ቤት በመዋል ነበር፡፡ ምዕራብ አውሮፓውያንና ሌሎች የነርሱን አቆጣጠር የሚከተሉት በዓሉን በቤት እንዲያከብሩ ያስገደዳቸው፣ የሥርጭት አድማሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ የመጣው፣ መድኃኒትና ክትባት ያልተገኘለት ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው ለበዓሉ የሚሆን ምግብም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች ግዢ በየሱፐርማርኬት ሳይንገላታ፣ ለወጪም ሳይዳረግ ቤት ያፈራውን በመቅመስ ከቤተሰቡ ጋር እየፀለየና እየተዝናና በሰላም ማሳለፉን በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስንልም ያለው ሁኔታ ከቤት የሚያስወጣ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በሬና ዶሮ ካልታረደ፣ የቅርጫ ሥጋ ካልገባ ጎረቤት፣ ዘመድ አዝማዱ እየተጠራራ በአንድ ላይ ካልበላና ካልጠጣ በዓል መስሎ ላይታይ ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ጥሩ መስተጋብር የሚፈጥር፣ ሲያያዝ የመጣ፣ የመረዳዳትና የመደሰት ባህል ቢሆንም፣ አሁን ካለው የወረርሽኝ ሥጋት አንጻር ለጊዜው መገታት እንደሚኖርበት ይመከራል፡፡

በግና ዶሮ ተራ ሄዶ መተፋፈግና መጨናነቅ መፍጠሩ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ ሁኔታው ማኅበራዊ ርቀትን ጠብቆ ለመገበያየት አዳጋች ነው፡፡

በመሆኑም የትም ሳይኬድ የተገኘውን ተቃምሶ ቤት ውስጥ ማሳለፉ አማራጭ የማይገኝለት ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተጠቀሰው ሐሳብ ይስማማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፀረ ኮሮና ቫይረስ የቅድመ ዝግጅትና ምላሽ አሰጣጥ ክፍል አስተባባሪ ያረጋል ፉፋ (ዶ/ር)፣ እንደሚያስገነዝቡት፣ ሰዎች ብዙም ሳይጨናነቁ ቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሰላምና በጤና በዓሉን ማሳለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በግና ፍየል የመግዛቱ ሁኔታ የግድ ከሆነ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በግና ፍየል እንገዛለን ብለው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚተላለፈውን ገዳይ ቫይረስ ሸምተው ይመለሳሉ፡፡

ዶሮ፣ በግ፣ ወይም ፍየል ካልታረደና የቅርጫ ሥጋ ካልገባ፣ ጎረቤት ተጠርቶ ካልበላና ካልጠጣ ዕለቱ ዓመት በዓል መስሎ የማይታያቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ዓይነቱን ሁኔታ ዛሬ በአገርና በመላው ዓለም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ በተከሰተበት ዘመን ተግባራዊ ቢደረግ ለከፍተኛ ኪሳራና ውድቀት ከመዳረጉ ባሻገር፣ በቅርርቡ ሳቢያ የሚፈጠረው የጤና ሥጋት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው እንደ አቅሙ በዓሉን ቤቱ ውስጥ ከቤተሰቡ ጋር በሰላም ማሳለፍ እንዳለበት አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሌ በዓሉ ትልቅና ሲያያዝ የመጣ መንፈሳዊ በዓል እንደመሆኑ፣ ማስቀረት እንደማይቻል፣ ነገር ግን ገዥና ሻጭ ሁለት ሜትር ያህል ተራርቀው ቢገበያዩ፣ ማኅበረሰቡም መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች በየጊዜው የሚሰጡትን ምክርና መመርያ ተቀብሎ ቢተገብር ወረርሽኙን ለመከላከልና በዓሉንም በሰላምና በጤና ለማሳለፍ ዋነኛ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ገበያው በአንድ ቦታ ከሚከማች፣ ወደ ማኅበረሰቡ ጠጋ ቢል ማኅበራዊ ርቀትን የጠበቀና ከንክኪ ነፃ የሆነ ሸመታ ለማከናወን እንደሚቻል አክለዋል፡፡

ዋና መሥሪያ ቤቱ ስዊዘርላንድ የሚገኘው ‹‹ኤኦ›› የተባለ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ወ/ሮ ትዕግሥት አሰፋ የአቶ ጌታቸውን አስተያየት በመጋራት ግብይቱ የማኅበረሰቡን ተደራሽነት ባማከለ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

አለበለዚያ ሰው ለሁለት ወራት ያህል ፆሞ ከገበያ እንቅስቃሴ እንዲገታ ወይም ቤት እንዲውል ለማድረግ መሞከሩ የተሻለ ነው ብሎ ለመቀበል እንደሚከብዳቸው አመልክተዋል፡፡

የእንጦጦ ሙዚየም ዋና ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን ዳኜ ሕማማትን ቤት ውስጥ በጸምና በፀሎት እንዳሳለፍን ሁሉ የትንሳዔ በዓልንም በዚህ መልኩ ታስቦ መዋል እንደሚገባ፣ ለዚህም የሚውለው ወጪ የኢኮኖሚ አቅምን ባገናዘበ መልኩ መሆን እንዳለበት፣ ቤተ ክርስቲያንም ለምዕመኖቿ የምትመክረው ይህንኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከበዓል አከባበሩ ውጪ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣው የአክፋይ ሥርዓት በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት የሚያጠያይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ለወረርሽኙ መጋለጥና መንስዔ ከሆኑት እንቅስቃሴዎች መካከል አንደኛው ክስተት ብዙ ሆኖ መሰባሰብ ነው፡፡ የአክፋይ ሥነ ሥርዓት ደግሞ ሁሉም ቤተሰብ ከያለበት ወደ እናትና አባት ወይም ታላቅ እህት ወይም ወንድም ቤት የሚሰባሰብበት የደስታና የስጦታ በዓል ነው፡፡

ይህንን ለማድረግ ከከተማ ወደ ክልል ከክልል ወደ ከተማ የሚመጡ ቤተሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ በአክፋይ በዓል ዕለት በአንድ ቤት ውስጥ ልጅና የልጅ ልጆች ጎረቤት የዘመድ አዝማዱ ቁጥር ከ50 ይልቃል፡፡ በቤተሰብ መካከል ምን ያህል ማኅበራዊ ርቀት ይጠብቃል? ግላዊነትስ ይኖራል ወይ? ጥንቃቄውስ በቢሮና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደምናደርገው ይሆናል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

ሊቀ ሥዩማን ዳኜ እንደሚሉትም፣ የአክፋይ ሥነ ሥርዓትንም ከመሰባሰብ ይልቅ ሁሉም በየቤቱ እንዲያከብረው ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...