Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየእነ ጭር ሲል አልወድም ፖለቲካ!

የእነ ጭር ሲል አልወድም ፖለቲካ!

ቀን:

በቁምላቸው አበበ ይማም

‹‹እውነተኛ መሪ አገሩ ፈተና በገጠመው ሰዓት ሕዝቡ ከእዚያ ፈተና እንዲወጣ ለማገዝምን ማድረግ አለብኝ?’ ሲል ራሱን ይጠይቃል፡፡ አድርባዩ ደግሞይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ እንዴት ራሴን ከፍ ለማድረግና የምሻውን ሁሉ ለመጨበጥ እችላለሁ?’ ብሎ ይብሰለሰላል፡፡ ‹‹ኃይለ ጊዮርጊስ ማሞ የተባሉ የፍትሕ ዓምደኛ በቅርቡ፣ ‹‹የፖለቲከኛ በየዓይነቱ!›› በሚል ርዕስ ካደረሱን ዘመኑን የዋጀ መጣጥፋቸው የቃረምሁት፡፡  በዚህ ጥቅስ ማንጠሪያነት የሁለት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እርስ በርሱ የሚጣረስ ወለፈንድ መግለጫንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሰሞነኛ ተጨባጭና ትክክለኛን ውሳኔ መሳ ለመሳ እንመለከታለን፡፡

በተያዘው ዓመት ሊካሄዱ ቀን ከተቆረጠላቸው 70 አገሮች ምርጫዎች ባለፈው አንድ ወር ብቻ በመላው አለም 40 አገሮችና ግዛቶች ሊካሄዱ የነበሩ 60 ብሔራዊ፣ የከተማና አካባቢያዊ ምርጫዎችኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ሥጋት የተነሳ ወደ ሌላ ጊዜ መራዘማቸውን (International Institute for Democracy and Electoral Assistance) (International IDEA) በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ዚምባቡዌ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋምቢያና ቱኒዚያ ከአኅጉራችን ይገኙበታል፡፡ በአሜሪካ 25 ግዛቶች የዴሞክራት ዕጩዎችንና የማሟያ ምርጫዎችን፣ በአውሮፓ 16 አገር አቀፍ፣ የፓርላማና የከተሞች ምርጫና ሕዝበ ውሳኔዎች፣ በእስያ ስምንት የብሔራዊ፣ የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች፣ በአውስትራሊያ፣ በሰሎሞን ደሴቶችናፓፑዋ ኒው ጊኒ እንዲሁ ተራዝመዋል፡፡

ኮሮና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ 30 አገሮችና ክልሎች ምርጫቸውን ያራዝማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የየአሮቹ ውሳኔ ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ሕይወት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ የሚያስረግጥ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ፈታኝ ጊዜ የመሪዎች የመወሰን አቅም፣ አስተባብሮ የመምራት ክህሎትና ጥበብ፣ እንዲሁም የመሪዎች ማንነት የሚፈተነው ከፖለቲካ ጥቅም በላይ ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ሕይወት ለማዳን በሰጡት ስትራቴጂካዊና ታክቲካዊ አመራር ነው፡፡ እዚህ ላይ የአሜሪካን መሪ ከሲንጋፖርና ከደቡብ ኮሪያ ያነጣጥሯል፡፡

እንደ ዶናልድ ትራምፕ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት አስይዞ፣ ፖለቲካዊ ቁማር የሚቆምር ከሆነ፣ እሱ መሪ ሳይሆን የፖለቲካ ሱቅ በደረቴ ነው፡፡ በቀኝ አክራሪዎችና በትራምፕ ሳምባ የሚተነፍሰው ፎክስ ቴሌቪዥንም ወረርሽኙን በማቃለልና ትራምፕን ለመጣል የተሸረበ የደባ ኀልዮት እንጂ፣ ኮሮና ከሌላው ቫይረስ የተለየ አይደለም እያለ ሕዝቡን ማዘናጋቱ ዛሬ አሜሪካ ለምትገኝበት ቀውስ በታሪክ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ፣
‹‹አገር የመምራትን ሥልጣን የጨበጠ በመንግሥትነትም ዙፋን ላይ የተቀመጠ መሪ እውነተኛ ማንነቱ የሚገለጸው ፈተና ወይም ውድቀት ከፊቱ የተደቀነ ጊዜ ነው፤›› እንዳሉት፣ በዚህ አስተዛዛቢና ፈታኝ ሰዓት የለውጥ ኃይሉም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ የወርቅ ሚዛን እየተመዘኑ ነው፡፡

ምንም እንኳ የምዘናውን ውጤት ለማወቅ ጊዜው ገና ቢሆንም፣ ከአሁኑ ከሚዛኑ ለመጉደል ዳር ዳር የሚሉን እየተመለከትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ሁለት ‹‹እህትማማች›› ፓርቲዎች በዚህ የጭንቅ የጥብ ቀን ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ይልቅ ፓርቲን፣ ፖለቲካዊ ሒሳብ ማወራረድንና ነጥብ ማስቆጠርን ያስቀደሙየጭር ሲል አልወድም ፖለቲከኛ አራማጅና መንግሥትን የማገት አባዜ የተጠናወታቸው የሚያስመስል መግለጫ አውጥተዋል፡፡

የፕሬዚዳንታዊ ታሪክ አጥኝዎችና የሕይወት ታሪክ ጸሐፍት ዶሪዝ ከርነስና ጆን ሜቻም አንድ መሪ ሊያሟላቸው ከሚገቡ ዋና ዋና ባህሪያት አንዱ የሕዝብን ችግር እንደ ራስ ማየት፣ መረዳት ነው ይላሉ፡፡ ሰሞኑን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ሕዝብ በዚህ ፈታኝ፣ አስፈሪና አስጨናቂ ሰዓት በሞትና በሕይወት መካከል በቀጭን ገመድ እየተራመደ እያለ ፖለቲካና ምርጫ አጀንዳዎቹ ሊሆኑ እንደማይችሉ እያወቁ፣ መግለጫ መስጠት ለምን አስፈለገ? ይኼን መረዳትስ እንዴት ተሳናቸው? ፍርኃቱን፣ ጭንቀቱንና ችግሩን እንደ ራሳቸው ችግር ዓይተው መጋራትና የመፍትሔው አካል መሆን ሲገባቸውሕዝብ ያለ ምንም የጎሳ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ልዩነት እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድነት ቆሞ ወረርሽኙን ለመመከት እየተረባረበ ባለበትየሕክምና ባለሙያዎች፣ የወገን አለኝታ የሆኑ ዜጎችና የካቢኔ አባላት ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ 24 ሰዓት ያለ ዕረፍት እየሠሩ ባሉበት፣ በአገሪቱ ሰማይ የፍርኃት ዳመና ባጠላበት እንዲህ ያለ ትኩረት አስቀያሽ መግለጫ ማውጣት ምን ይሉታል? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጋቢትና በሚያዚያ ማጠናቀቅ ከሚገባው ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠናና ሥምሪት፣ የመራጮች ትምህርት፣ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ሥርጭትና የመሳሰሉት ተግባራት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ ተስተጓጉለዋል፡፡

 በምርጫው  የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተጣለበት ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት እያደረገ ሳለ፣ ካለፉት ሦስት ወራት በፊት በዓለማችን ከሦስት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በአገራችን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ የመንግሥትንና የግል ተቋማትን አሠራር እንደ ገና በመበየኑ ሌሎች ተቋማት እንዳደረጉት ምርጫ ቦርድም ሥልጣኑን ተጠቅሞ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ ሰርዟል፡፡ የሌሎች አገሮች ምርጫ ቦርዶች እንዳደረጉት ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ቀን፣ እንዲሁም የቅድመና ድኅረ ምርጫ ጊዜ ሰሌዳዎችን ሰርዟል፡፡

የቀድሞው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ‹‹ኮቪድ 19 እና ምርጫ›› በሚል ርዕስ ፍትሕ መጽሔት ላይ ባስነበቡን መጣጥፍ፤››. . . ‘በዝናብ እንዴት አርገን ቀስቅሰን ነው ምርጫ የምንወዳደረው?’ ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች፣ ‹‹በኮቪድ 19  የተነሳ የምርጫ ሰሌዳ ሲሰረዝ ለምን ይብሰከሰካሉ? ሲሉ›› በዘወርዋራ ይሞግታሉ፤›› ኦሎምፒክን ያህል ግዙፍና ከፍተኛ ወጭ የወጣበት  ዓለም አቀፍ ሁነት ተራዝሞ እያለምናልባት ለብጥብጥ ሰበብ ሊሆን የሚችል ምርጫ ቢራዘም ለምን ይገርመናል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ይሁንና ኦነግና ኦፌኮ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫ የመሰረዝ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ሲሉ በጋራ መግለጫቸው ነቅፈው፣ መልሰው ‹‹ኮቪድ 19 በምርጫ 2012 ዕቅድና የጊዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮቶችን ደቅኖ ቦርዱን እየተፈታተነ መሆኑን እንረዳለን፤›› በማለት፣ ይውጋህንና ይማርህን ያዛንቃሉ፡፡ ልግጫና ማስተዛዘኛ የሚመስል ነገር ጣል አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ፣ ‹‹የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን፤›› በማለት እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ውኃ ቀጠናቸውም፣ ‹‹ቦርዱ እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መጋቢት 12 ቀን 2012 .ም. ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ኦነግና ኦፌኮ የተገኙበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ አዘጋጅቶ ምክክር ተደርጎ እንደነበር ጠቅሶ፣ በስብሰባው መጨረሻ ላይ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚኖር ቢገለጽም፣ ይህ ሳይሆን ውሳኔ ላይ መድረሱ አግባብ አይደለም፤›› የሚል ነው፡፡ በዘወርዋራ ያለ እኛ ቡራኬ ምን ሲደረግ ማለታቸው ነው፡፡ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተቀበሉትን እነ ኦነግ ምርጫ ቦርድ ወደ ውሳኔ ‹‹የሄደበት መንገድ›› ለምን በአቋራጭ ሆነ ዓይነት ያዙኝ ልቀቁኝን ምን አመጣው!? መንገድ መሪስ ማን አደረጋቸው? ላለፉት 25 እና 50 ዓመታት የተጓዙበትን የዝንጀሮ መንገድ መቼ አጣነውና?

ወረርሽኙን ለመከላከል ማኅበራዊ ፈቀቅታ (Social Distancing) በታወጀበትምዕመናን ፀሎታቸውንና ልመናቸውን በቤት እንዲያካሂዱ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች በራቸውን በዘጉበት፣ ዜጎች ከአሁኑ ቁጥር የሚልቅ ቀሳ ወይም ወሸባ (ኳራንቲን) ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት፣ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን በቤታቸው እንዲሠሩ፣ አገር አቋራጭና ሌሎች ማኅበራዊ ፈቀቅታን የሚጥሱ መጓጓዣዎች በታገዱበት፣ሰባት ክልሎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አከልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበትምርጫ ቦርድ ለእዚያም ለሁለተኛ ጊዜ ሰብስቦ ፈቃዳችንን ሳያገኝ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን መሰረዙ ትክክል አይደለም ማለት፣ እስከ ግማሽ ክፍለ ዘመን ከዘለቀ የፖለቲካ ፓርቲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልሂቅ ለዚያውም በዚህ አስጨናቂ ጊዜ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ሲሆን ሲሆን ምን እናግዝ? እንዴት እንቀናጅ? ባሉ፡፡ ለዚያውም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ሊያስቀይር የማይችልሌላ አስማተኛ አማራጭ ያላቸው ይመስል፡፡

ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን የመወሰን ሥልጣኑን ተጠቅሞ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረዙ፣ ከጠረጴዛው ያገኘው ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አምኖ መቀበል እንጂ በሰበብ አስባቡ ማነጋገር አይገባም፡፡ በዚህ ድባብ የሚካሄድ ምርጫስ እንዴት ግልጽ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ሊሆን ይችላል? እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ተፎካካሪ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳደረጉት የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ይራዘም የሚለውን ጥያቄ ቀድመው ማቅረብ የነበረባቸው እነሱ መሆን ሲገባቸው፡፡ በሰሞነኛ መግለጫቸውም ሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባሳዩን ግንባር አያድርገውና አሸንፈው ሥልጣን ቢይዙ እንዴት እንደሚገዙን፣ ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ ማንን እንደሚያስቀድሙ አበክረን የደረሰንበትን መደምደሚያ የሚያፀና ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ለዚህ ነው ከድርጅት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን፣ አገርንና ሕዝብን ከሚያስቀድም መዳረሻ (ፌርማታ) ሳይደርሱ ባቡሩ ሲንገጫገጭ ሐዲዱን የሳተ መስሏቸው ዘለው ወርደዋል፡፡

ከማንነት ዛጎል (ሼል) ባሻገር ገዝፈው ከፍታው ላይ የሚታዩትን ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ ኩሩውን ሕዝባችንና ራዕያችንን አሻግረን እየተመለከትን ጉዟችንን ቀጥለናል፡፡ ሙኀዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትና የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሸል ኦባማ ‹‹. . .አትውረዱ!›› እንዳሉት አንወርድም፡፡ ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ መቅሰፍት ይጠብቅ! አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...