Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአንድ ዓይናችንን ኮሮና ላይ ሌላኛውን ደግሞ ሙስና ላይ ትኩረት እናድርግ!

አንድ ዓይናችንን ኮሮና ላይ ሌላኛውን ደግሞ ሙስና ላይ ትኩረት እናድርግ!

ቀን:

በሐረጎት አብረሃ

ኮሮና የዓለማችን ቁጥር አንድ ሥጋት ከሆነ ወራት አልፈዋል፡፡ ዓለም ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖላቲካዊ ቀውስ እንድትወድቅ አድርገዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የበሽታው አደገኝነትን በመረዳት የዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በሽታ (Pandemic Disease) ብሎ ካወጀ ወራት አልፈዋል፡፡ ሰዎች ማኅበራዊ  ግንኑኝት ባልተለመደ መልኩ እንዲላላና አብዛኛው ቤታቸው እንዲውሉ አስገድደዋል፡፡ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ሥነ ልቦና ቀውስ ዳርጓቸዋል፡፡ ቫይረሱ በዚህ ሳያበቃ በየደቂቃ ልዩነት ፆታ፣ ዕድሜ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ አገር ሳይለይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት ቀጥፏል፡፡ አሁንም እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ በሽታው ያልተዛመተበት አገር አለ ብሎ መውሰድ በጣም ያስቸግራል፡፡ የጣሊያን፣ የስፔን አሁን ደግሞ ልዕለ ኃያልዋ አገር አሜሪካ በየቀኑ የሚሞቱ ሰዎች መቀበሪያ ቦታ የታጣበት፣ በኢኳዶር በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች የሚያነሳቸው አጥተው በየመንገዱ የተደረደሩ የሬሳ ሳጥኖች በሚዲያ ሲታይ፣ እውነትም ወረርሽኙ የዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ሆኗል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ቫይረሱ ከዚህ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፡፡  

አፍሪካም የዚህ በሽታ ሰለባ ስትሆን አፍሪካን አዳርሶ ድንበር ተሻግሮ አገራችንም ገብቶ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ቫይረሱ ባስከተለው ሥጋት የዜጎችን መንቀሳቀስ ተገድበዋል፡፡ በርካታ ወንድምና እህቶቻችን ቢዘህ በሽታ ተይዘዋል፣ እስካሁን ባለው መረጃም ሦስት ዜጎቻችን በዚህ በሽታ ሕይወታቸው ተቀጥፏል፡፡

ኮሮናና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ

ቫይረሱ ካስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ባሻገር በዓለማችን ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በአገሮች መከላከል የነበረውን የአየር ትራንስፖርት ተቋርጠዋል፣ የአገራችን መለያ የሆነው አየር መንገድ ጨምሮ የአየር የትራንስፖርት ሴክተር በብዙ በቢሊዮን የሚገመት ኪሳራ አጋጥሞታል፡፡ በየቀኑ የብዙ ሺሕ ደሃ የዕለት ጉርስ ምንጭ  የነበሩት  የግልና የመንግሥት ተቋማት ተዘግተዋል፣ አሊያም ሠራተኛ እንዲቀንሱ ተገደዋል፡፡ ከዚህ ይባስ ብሎ ቫይረሱ ባስከተለው መዘዝ የአገሮች ኢኮኖሚ ወደ ታች እየተምዘገዘገ ይገኛል፡፡ በነዳጅ ምርት ላይ የተመሠረተውን ኢኮኖሚ ያላቸውን አገሮች በታሪካቸው ዓይተውት በማያውቁት ደረጃ ለአንድ በርሜል ነዳጅ እስከ 16 ዶላር እየሸጡ ይገኛል፡፡  የሰዎች መሠረታዊ የዕለት ፍጆታ የሚከፋፈልባቸው ሱፐርማርኬቶች፣ መጋዘኖች ባዶ ሆነዋል፡፡

አገራችንም ከዚህ የተለየ ገጽታ የላትም፡፡ ከነበረችበት የሰላም መደፈረስና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ወጥታ ወደ መረጋጋት እየሄደች በነበረችበት ወቅት ድንገት ቫይረሱ ባስከተለው ቀውስ ኢኮኖሚያችን ከፍተኛ ሥጋት ተደቅኖበታል፡፡ የብዙ ዜጎቻችን የዕለት ጉርስና የገቢ ምንጭ የነበሩት ሆቴሎች፣ የግንባታ ተቋማትና ካፌዎች ተዘግተዋል አልያም ሠራተኞቻቸው እንዲቀንሱ ተገደዋል፡፡

ወረርሽኝ ያስከተለውን የኢኮኖሚያዊ ጫና ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡ በቢሊዮንና በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ድጋፍ በማድረግ ኢኮኖሚያቸውን ከውድቀት ለመታደግ ጥረት እያደረጉ ይገኛል፡፡ የአሜሪካ የትራምፕ አስተዳደር ቫይረሱን ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከል 2.2 ትሪሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የቫይረሱ የመጀመርያ ተጠቂ የሆነችውን ቻይና ጨምሮ ህንድ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ስፔን  ወዘተ. ቫይረሱን ያስከተለውን ኢኮኖሚያው ቀውስ ለመከላከል በመቶ ቢሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የቫይረስ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግን ጨምሮ በሽታውን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራ ብሔራዊ አሰተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ቫይረሱን እንዳይስፋፋ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

ኮሮናና ሙስና 

ታዲያ ቫይረሱ በኢኮኖሚ ያሳደረውን ተፅዕኖ በማየት ወይም ወደፊት ሊያስከትለው የሚችለው ሥጋት በመገመት አንዳንድ ተቋማት፣ ግለሰቦች ወይም የተደራጁ ቡዱኖች ይኼን ወረርሽኝ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ወደ ሙስናና ሥርቆት የሚገቡበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ አገሮች ቫይረሱን ለመከላከል ከመደቡት በጀት ውስጥ ቦጭቀው ወደ ግል ኪሳቸው ለማስገባት የሚሯሯጡ ስግብግብ ሰዎች እንደሚኖሩ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ቀደም ሲል በሙስና የሚታሙ፣ ባላቸው ኃላፊነት ከተለያዩ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎችና ግለ ሰዎች ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ይኼን አጋጣሚ እንደ ዕድል ይቆጥሩታል፡፡ ከተሳካለቸውም የሰው ሕይወት ቀምተው በሚሊዮን ሊያተርፉ ይችላሉ፡፡ ሙስና በተገኙ አመቺ ሁኔታዎች ወይም ዕድሎች የሚፈጸም ወንጀል ነው የሚባለው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ነው፡፡ ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ›› እንደሚባለው በጤና ዘርፍ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት በራሱ ደካማ በመሆኑ በቀላሉ በዚህ አጋጣሚ ለመበለፀግ ለሚፈልጉ ሰዎች አመቺ ነው፡፡  

የአፍሪካ አገሮች የጤና ሥርዓት ጥራቱና ተደራሽነቱ በእጅጉ በሙስና የተዳከመ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት በራሱ ሌላ ሙስና ለመፍጠር ሰፊ ዕድል እንዳለው ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በውጭ ይሁን በውስጥ አገር የሚመረቱ መድኃኒቶች ጥራታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ ሲስተም ባለመኖሩ፣ ልክ እንደ ኮሮና ዓይነት ወረርሽኝ ለመከላከል አዳጋች መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ለሕክምና ተቋማት ግንባታና ግብዓት ሟሟያ የተመደበውን በጀት ባይዘርፉት ኖሮ፣ አሁን በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎችን የሚታከሙበት ቦታ ባላጡ፣ የግብዓት ችግርም ባላጋጠመ ነበር ብለው በቁጭት ይናገራሉ፡፡

በተለይም አንዳንድ አገሮች እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ጠንካራ የሙስና መከላከል ሥርዓት ካልዘረጉ ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ ለመቆጣጠር እንደሚቸገሩ፣ ከእዚያም አልፎ ወረርሽኙ የሙስና መፈልፈያ (An Incubator to Corruption) ሆኖ ሊወጣ እንደሚችል ያሳስባሉ፡፡ ከተከሰተ በኋላ ለመቆጣጠር መሞከር ለአላስፈላጊ ወጪ ከማድረግ ውጪ ጥቅም እንደሌለው ምሁራን ያወሳሉ፡፡ በመሆኑም ከወረርሽኝ  ጎን ለጎን የቁጥጥር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ማጠናከር የግድ የሚል ጉዳይ መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻሉ፡፡

እንግዲህ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና ዜጎች ከሞት ጋር በሚተናነቁበት ጊዜ፣ ለሕክምና የተመደበውን በጀት የሚዘርፍ፣ ሌሎች ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያመቻች፣ ቫይረሱን ለመከላከል ተብለው በአገር ደረጃ የወጡትን ሕጎችን የሚጥስ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ችላ ብሎ ወደ ዘረፋ፣ ስርቆትና እምነት ማጉደል የሚገቡ፣ መንግሥት ትኩረቱ ወረርሸኙን ላይ አድርጓል ብለው የድርሻዬን ልውሰድ የሚሉ ምግባረ ብልሹ ሰዎች አይጠፉምና መጠንቀቁ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋማት  ከወዲሁ ሊከሰት የሚችለውን ሙስና ትኩረት እንዲሰጡበትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በተለያዩ አገሮች እየታዩ ያሉ የሙስና ድርጊቶች ማውሳት፣ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ዕድል ይፈጥራል ብዬ አስባለሁኝ፡፡

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ባወጣው መረጃ ባለፈው ዓመትና ከእዚያ ቀደም ብሎ በጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ወደ 11,000 ሰዎች ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከፍ እንዲል ያደረገው ሳይታወቅ በውስጥ ለውስጥ የተፈጸመ ሙስና ሙሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ ለዚህ ማሳያ ያነሳው በወቅቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ከተመደበው በጀት ውስጥ ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የዕርዳታ ገንዘብ በሐሰት በተዘጋጀ የጉምሩክ ቀረጥ፣ በተጋነነ የግዥ ዋጋ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ያልነበሩ የጤና ሠራተኞችን በሥራ ላይ እንደነበሩ አስመስሎ በተከፈለ ክፍያ (Ghost Employee Payement)  መሠረት መሆኑን፣ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ የማኅበሩ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ወረርሽኝ በተከሰተ ቁጥር ሙስና ለመፈጸም አመቺ መሆኑን ባለሙያዎቹ አውስተዋል፡፡ ኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላም እየታየ ያለው ጉዳይ ከኢቦላ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በጤና ዘርፍ ያለውን ሙስና ጥናት ያደረጉ ምሁራን በቅርብ ጊዜ የተከሰተውን ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና እስያ አገሮች የሚገኙ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ጤና ምርመራ ለማድረግ (Access to Testing and Treatment) ገንዘብ እንዲከፍሉ እንደሚገደዱ ገልጸው፣ ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ወይም ጉቦ ለመክፈል አቅም ያነሳቸው ዜጎች ምርመራ ለማድረግ እንደሚከለከሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሥርጭቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው አቢጋል ቤለውስ የተባሉ አሜሪካዋ ብሎገር ባወጡት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡

እንድያውም ይላሉ ምሁሩ ቫይረሱን ለመካለከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማግኘት በጣም ሰፊ የሆነ ግዥ እየተፈጸመ ባለበት ወቅት፣ እንደ ኬንያ የመሳሰሉ አገሮች በቀላሉ የመንግሥት በጀት ወደ ግለሰብ ካዝና የመግባት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን አውስተዋል፡፡ የትራምፕ አሰተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮሮናን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች እንዲውል 37 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሰጠ ሲሆን፣ ከሙስና በፀዳ መንገድ ለታቀደለት ዓለማ እንዲውል ዕርዳታ ለሰጣቸው አገሮች ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ይኼን የሚያሳየው ኮሮናን ሰበብ በማድረግ ሊፈጸም የሚችል ሙስና ሊኖር እንሚችል መገመቱን ነው፡፡ በኢራቅና በአልጄሪያ ሙስናን ለማውገዝ ለሳምንታት እየተደረጉ የነበሩ ሠልፎች ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በመሥጋት ለጊዜው ቢቆሙም፣  አሁን ያለው መንግሥት እየፈጸመ ያለው ሙስና ከኮሮና የባሰ የአገራችን በሽታ ነው የሚል መፈክር ይዘው ወጥተዋል፡፡

ስሎቬኒያ ቫይሩሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለሟሟላት የሚውል አሰቸካይ የ80 ሚልዮን ዩሮ በጀት የመደበች ሲሆን፣ ከግልጽ ጨረታ ውጪ በሆነ መንገድ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ብዙ ግዥ ፈጽማለች፡፡ የተፈጸመው ግዥ ግን ከሙስና መረብ ሊያልጥ አልቻለም፡፡ የአገሪቱ ባለሥልጣን በቁማር በኤሌክትሮኒክስና በሪል ስቴት ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር የፈጸሙት ወንጀል መሆኑን የአገሪቱ ሚዲያ አጋልጧል፡፡ ሕዝቡ ባሰማው ከፍተኛ ቁጣና ጫና መሠረት የተቀሩት ግዥዎች በአገሪቱ (Agency for Commodity Reserves) በሚባል ተቋም ብቻ እንዲፈጸም መንግሥት አዟል፡፡

የአሜሪካ የትራምፕ አስተዳደር ኢኮኖሚውን ከውድቀት ለመታደግ 2.2 ትሪሊዮን ዶላር የመደበ ሲሆን፣ ከዚህ ውሰጥ 500 ቢሊዮን ዶላር ለትልልቅ ኩባንያዎችና ኮርፖሬሽኖች በድጋፍ መልክ እንዲሰጥ ወስኗል፡፡ የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ውሳኔው በተዘዋዋሪ የፕሬዚዳንቱና የቤተሰቦቻቸው ኩባንያዎች ማበልፀጊያ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ያነሱ ምሁራን ቀላል አይደሉም፡፡ የፀደቀውን 2.2 ትሪሊዮን ዶላር የመታደጊያ በጀት ወጪን በአግባቡ የሚከታተል ኮሚቴ እንዲቋቋም ከአንዳንድ የኮንግረስ አባላት የቀረበውን ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ውድቅ ማድረጋቸው፣ ምናልባትም በቀጣይ ዓመት የሚካሄድን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባለፀጋ ደጋፊዎቻቸው እንዲያግዟቸው ለመጥቀም በረቀቀ መንገድ ሆን ተብሎ የተመቻቸ አካሄድ ሊሆን እንደሚችል  ሥጋታቸው የገለጹ ምሁራን አሉ፡፡

በቻይና መንግሥት ድጋፍ ለጣሊያን የተላኩትን 28,000 ቬንትሌተሮችና 680,000 የአፍ መሸፈኛዎች አንድ ቻይናዊ ግለሰብ ከቼክ ሪፐብሊክ ባለሥልጣናት ጋር በፈጠረው ሕገወጥ ትስስር መሠረት፣ አየር በአየር በሁለት እጥፍ ዋጋ ለመሸጥ ሲደራደር በአገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል፡፡ ከዚህ ማየት የሚቻለው ሙሰኞች ራሳቸውን ለማበልፀግ ማንኛውንም ጊዜ፣ ቀዳዳና ዕድል እንደሚጠቀሙ ነው፡፡

በተመሳሳይ በአፍሪካም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከቫይረሱ ባልተናነሰ ሁኔታ ሙስና ራሱ ወረርሽኝ ሆኗል በማለት የሚወጡ መረጃዎች ቀላል አይደሉም፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብዓቶች ለሟሟላት መንግሥት የግዥ ሕጉና ቁጥጥሩ ሆን ብሎ እንዲላላ እያደረገ ነው፡፡ ቫይረሱ እንዲስፋፋ ሙስና የራሱን አሰተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ድሮም በጣም ለሙስና ተጋላጭ የነበረውን የአገሪቱ የጤና ሴክተር የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል ብሎ አንድ የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ ለዚህ በማሳያነት የቀረበው እ.ኤ.አ. በ2019 ብቻ በጤና ሴክተሩ ወደ 100 የሚጠጉ የሙስና ጥቆማዎች መቅረባቸውን ያወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውኃ ለማቅረብ ቀደም ሲል ሲሠሩ የነበሩ ፕሮጀክቶች የሙስና ሰለባ በመሆናቸው በአሁኑ ሰዓት ወረርሽኙን ለመከላከል የውኃ እጥረት ማጋጠሙን (Anti-corruption Wachdog) የተባለውን የአገሪቱ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አጋልጠዋል፡፡ 

በኒጀርም ይኼን የኮሮና ቫይረስ በሽታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ አጋጣሚ በመቀጠም በአገሪቱ የነበሩ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች 232 ሕፃናትና ሴቶች በሕገወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በእጃቸው የገቡትን ሕፃናትና  ሴቶች  በአንድ ትንሽ ቤት እንዲቀመጡ በማድረጋቸው፣ ለኮሮናና ለሌሎች ቫይረሶች መጋለጣቸውን የአገሪቱ ሚዲያ በሐዘን አስነብቧል፡፡

ይኼንን ቀውስ መልካም ዕድል አድርገው የሚወስዱት ሙስና ለመፈጸም ያሰቡ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ቀደም ሲል በሙስና ተከሰው የፍርድ ሒደታቸው ያለቀ ወይም በፍርድ ሒደት ላይ  እያሉ ለጊዜው እንዲለቀቁ ወይም ዕፎይታ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ ቀውሱን እንደ ዕድል ወስደውታል፡፡ ለምሳሌ እንኳ ብናይ በእንግሊዝ በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩ የሦስት ኢንዱስትሪ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች የፍርድ ቤት ክርክር ሳያልቅ ለጊዜው እንዲቋረጥ ወይም እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ የሙስና ቅሌት ፈጽመዋል ተብለው ስማቸው በሚዲያ ሲብጠለጠሉ የነበሩ የትንሽዋ አገር እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በንጃሚን ኔታናያሁ፣ ቫይረሱ ያስከተለውን ተፅዕኖ ለመከታተል ሲባል የክስ ሒደታቸው  እስከ ግንቦት ድረስ እንዲራዘም የአገሪቱ ፍትሕ ቢሮ ወስኗል፡፡

ታዲያ ይኼንን ዕድል እንደ ሎተሪ የቆመሩት የቤንጃሚን ኔታናያሁ ተቋሚዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ መረዳት የሚቻለው አገሮች ይኼንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ሙስናን መቆጣጠር ካልቻሉ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች መና ሊያስቀር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡  

ኮሮና ሙስናን በአገራችን ለማስፋፋት ያለው ዕድል

አገራችን ኢትዮጵያ ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊት ለቅድመ መከላከል ሥራ 500 ሚሊዮን ብር መድባ የነበረች ሲሆን፣ ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ ያስከለተውን ጫናና በኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በማየት የተመደበውን በጀት ወደ 29 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል አድርጋለች፡፡ የተመደበውን በጀት መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ እንዳይጎዳ ለብሔራዊ ባንክ የመደበውን የማነቃቂያ በጀት፣ እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት ቫይረሱን ለመካከል የሚረዱ እንደ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ሳሙና፣ ሶፍት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ግብዓቶ ለሟሟላት በራሳቸው በጀት የሚያጧቸውን ወጪዎች አይጨምርም፡፡ ከዚህ ቫይረሱን ለመከላከል ከፍተኛ በጀት የተመደበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ግብዓቶች ለሟሟላት ሥራው ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመምጣቱ መንግሥት ለዚህ ሥራ ተጨማሪ በጀት እንዲመድብ አስገድዶታል፡፡ በተለይም ግብዓቶችን ለሟሟላት የሚካሄዱ ግዥዎች በተፈጥሮአቸው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው፣ የግዥ ሒደቱ ጨርሶ ወደ አገር እስኪገቡ ድረስ የሚወስደውን ታሳቢ ሲደረግ መንግሥት ከአንድ አካል ብቻ በቀጥታ ግዥ ሊፈጸም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ አሰቸጋሪ ወቅት የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን ትቶ በወንድሞቹና በእህቶቹ ሕይወት የሚቀልድ ሰው አይጠፋም፡፡ በማስረጃ ባይረጋገጥም ከአንዳንድ ሰዎች የሰማሁት መረጃ እንደሆነ፣ ፖሊሶች ከውጭ መጥተው ለ14 ቀናት ማቆያ (ኳራንቲን)  እንዲገቡ ከተደረጉ ሰዎች መካከል ገንዘብ በመቀበል እንዲወጡ ሙከራ ያደረጉ እንዳሉ ነው፡፡ ይኼ ተፈጽሞ ከሆነ በእውነት በጣም አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል እንዲውሉ እንደ ሳኒታይዘር፣ አልኮሆል፣ ሳሙናን ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶች ግዥ ምን ያህል ከሙስናና ከመመሳጣር በፀዳ መንገድ ግዥ እንደተፈጸመ ሁላችንም እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ከጤናው ሴክተር ወጣ ስንልም ከመሬት፣ ከገበያ ዋጋ  ጭማሪ፣ ከዶላር ወደ ውጭ አገር መሸሽ (Illicit Financial Flow)፣ ከኮንስትራክሽንና ከሌሎች ትልልቅ ግዥና ሽያጮች የመሳሰሉ ሴክተሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ለሙስና የተጋለጡ ናቸው፡፡ አገሪቱ ካለችበት ችግር አንፃር ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን፣ ይኼንን አጋጣሚ በመጠቀም የሙስና ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ጥበቅ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ወረርሽኙን ተከትሎ ሙስና እንዳይፈጸም ምን ይደረግ?

ከላይ እንደገለጽኩ ይኼን አስቸጋሪ ወቅት ተጠቅመው አይደረስብንም በሚል እምነት ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቡድኖች ወይም ግለሰዎች ወደ ሙስና አይገቡም፣ የግል ጥቅማቸውን አያስቀድሙም ብሎ በድፍረት መናገር ከባድ ነው፡፡ እነዚህ ከሕዝብ ጤንነት ይልቅ ለራሳቸው ጤንነትና ምቾት ቅድሚያ የሚሰጡ ግለሰቦች ሲኖሩ፣ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ በተለይም በነበረው የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለውን ጫና ስንገነዘብ፣ የተመደበውን የሕዝብ ሀብት እጅግ በጥንቃቄ፣ ከሙስና በፀዳና ግልጽነት በተሞላበት አኳኋን ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ምናልባትም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሕግ አስከብራለሁ ብሎ የሰጠው መገለጫ ከዚህ የመነጫ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የሚበልጥ ታሪካዊ ኃላፊነት የለብንም፡፡ በመሆኑም በወረርሽኙ ምክንያቱት ሊከሰቱ የሚችሉ ሙስናዎችን ለመከላከል እንዲቻል፣ የሚከተሉት አካላት ተገቢ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሚና

እንደ አገር የተመደበውን በጀት ለምን ጉዳይ ይውላል ብሎ በዝርዝር ያፀደቀው አካል ተፈጻሚነቱን በእዚያው ልክ የመከታተል ትልቅ ኃላፊነት ያለው አካል በመሆኑ፣ በጀቱ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ለምን አግባብና ዓላማ ለማዋል እንደታሳበ፣ ሥራው ሲከናወን ሒደቱን ምን ነበረ? በዚህ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የሙስና ሥጋቶች ምን ነበሩ? ብሎ ብሎ በጥልቅ መገምግም አለበት፡፡ አስፈላጊ ከሆነም በጀቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ  እየዋለ መሆኑን አለመሆን የሚከታተል ገለልተኛ ንዑስ ኮሚቴ በማቋቋም፣ በሕዝብ ዘንድ መተማመን መፍጠር ቀዳሚ ሥራው ሊሆን ይገባል፡፡ በተወሰነ ጊዜ አፈጻጸሙንና የተወሰደውን ዕርምጃ ካለም ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የተቆጣጣሪ አካላት ሚና

 ተቆጣጣሪ አካላት ዋና ኃላፊነታቸው የተመደበውን በጀት የፋይናንስ አስተዳደሩና ወጪው ምን ይመስላል? ሕግ የተከተለ ነው አይደለም? ብለው የሚቆጣጠሩ የመንግሥት አካላት እንደ መሆናቸው መጠን የተመደበውን በጀት በትክክል አስተባባሪ ኮሚቴው ባፀደቀው አግባብ ሥራ ላይ መዋሉንና የወጪ ሥርዓቱ ጤናማ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ከመንግሥትና ከለጋሽ አካላት የተመደበን በጀት ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማስተዳደርና መሟላት የሚገባቸው ጊዝያዊ መመርያዎችና ማኑዋሎች ካሉ በመለየትና በአስተባባሪ ኮሚቴ በማፀደቅ፣ በጀቱ ለተፈለገለት ዓለማ መዋሉን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ይኼን ለማረጋገጥ ከሕዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት አለባቸው፡፡ የፀረ ሙስና ተቋማትም ከሕዝብ የሚመጣውን ጥቆማ ቅድሚያ ለዚህ በመስጠት ማጣራትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

የሕዝቡ ሚና

የተመደበውን በጀት በግብር መልክ የከፈለውን፣ የራሱ ሀብትና ለተገቢ ዓለማ መዋሉን ማረጋገጥ ያለበት መጀመርያ ራሱ ሕዝቡ በመሆኑ በበጀቱ አቅርቦትና አሰተዳደር፣ በተለይም ሕዝቡ በሚገለገልባቸው የጤና ተቋማትና የመንግሥት መዋቅሮች የሙስና ዝንባሌዎች ሲከሰቱ ለሚመለከታቸው አካላት ሊያጋልጡ ይገባል፡፡ ከጤና ሴክተር ውጪ ባሉ ተቋማት ሙስና ሲከሰትም በዛው ልክ ለሚመለከታቸው አካላት ማጋለጥ አለባቸው፡፡

ጉዳዩን ለማጠቃለል ያህል እንዲህ ዓይነት የወረርሽኝ ቀውስ በሚያጋጥምበት ወቅት፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ብሔራዊ ጀግንነትና ቁርጠኝነት የሚይጠይቅ በመሆኑ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ አገራችንን እየተፈታተኗት የሚገኙትን ሁለቱንም አደገኛ ቫይረሶች (ኮሮናና ሙስና) ለመከላከል፣ አገራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣ እላለሁኝ፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር አውታሮች ማስተባሪያ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...