Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቁጣው ይብረድልን!

ጉዞ ከፒያሳ ወደ ቄራ ለመጀመር እየተንጠባጠብን ሚኒ ባስ ታክሲ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ዘመኑ ከፍቶ ከማይታገሉት ባላጋራ ጋር ግብግብ ቢያጋጥመውም፣ የሰው ልጅ ነግቶ እስኪመሽ ድረስ መንቀሳቀሱን አላቆመም፡፡ አየሩን ያለ ከልካይ በነፃ ከሚምጉ ብዙኃን፣ አፋቸውን በእራፊ ጨርቅ ከለጎሙ ምስኪኖችና በኅብረ ቀለማት ባጌጡ ጭምብሎች ከደመቁ የፋሽን ተከታዮች ድረስ ጎዳናው በማይታክቱ ነፍሶች አሁንም እንደተሞላ ነው፡፡ ኮሮና የሀብታሞች የቅንጦት በሽታ የሚመስላቸው ዝንጉዎች፣ ሺሕ ዓመት አይኖር እያሉ ዓለምን የናቁ፣ እንዲሁም ቁጣ ከበስተጀርባቸው የሚያሳድዳቸው የሚመስሉ እርብትቦቶችና ዙሪያ ገባውን በትኩረትና በጥንቃቄ እየቃኙ የሚራመዱ ብልሆች ድረስ ጎዳናውን ተጋርተውታል፡፡ ከዕለት ጉርስ ፈላጊው እስከ ሀብት ፈጣሪው በተሰማራበት መስክ የሚፈልገውን ለማግኘት ይጣደፋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ምፅዋት ፈላጊውና ዘራፊውም ከሠርቶ በሌው እኩል ጎዳናው ላይ ፈሰዋል፡፡ በአዲሱ ሕግ መሠረት ስድስት ተሳፋሪዎች ጭኖ መነሳት ያለበት የታክሲያችን ወያላ ታሪፍ እጥፍ ቢደረግለትም ደራርቦ ሊጭነን ፈልጎ ነው መሰል፣ ‹‹አንድ ሰው የቀረ. . .›› እያለ ይጮኻል፡፡ ሾፌሩ ግን፣ ‹‹ወይ ልማድ ሞላ እኮ በሩን ዝጋና እንሂድ. . .›› ሲለው እየከፋው ገብቶ በሩን ዘጋ፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ከሾፌሩ ጀርባ ያለው ወንበር ላይ የተሰየመች እግዜር እጁን ታጥቦ የሠራት የምትመስል ልዕልት የመሰለች ውብ ቆንጆ፣ ‹‹እንደለመድከው ለምን ደራርቤ አልጫንኩም ብለህ እንዳይሆን ያኮረፍከው. . .›› ብላ ወያላውን ወጋ ስታደርገው፣ ውበቷ ማርኮት ይሁን ወይም አነጋገሯ አስገርሞት ፍዝዝ ብሎ ዘለግ ላለ ጊዜ ተመለከታት፡፡ ‹‹ለምንድነው አፍጥጠህ የምታየኝ?›› ብላ ኮስተር ስትልበት፣ ‹‹አንቺን ከመሰለች የብርሃን ፀዳል እንዲህ ያለ ንግግር አልጠበቅኩም ነበር. . .›› እያለ ሲያጉተመትም መሀል ወንበር የተቀመጠ ጠረንገሎ ጎረምሳ፣ ‹‹አሁን በዚህ ጊዜ ስለውበት ሳይሆን ስለሥነ ምግባር ነው መወራት ያለበት. . .›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ወንድሜ ከሥነ ምግባሩ በፊት እጅህን ታጥበሃል?›› አለው፡፡ ጎረምሳው ቶሎ ብሎ የገዛ መዳፎቹን ከፍ አድርጎ፣ ‹‹አሁን እጄ ምን ይወጣለታል?›› እያለ ሲያሳየው፣ ‹‹ወዳጄ እጅህ ውስጥ ያለውን ጀርም ማይክሮስኮፕ እንጂ ዓይኔ አያሳየኝም. . .›› ብሎ ወያላው ሲመልስለት ፈገግ አስደረገን፡፡ ውቢት ጊዜ ሳታጠፋ፣ ‹‹ታክሲውን ለምን መጠቅጠቅ አማረህ?›› ብላ ወደ ተጀመረው ጉዳይ ስትመልሰው፣ ‹‹የእኔ ቆንጆ መጠቅጠቅ ሳይሆን ያማረኝ፣ ለአንድ ወር የሚበላ ባገኝ በሬን ዘግቼ መደበቅ ነው ፍላጎቴ. . .›› እያለ ዓይኑን ሲያንከራትትባት ሾፌሩ ሳቁን ለቀቀው፡፡ ከሳቁ አይቀር እንዲህ ነው ያሰኝ ነበር!

ወያላው ወደፊት እያንጋጠጠ ሾፌሩን፣ ‹‹ጥርስህ ይርገፍ እንዳልል ስምንቱን ጫት ረፍርፎታል. . .›› ሲለው፣ ‹‹አንተ አለህ አይደል እንዴ ጢምቢራህ እየዞረ ስትንደባለል ፊትህን የተረበሸ ጠጅ ቤት ያስመሰልከው. . .›› ብሎ በመልስ ምት ሲያቀምሰው፣ እነዚህ ሰዎች ዓለምን የናቁ ይመስሉ ነበር፡፡ ጎረምሳው አሁንም ሲንቀዠቀዥ መሀላቸው ገብቶ፣ ‹‹ለካ ከጫትና ለጠጅ ላይ እየተነሳችሁ ነው አቅላችንን የምታስቱት…›› ብሎ ወግ መጠረቅ ሊጀምር ሲቃጣው ወያላው በተለመደ ፍጥነቱ፣ ‹‹ስትንከረፈፍ ለሚደርስብህ ጉዳት ኃላፊነቱ የአንተ ነው እንጂ የእኛ እኮ አይደለም. . .›› እያለ ሲስቅበት ሾፌሩ ደግሞ በሻካራ አንደበቱ፣ ‹‹ጀለስ በፀሎትና በምህላ ጊዜ ለምን ክፉ ታናግረናለህ?›› ብሎ በኋላ መመልከቻ መስተዋቱ አጨንቁሮ ሲያየው፣ ውቢት ከሳቋ ጋር እየታገለች በኃፍረት ውጭውን ማየት ጀመረች፡፡ ወያላና ሾፌር እየተጠቃቀሱ ነገር መቆስቀሳቸውን ሲቀጥሉ ጎረምሳው ጭልጥ ያለ ትካዜ ውስጥ ገብቶ ቀረ፡፡ ከማይችሉት ባላጋራ ጋር ንትርክ የከበደው መሰለ፡፡ ‹አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው› የተባለው መቼ ይሆን ያሰኛል!

ታክሲያችን ቡናና ሻይ ባለሥልጣንን አልፎ የቄራን መንገድ ሲይዝ ፌርማታው ላይ የሰው ጎርፍ ያዩ ፀጥ ብለው ኋላ ወንበር የተቀመጡ አንድ አዛውንት፣ ‹‹ሰው ቤትህ አድብ ሲባል ብሶበት ጎዳናው ላይ ይተፋፈጋል እንዴ?›› ብለው ሲበሳጩ ሾፌሩ፣ ‹‹ፋዘር አይግረምዎት! የእኛ ሰው ኑሮ ቢመቸው ኖሮ ቤት መቀመጥ መቼ ይጠላ ነበር? ድህነት ነው እንደ አሸዋ ጎዳና ላይ ዘርግፎት ለቁራሽ እንጀራ የሚያሯሩጠው. . .›› ሲላቸው፣ ‹‹ወይድ! ድህነት እያልክ ሰበብ አትፈልግ. . .›› አሉት፡፡ ወያላው ወደ አዛውንቱ እያማተረ፣ ‹‹ፋዘር በዘመነ ኮሮና ድህነት ባይኖር ኖሮ እኔም እኮ ይህችን የመሰለች ውብ እቅፍ አድርጌ ከቤቴ አልወጣም ነበር. . .›› ብሎ ልቡ ውስጥ የደበቀውን ሲነግራቸው አዛውንቱ ከት ብለው ስቀው፣ ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ማለት አንተ ነህ፡፡ ፍጡር የሚባል የሕይወት ጉዳይ የሞትና የሽረት ሆኖበት አንተ ግን. . .›› ብለው ተውት፡፡ ‹‹ኧረ ፋዘር የጀመሩትን ይጨርሱት. . .›› ሲላቸው ሾፌሩ፣ ‹‹ለአዋቂ አንድ ቃል በቂ ነው›› ብለው ዘጉት፡፡ እውነት ነው!

ታክሲያችንን በረሃ የመሰለውን የድሮውን ቡልጋሪያ ሲያቋርጥ፣ ሁላችንም በፀጥታ ተውጠን በየልቦናችን ከሐሳባችን ጋር የምንሟገት እንመስል ነበር፡፡ በዚህ መሀል ውቢት ስልኳ በሞዛርት የሲንፎኒ ሙዚቃ አንሺኝ እያለ ሲጮህ የሁላችንም ጆሮ ተርገበገበ፡፡ ውቢት በቄንጠኛ አያያዝ የስልኳን ስክሪን ዓየት አድርጋ በውብ ቅላፄ፣ ‹‹ሃ. . .ይ. . .›› ስትል ከባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አንደኛው የእንግሊዝ ልዑል የደወለላት ትመስል ነበር፡፡ በጣም ዝቅ ባለና እንደ ማስቲካ በሚለጠጥ የአነጋገር ዘዬ ስትነጋገር የምትለው ሁሉ በኮድ የተቆለፈ እንጂ፣ ፈፅሞ በአማርኛ የምትነጋገር ነበረች ለማለት ይከብዳል፡፡ ወያላው በመገረም ካያት በኋላ ፊቱን ወደ ተሳፋሪዎች መለስ አድርጎ፣ ‹‹ይህች ውብ ፅጌረዳ ፍርድ ቤት ብትቀርብና ብትናገር እርግጠኛ ነኝ ዳኛው ንግግሯ ተተርጉሞ ይምጣልኝ ነው የሚሉት. . .›› እያለ ሲስቅ ጎረምሳው ጭልጥ ብሎ ከሄደበት ተመልሶ ነው መሰል፣ ‹‹አንተስ ምን ትል ነበር?›› ብሎ ሲጠይቀው ለአፍታ እንኳ ሳያስብ፣ ‹‹እኔማ እገድልሃለሁ ብትለኝም እሺ ነው የምለው. . .›› ከማለቱ አዛውንቱ አተኩረው እያዩት፣ ‹አንተስ ልክፍት ነው የያዘህ. . .› አሉት፡፡ ምን ይበሉት ታዲያ!

ውቢት በኮድ የታሰረውን የስልክ ወሬዋን ጨርሳ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ ምን አድርጊ ነው የምትለኝ?›› ብላ ወደ ወያላው የጥያቄ ሮኬት ስታስወነጭፍ፣ ‹‹ምንም አይደለም፣ የምስኪን ሰው የፍቅር አቤቱታ ነው. . .›› ሲላት እኔ አላምንም በሚል ስሜት ከትከት ብላ ሳቀች፡፡ ምስኪን መሳዩ ወያላ፣ ‹‹ምነው የእኔ እመቤት?›› ብሎ ሲለሳለስ፣ ‹‹ሰሞኑን ኮሮና አለ ተብሎ የተቀለደውን አልሰማህም?›› ስትል እንኳንስ ወያላው የሁሉም ተሳፋሪዎች ጆሮዎች ቀልዱን ለመስማት አቆበቆቡ፡፡ ይህን ጊዜ አዛውንቱ፣ ‹‹ወይ ግሩም ኮሮና በፀጥታ የአዳምን ዘር መፍጀቱን ትቶ ወሬ ጀመረ ነው ያልሽው ልጄ? ወይስ ጆሮዬ ነው?›› ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡላት፣ ‹‹አባቴ ከፍጅቱ ጎን ለጎን የእኛ ነገር ቢገርመው ነው በመሀል ወሬ ሲሰልቅ የነበረው. . .›› ብላ ስትስቅ ልባችንን አንጠለጠለችው፡፡ አዛውንቱ በዋዛ የሚላቀቁ አይመስሉም፣ ‹‹ጭራሽ ወሬ የጀመረው እዚህ እኛ አገር ነው እያልሽኝ ነው?›› ብለው እንደ ገና ሲያጣሩ፣ ‹‹አዎን አባቴ. . .›› ከማለቷ፣ ‹‹በይ እንስማሻ. . .›› አሉ፡፡ ዕድሜ ለጆሮ መስማታችንን ቀጠልን፡፡

ቆንጂት የሁላችንንም ቀልብ መሰብሰቧን ካረጋገጠች በኋላ፣ ‹‹አጅሬ ኮሮና በየአገሩ እየዞረ ሥራውን ሲያከናውን እኛ ጋ መድረሱን መቼም የማያውቅ የለም. . .›› ብላ ቀና ብላ ስታይ ጎረምሳው፣ ‹‹በየቀኑ ዜና እየሰማን አይደል እንዴ?›› ከማለቱ ወያላው እንደለመደው፣ ‹‹ማሬ እየቀረጠፈን እኮ ነው. . .›› ሲላት፣ ‹‹እንዳንተ ዓይነት አጉል ደፋሮችን ዓይቶ እኮ ነው ገጠመኙ አልጄዚራ ላይ የተወራው. . .›› ብላ በሳቅ ስትንፈቀፈቅ አዛውንቱ ደንግጠው፣ ‹‹ጭራሽ አልጄዚራ. . .›› እያሉ ሲገረሙ የሾፌሩ ሳቅ ቄራ ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ ‹‹እናላችሁ አጅሬ ኮሮና ቀብረር ብሎ እነዚህ የዓድዋ ጀግኖች የልጅ ልጆች እንዴት እየሆኑ ነው እያለ መገናኛ ሲደርስ፣ የሕዝቡ ብዛት አስደንግጦት ርቀቱን እንኳ አላስጠብቅ ስላለው ወደ ሾላ በሩጫ አፈተለከ፡፡ ሾላ ሲደርስ ለሌዲ ጋጋ የሙዚቃ ኮንሰርት የሚተሙ ሙዚቃ አፍቃሪዎች መሀል የገባ መስሎት በርግጎ የሸሸ ራሱን መርካቶ መሀል አገኘው፡፡ እዚህ ደግሞ የአገሬው ንጉሥ ለጦርነት የሚያዘምቱት ሠራዊት መስሎ ሲያየው በድንጋጤ ደንብሮ ጃንሜዳ ደረሰ. . .›› ብላ ቀና ብላ ስታይ ሁሉም አፋቸውን ከፍተው ያዳምጧታል፡፡ ተናጋሪ ይኑር እንጂ ለማዳመጥ ምን ይቸግራል!

‹‹አትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ በመዛወሩ ምክንያት በሰሞነ ትንሳዔ የጥምቀት በዓል ድባብ የሚታይበት የመሰለው ጃንሜዳ የደረሰው ኮሮና፣ በየትም ሥፍራ ያላጋጠመው የሕዝብ ብዛት ሲያጋጥመው ልቡ ቀጥ አለችበት. . .›› እያለች ስትስቅ የብዙዎች ልብ ቀጥ ያለች ትመስል ነበር፡፡ አዛውንቱ ቀልዱ እውነት የሆነ ያህል ተሰምቷቸው፣ ‹‹አሁን መቼ ዕለት ነው አትክልት ልሸምት ሄጄ እንዴት እንዳስደነገጠኝ አትጠይቁኝ፡፡ እንኳንስ ኮሮና እንግዳው የእኔም ልብ ቀጥ ብላ ነበር. . .›› እያሉ ሲነግሩን ሾፌሩ በዚያ አቯፊ ሳቁ እየተመራ፣ ‹‹ፋዘር የእርስዎ ድንጋጤ ተጋብቶብኝ እኔም ልቤ ቀጥ ልትል ነው. . .›› ሲላቸው፣ ‹‹ግዴለም አሹፍ ከጎንህ ታገኘዋለህ. . .›› አሉት፡፡ ወያላው የውቢት ትረካ ጥሞት ኖሮ፣ ‹‹እባክሽ መጨረሻው ምን ሆነ?›› ብሎ በዓይኑ ጭምር ሲለማመጣት፣ ‹‹መጨረሻውንማ እናገራለሁ፣ ግን አንተ እና ቢጤዎችህ የሚነገራችሁን ምክር ለምንድነው የማትሰሙት?›› ስትለው፣ ‹‹እንዳንቺ ዓይነት ፈትፍቶ የሚያጎርስ ስለጠፋ ነው. . .›› ብሎ ሲያሳስቃት እኛም አብረን ሳቅን፡፡ እንሳቀው እንጂ!

‹‹አጅሬ ኮሮና ጃልሜዳ ልቡ ቀጥ ብላ ውኃ ደፋፍተውበት ቀና ሲል በርካቶች ዙሪያውን ከበው ያዩታል፡፡ የሰዎቹ ድፍረት ገርሞት ነው መሰል አንገቱን በኃፍረት ደፋ ሲያደርግ. . .›› እያለች ልትቀጥል ስትል አዛውንቱ፣ ‹‹እንዴ አልበዛም እንዴ?›› ሲሉ ወያላው፣ ‹‹ምኑ ነው የበዛው ፋዘር?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ሾፌሩ፣ ‹‹ቀደዳው ነዋ ፋራው. . .›› ከማለቱ ውቢት፣ ‹‹አንተም አልተባልክ ጅሉ. . .›› ብላ ወደ ትረካው ከመመለሷ በፊት ወያላው በደስታ ጭብጨባ ታክሲውን ድብልቅልቁን አወጣው፡፡  ውቢት ወያላውን በደስታ አስፈንድቃ ለአፍታ ቆይታ፣ ‹‹ኮሮና አንገቱን ደፍቶ ለደቂቃዎች ከቆየ በኋላ ቀና ሲል የጃንሜዳ አትክልት ሸማች እጥፍ በእጥፍ ቁጥሩ ጨምሮ ሲያየው ዓይኖቹ በፍርኃት ተንከራተቱ. . .›› በማለት ቀና ስትል፣ ግራ የተጋቡ ዓይኖቹ ላይዋ ላይ ይንከራተታሉ፡፡ ወያላው በስስት እያያት፣ ‹‹ከዚያስ የእኔ ቆንጆ?›› ሲላት፣ ‹‹ከዚያማ አጅሬ ኮሮና በድንጋጤ ተውጦ ዓይኖቹ እንባ እያቀረሩ ‹ብዙ አገሮች ሄጄ አይቻለሁ እንደዚህ የተናቅኩበት የለም፣ እንዲህ እንደተናናቅን አንከርማትም› ብሎ በንዴት ተንጨርጭሮ ዝቶ ሄደ. . .›› ብላ ቀልዷን እንዳበቃች አዛውንቱ በድንጋጤ ውስጥ ሆነው፣ ‹‹አቤተ አንተው ቁጣህን አብርድልን. . .›› እያሉ ሲማፀኑ ‹‹መጨረሻ›› ተብለን ወርደን ወደ ጉዳያችን ተበታተንን፡፡ ቁጣው ይብረድልን እንጂ አያያዛችን ያስፈራል፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት