Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ ለኮሮና ተጎጂዎች ዋስትና መስጠት ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኮሮና ቫይረስ ተጎጂዎችና ተጋላጮች የመድን ሽፋን ለመስጠት ሲዘጋጅ የቆየው ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ የጤናና ሕይወት ነክ ሽፋን ላላቸው ደንበኞቹ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የሕይወትም ሆነ የጤና ዕክል ወጪዎች የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኮሮና ቫይረስ ለሚጎዱ ደንበኞች የመድን ሽፋን ለመስጠት ከጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር ኒያላ ኢንሹራንሽ በመደራደርና ስምምነት በመፈጸም የመድን ሽፋኑ በጤና መድን ዋስትና ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ በመወሰን ወደ ትግበራ አስገብቶታል፡፡

በዚሁ መሠረት በኒያላ ኢንሹራንስ የጤናና ሕይወት ነክ የመድን ሽፋን ያለው ደንበኛ በውሉ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የመድን ሽፋን እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡ ይህም ደንበኛው በገባው የጤና መድን ሽፋን ልክ በኮሮና ቫይረስ ለሚያስፈልገው የሕክምና ወጪ፣ የሕልፈተ ሕይወትም ሆነ ተያያዥ ወጪዎች እንዲሸፈንለት ይደረጋል፡፡ በዚሁ ቫይረስ የተጠቃ ሰው በዓመት ለቤተሰቡ በጤና መድን ዋስትና ልክ ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኝ የሚደረግ መሆኑንም ከኒያላ ኢንሹራንስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኳራንቲን መግባትም አንዱ ኮሮና ቫይረስ የሕክምና መደብ ስለሆነ ሽፋኑ እንዲህ ያለውንም ያካትታል ተብሏል፡፡

አዲስ ደንበኞችም ይህንኑ ሽፋን እንዲያገኙ ዕድል ስለመመቻቸቱ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለሽፋኑ የሚጠየቀው የዓረቦን መጠንም መደበኛ የጤና መድን ሽፋን አገልግሎት አሰጣጥ መሠረት የሚፈጸም እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው በመንግሥት ለተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ትናንት ሚያዝያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ኩባንያው ያደረገውን የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በቼክ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ጥልቀትና ስፋት በመገምገም በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ከደንበኞቹ ጎን መቆምና አለኝታነቱን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት በጽኑ ያምናል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ስለዚሁ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ምንም እንኳ ደንበኞች ቀደም ሲል የገዙት የጤናና የሕይወት መድን ፖሊሲ በእንደዚህ ዓይነት ወረርሽኞች ምክንያት ለሚከሰቱ አደጋዎች ሽፋን ባይሰጥም፣ ኒያላ ኢንሹራንስ ግን ከዓለም አቀፍ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ከነባር ደንበኞቹ የካሳ ጥያቄ ቢቀርብ ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፡፡ በተጨማሪም ለአዳዲስ ደንበኞች ያለምንም ተጨማሪ የዓረቦን ክፍያ ለዚሁ በሽታ ሽፋን ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቀነስ በባለሙያዎች የሚቀርቡ እንደ ማኅበራዊ ፈቀቅታን የመሳሰሉ የጤና አጠባበቅ መመርያዎች ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማዋል ደንበኞች የዋስትና ውሎችን ለማደስ፣ አዳዲስ ውሎችን ለመግዛት፣ የካሳ ጥያቄ ለማቅረብ ወይም ማብራሪያ የሚፈልጉ ማናቸውም ዓይነት ጥያቄ ቢኖራቸው ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው ጥያቄዎቻቸው የሚስተናገዱበትን አሠራር ኩባንያው እንዳመቻቸ አስረድተዋል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በብሔራዊ ደረጃ ለተዋቀረው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ባደረገበት ወቅት፣ የኮሮና ቫይረስ የመድን ሽፋን መስጠት መጀመሩን በይፋ አስታውቋል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ ተግባራዊ ያደረገው ይህ የመድን ሽፋን በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ መስክ እንደ በሽታው ሁሉ አዲስ አገልግሎት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች