Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮሮናን ለመከላከል የሚገለግለው የፊት ጭምብል በኢትዮጵያ ቸል መባሉ ሥጋት ፈጥሯል 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮሮና ቫይረስ ጦስ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. ከ1929 እስከ 1932 ያለፈበትን አስከፊ ጊዜ እያስታወሰ ይገኛል፡፡ ‹‹ዘ ግሬት ዲፕሬሽን›› እየተባለ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚጠቀሰውና የሚታወሰው ይህ አስከፊ የኢኮኖሚ ድቀትና ውድቀት ዘመን የዓለምን ኃያላን ለረሃብና ቸነፈር ዳርጎ ያለፈ፣ በርካታ ትልልቅ አገሮችን ያሽመደመደመ ክስተት ነበር፡፡

ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ወይም ‹‹ዘ ግሬት ዲፕሬሽን›› እየተባለ የሚጠራው የዚያን ጊዜውን ቀውስ ከ90 ዓመታት ወዲህ ሌላ ታላቅ ቀውስ ቀስቅሶታል፡፡ ‹‹ታላቁ መዘጋት›› ልንለው የምንችለው ዓይነት መገለጫ የተሰጠው ‹‹ዘ ግሬት ሎክዳውን›› የተሰኘ ቀውስ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ዓለምን መናጥ ከጀመረ ሦስት ወራት አልፈዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተይዟል፡፡ 100 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በበሽታው ከፍተኛ የመዛመትና የመሠራጨት ሥጋት ምክንያት ዓለም በሯን ዘጋግታ ቀን እስኪያልፍ ትጠባበቃለች፡፡ ከዚህ ቀደም የወጡ የሁለት ወይም የሦስት ሳምንታት በቤት ውስጥ የመቀመጥ አስገዳጅ ሕጎች ዳግም እየተራዘሙ በበርካታ አገሮች የሚገኙ ቢሊዮኖች ሕዝቦች በበሽታ ፍራቻ ቤታቸው ውስጥ ለመመሸግ ተገደዋል፡፡ ከሰባት ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላዩ በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳይወሰን በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳይዛመት፣ ንክኪን የሚያስቀሩ፣ ጥግግትን የሚከለክሉ፣ አፍና አፍንጫ መሸፈንን የሚያስገደዱ፣ እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ፣ አልኮል ያለባቸውን ማፅጃዎች በመጠቀም ንፅህናን የሚያስጠብቁ ሕጎች በየአገሮቹ እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያም የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እነዚህ ዕርምጃዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡ አገሪቱ በከፊል ዝግ ተደርጋለች፡፡ አስገዳጅ ከሆኑ የምርት ሥራዎች፣ አስገዳጅ የሎጂስቲክስ፣ የጥሬ ዕቃ እንዲሁም የምግብ አቅርቦቶችንና መሰል ግብዓቶችን ከማመላለስ በቀር መሠረታዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ተቋርጧል፡፡ በሆነው መንገድ ወደ ከተማም ሆነ ወደ ገጠር መንቀሳቀስ ተገድቧል፡፡

ድንገት እንኳ የሚገባ ወይም የሚወጣ ሰው ቢኖር የጤና ማረጋገጫ ይለፍ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህን የሚያስፈጽም የአምስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በሥራ ላይ ነው፡፡ አዋጁ በአስገዳጅነት ከሚያስቀምጣቸው አንኳር አንኳር ክልከላዎች መካከል ሰዎች በርከት በሚሉባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማጥለቅ አንዱ ነው፡፡ ጭንብል ማጥለቅ እንደ መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባር ልማድ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ከአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አኳያ ዝቀተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በጃፓን፣ በኮሪያ እንዲሁም የኮቪድ-19 መነሻዋ ቻይና ሳይቀር የፊት ጭንብል የተመለደ በመሆኑ፣ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ሳይወጣ ለመከላከል አጋዥ ከሆኑት ዘዴዎች ይመደባል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2003 ተከስቶ በነበረው ሳርስ በሽታ በርካታ የሩቅ ምሥራቅ ዜጎች ዋጋ መክፈላቸው አሁን ላይ ላዳበሩት የፊት ጭንብል ልማድ ጠቅሟቸዋል የሚሉ ወገኖች፣ ተራ ጉንፋን ሲያገኛቸው ጭምር ጭንብላቸው ማድረጋቸው፣ በአየር ብክለት ሳቢያ የሚፈጠሩ የመተንፈሻና ሌሎችም በሽታዎችን ለመከላከል ጭንብል ማዘውተር በተለመደባቸው አገሮች ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝም ይህ ልማድ ባልዳበረባቸው አገሮች ካደረሰው ጉዳት በመለስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ጫና እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ በሽታው ከጤና ቀውስነት አልፎ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቅነቱ ከፍተኛ በመሆኑና ሁሉን አቀፍ ጥፋት ከማስከፈሉ በፊት በጊዜ ለመግታት፣ በጤና ሚኒስቴርና በሚመለከታቸው አካላት የሚቀርቡ የደኅንነት ማስጠበቂያ መመርያዎች ያለ ማቅማማት መተግበር እንዳለባቸው በየመስኩ እየተገለጸና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ አስቸኳይ አዋጁም የእጅ መጨባበጥን ጨምሮ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ የፊት ጭንብል ማጥለቅንና ሌሎችም መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ መመርያዎችን አስቀምጧል፡፡ 

የፊት መሸፈኛ ጭንብል እጥረት እንዳያጋጥም በአገር ውስጥ የሚገኙ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች መስፋት መጀመራቸው እየተነገረ ነው፡፡ እንደውም ከጎረቤት አገሮች ትዕዛዝ ተቀብለው ለውጭ ገበያ የሚውል የፊት ጭንብል በመስፋት ላይ እንደሚገኙ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ዓለም አቀፉ የበሽታ መካላከያና ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) በበኩሉ በፋብሪካና በጤና መጠበቂያ አምራቾች ብቻም ሳይሆን፣ በቤት ውስጥ በቀላሉ ከሚገኙ የጥጥ አልባሳት ቆርጦ በመስፋት የፊት መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም እንደሚቻል የሚመክር መመርያ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የጥግግት መመርያዎችንና ርቀትን የመጠበቅ ግዴታን ማክበር ቢቸግር እንኳ እነዚህ በቤት ውስጥ በቀላሉ ተሰፍተው የሚዘጋጁ ጭንብሎችን ማጥለቅ፣ የበሽታውን ሥርጭት በመግታት ዓለም ላይ እያሻቀበ የሚገኘውን ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ መቀነስ እንደሚቻል ይመክራል፡፡

በመሆኑም ከልባሽ ጨርቅ ተቆርጦ የሚወጡ ሁለት 25 በ15 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸውን የጥጥ ጨርቆች ከካኔቴራ አልያም ከሌላም ዓይነት ተለባሽ ጨርቅ በመቅደድና በግማሽ ሴንቲ ሜትር እጥፋት ምጣኔያቸውን አስተካክሎ፣ ዳርና ዳር የብር መያዣ ተለጣጭ ፕላስቲክ አልያም ተመሳሳዩን በማዘጋጀት አፍና አፍንጫን በቀላሉ መሸፈን እንደሚቻል፣ ባስፈለገ ጊዜም በሚገባ አጥቦ ዳግም መጠቀም እንደሚገባ ሲዲሲ ያወጣው ምክር አስፍሯል፡፡ ይህ አማራጭ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ማኅበራዊ ጥግግትን በቀላሉ ለማስቀረት ወይም እንዲተገበር የሚመከረውን የሁለት ሜትር ርቀትን የመጠበቅ ግዴታ ለማስተግበር ሲቸግር አማራጭ ከሆኑ መፍትሔዎች አንዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን መጠቀም ነው፡፡

እንዲህ ያሉ የጤና አጠባበቅ መመርያዎችን ማክበርና መተግበር ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆናቸውን የሚያመላክቱ አሳሳቢ የኢኮኖሚ ጫናዎችም በምሁራን እየቀረቡ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ይፋ ባደረገው ትንበያ መሠረት፣ የወረርሽኙ ሥርጭት ቢባባስና ኢትዮጵያም ሁሉንም እንቅስቃሴዎች የማገድ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ብትገባ፣ ከ200 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት አደጋ ሊያጋጥማት እንደሚችል አስታውቋል፡፡

መንግሥትና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ይፋ ባደረጉት መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደሚያድግ ከሚጠቀበቀው የዘጠኝ በመቶ ዕድገት ወደ ስድስት በመቶ እንዲቀንስ ኮሮና ከወዲሁ አስገድዶታል፡፡ ሕዝቡ የሚቀርቡለትን የጥንቃቄ መመርያዎች መተግበር ካልቻለ ተለዋዋጩ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ሳይታሰብ ከባድ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳስቡ ማስጠንቀቂያዎች እየጎረፉ ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም ለአስቸኳይ አዋጅ ማስፈጸሚያነት ያወጣው መመርያ እንዲተገበር እየተማፀነ ነው፡፡

ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት፣ ዘንድሮና በመጪው ዓመት ዓለም ዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እንደሚያጋጥማት የዓለም ገንዘብ ድርጅት ስሌቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ጠቅላላው የዓለም ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. በ2009 ካጋጠመው ከዜሮ በታች የነበረው ወይም ኔጋቲቭ የ0.1 በመቶ የዕድገት ዝቅጠት ይልቅ በዚህ ዓመት ወደ ኔጋቲቭ ሦስት በመቶ ያሻቀበ ከባድ ድቀት እንደሚያጋጥም አስጠንቅቋል፡፡ መረጃዎቹ በሙሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ድሆች አገሮች ይበልጥ ሥጋት የሚያሳድሩ በመሆናቸው፣ ቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ ላይ ያተኮሩ ዕርምጃዎች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ቀድመው መዘጋጀት የቻሉ አገሮች ከጤናውም ከኢኮኖሚውም ማዕበል የመዳን ዕድል እንዳለ አሳይተዋል፡፡ የበሽታው መነሻ ቻይና፣ በሠራችው የመከላከልና የጥንቃቄ ሥራ ከበሽታው ቀውስ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገግማ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት ብቻም ሳይሆን፣ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው አገሮችም ጭምር ተርፋለች፡፡ ኢትዮጵያም ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ መተርፍ እንድትችል የፊት ጭንብልን ጨምሮ መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ መመርያዎች በውዴታም በግዴታም ማስተግበር እንደሚጠበቅባት የሚያስጠነቅቁ በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች