በሰዎች ሕይወት ውስጥ መስጠትና መቀበል አንዱ የኑሮ አካል ነው፡፡ ሥጦታ ሰዎች በቅርበት እንዲተሳሰሩ ያደርጋል፡፡ ስጦታ ሰዎች እንዳይዘነጋጉ ምክንያት ነው፡፡ የእከሌ ስጦታ ነው ብሎ የተሰጡትን ዕቃ ማስቀመጥ፣ ዕቃውን ባዩ ቁጥር የሰጠውን ስም መጥራትም የተለመደ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከውልደቱ እስከ ሞቱ በስጦታ የታጀበ ነው፡፡ ይህ በሥጦታ የታጀበ የአኗኗር ዘይቤ፣ በተለይ በበዓላት ይጎላል፡፡
የትንሳዔ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቀዳሚው ነው፡፡ ከ55 ቀናት ፆም በኋላ የሚከበረው ትንሳዔ (ፋሲካ) በዓለማዊው ዕርድ የሚከናወንበት፣ ዳቦ የሚቆረስበት፣ ጠላና ጠጅ የሚንቆረቆርበት ነው፡፡ በፆምና በፀሎት የከረመው ምዕመን በቤቱ ደግሶ ከጎረቤትና ከዘመድ አዝማድ የሚቋደስበትም ነው፡፡ በዓሉ በእንዲህ ዓይነት በስፋት ተከብሮ ይዋል እንጂ፣ የበዓሉ ድምቀት በሁሉም ጓዳ የሚሞላ አይደለም፡፡
በችግር ውስጥ የሚኖሩ አቅመ ደካሞች፣ ነዳያንና ሕሙማን አዘውትሮ በተለይም በበዓላት ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ እንደ ዛሬው ኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያ ችግር ባልነበረባቸው ዓመታት፣ በየአካባቢው የተሰባሰቡ ወጣቶች ችግረኞችን ፆም ለማስፈታት ከብት አርደው፣ ሽንኩርትና ዘይት፣ በርበሬና ሌሎችንም አሟልተው በየአካባቢው በመዞር ለተቸገሩ ሲረዱ ማየቱ የተለመደ ነበር፡፡
ይህ ስጦታ በተለይ በአዲስ አበባ በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ የሚኖሩ ነዳያን የፋሲካ ሌሊት ፀሎት ቅዳሴ እንዳበቃ፣ መመገብ፣ አንገት ማስገቢያ ኖሯቸው ለጉርሳቸው የሚቸገሩትንም በቤታቸው ተገኝቶ ፆም ማስፈታት የተለመደ ነው፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በ2012 ዓ.ም. በተለይ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ዓብይ ፆም የሚከናወንበት ወቅት መከሰቱ፣ ብዙ ነገሮችን አሳጥቷል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ሲባል ምዕመናን በቤታቸው እንዲቀመጡ ሆኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ደጆች ተዘግተዋል፡፡ ምዕመናን ቤታቸው ሆነው የፀሎት መርሐ ግብሩን በቴሌቪዥን መስኮት እንዲከታተሉ ተገደዋል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ደጃፍ ደርሰው አትገቡም የተባሉ እናቶችና አባቶች አንብተዋል፡፡ በምዕመናን ልገሳ ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ቋሚ ነዳያን ተቸግረዋል፡፡
ይህ ወረርሽኝ በበርካታ ቤተሰቦች ላይም አጥልቷል፡፡ እንራብ ይሆን? የሚል ሥጋትንም አሳድሯል፡፡
ይህንን የተመለከቱ ወጣቶች የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው የሀብት ማሰባሰብ ጎን ለጎን ደረቅ ምግብ ለማሰባሰብና ለተቸገሩት ለመርዳት ሲዋትቱ ከርመዋል፡፡ ብዙዎቹም ተሳክቶላቸው ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሳሙናና ሌሎችንም ዕርዳታዎች ማሰባሰብ ችለዋል፡፡
ረቡዕ ሚያዝያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት የታቦት ማደሪያ ወጣቶች ማኅበር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ዕርዳታ አድርጓል፡፡ በአካባቢው ስንዘዋወር እንደተመለከትነው መኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ዱቄት፣ ሽንኩርት፣ ሳሙናና አምስት ሊትር ዘይት ለአንድ ለአንድ ቤተሰብ መድበው ሰጥተዋል፡፡
ከወጣቶቹ ባገኘነው መረጃ፣ ዕርዳታውን ከመስጠታቸው በፊት የሚሰጣቸውን ሰዎች ቤት ለቤት በመዞር ተመልክተዋል፡፡ ለተመረጡና በችግር ውስጥ ለሚኖሩ ቤተሰቦችም ለግሰዋል፡፡
በየካ ሚካኤል አካባቢ የሚገኘው ውሉደ ሚካኤል መንፈሳዊ ማኅበር የበጎ ፈቃድ ዕርዳታ ከሚያደርጉ ማኅበራት ይመደባል፡፡ ከማኅበሩ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ ለ31 ቋሚ ቤተሰቦች በየወሩ ዕርዳታ ማድረግ ከጀመረ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡
የማኅበሩ አባላት የችግረኞችን በተለይም የነዳያንን ቤት ማደስና ደም መለገስ ቋሚ አገልግሎታቸው ሲሆን፣ በዓል በመጣ ቁጥርም ለችግረኞች ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩ በዓላት ሥጋ፣ እንቁላል፣ ሽንኩርት፣ በርበሬና ዘይት ይሰጡ የነበረ ሲሆን፣ ለአሁኑ ትንሳዔ ግን ከዕርዳታ ሰንጠረዥ ውስጥ ሥጋን ሰርዘዋል፡፡
የማኅበሩ አባል እንደነገሩን፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ብክለት እንዳይፈጠር በመሥጋት ሥጋን ይሰርዙ እንጂ፣ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ 1,200 ብር በመመደብ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዱቄት፣ ሩዝና ሌሎችንም በመግዛት አበርክተዋል፡፡
በተለያዩ በዓላት ስጦታ ይዘው ድንገት ከችግረኞች ቤት መገኘትን ያስለመዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የትንሳዔ በዓልን አስመልክተው ዳግም ጎራ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ጋር በመሆን፣ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን የጎበኙ ሲሆን፣ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እያገለገሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ቤት የማደስ መርሐ ግብር ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ከንቲባው የተገኙበት የእማሆይ አዱኛ መኖሪያ ቤት፣ የትንሳዔ በዓልን አስመልክቶም ዳግም ተጎብኝቷል፡፡ ለእሳቸውና ለአካባቢው ነዋሪዎችም የተለያዩ የፋሲካ ስጦታዎችንም አበርክተዋል፡፡ የስጦታ ተቋዳሽ ከሆኑት መካከል በአፍንጮ በር አካባቢ የሚገኘው የሕፃናት ማሳደጊያ ይገኝበታል፡፡