Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከዘመናት ፈተናዎች በመማር የከፋ ጊዜን መሻገር ይቻላል!

ኢትዮጵያዊያን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ከሚያደርጉዋቸው የጥንቃቄ ተግባራት በተጨማሪ፣ ወቅቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምክንያቶችን መመርመር ይገባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከሚደረጉ ርብርቦች መካከል ለክፉ ጊዜ የሚሆኑ መጠባበቂያ ምግቦች ማከማቸት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የልየታና የምርመራ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ላቦራቶሪዎችን ማዘጋጀት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1,200 በላይ የምግብ መቀበያ ባንኮች መዘጋጀታቸውም በአርዓያነት እየተወሳ ነው፡፡ የቫይረሱ ጥቃት በከፋባቸው ሀብታም አገሮች ሳይቀር ለማግኘት አዳጋች የነበሩ ሜካኒካል ቬንቲሌተሮችን፣ እዚህ ለማምረት የተጀመሩ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በክፉ ጊዜ የመረዳዳት ባህላቸው አገራቸው ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል እንዳገዘ፣ ኢትዮጵያም በአፍሪካ ብቸኛዋ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች አገር እንዳደረጋትና ጀግንነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚወራረስ እንዲሆን እንዳስቻለ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ካጋጠሙዋቸው ፈተናዎች ለመማር ዝግጁ ይሁኑ፡፡

ይህንን የመሰለ አኩሪና አስመኪ ባህል እንዴት ወደ ልማትና ብልፅግና መቀየር አልተቻለም በማለት፣ በዚህ የፅሞና ወቅት ጠለቅ ብሎ በመመርመር ትክክለኛውን ጎዳና መያዝ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ 12 ተፋሰሶች ያሏት የውኃ ሀብታም፣ በደጋም ሆነ በቆላ ለእርሻ ተስማሚ የሆኑ በጣም ሰፊ መሬቶች ባለፀጋ፣ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ፣ የተስማሚ የአየር ፀባዮች ባለቤት፣ ተዝቀው የማያልቁ በርካታ ማዕድናት በማህፀኗ የያዘች፣ በተለያዩ የቱሪስት መስህቦች የከበረች፣ ወዘተ አገር ናት፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች በላይ 110 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ከሚገመተው ሕዝቧ ከ70 በላይ የሚሆነው ታዳጊና ወጣት ሲሆን፣ 30 ሚሊዮን ልጆቿ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ ያላት አገር በረሃብ፣ በቸነፈር፣ በኋላቀርነትና በእርስ በርስ ጦርነት መሰቃየቷ ለምን ይሆን መባል ይኖርበታል፡፡ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ለዓለም ገበያ አቅርባ መበልፀግ የሚገባት አገር ስንዴ፣ ዘይት፣ ወተትና የመሳሰሉ ምርቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገባት የሌሎች ጥገኛ የመሆኗ ምክንያቱ መመርመር አለበት፡፡ የሀብት ማማ ላይ መገኘት የነበረባት ኢትዮጵያ ለምን ድሆች ተርታ ተሠለፈች ተብሎ መገምገም የግድ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊያን አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይሆንላቸውም›› ተብሎ ሲተረት የኖረው ለምንድነው? ባለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ለአገሪቱ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ አግሮ ኢንዱስትሪዎች በአክሲዮን ማኅበራትነት ከተመሠረቱ በኋላ ለምን መከኑ? በሽርክና የተመሠረቱ ብዙ ኩባንያዎች ለምን ተጨናገፉ? በአንድ ወቅት ብዙ የተወራላቸው የቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የት ደረሱ? ሌሎች ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአገሪቱ በሥራ ላይ ያሉ የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ባይወድቁ ኖሮ፣ ዛሬ በሕይወት እንደማይገኙ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ብዙዎቹ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የተፈጠሩ ሽኩቻዎች የከሸፉት፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ቀውስ ከተፈጠረ አገሪቱ እንደምትሽመደመድ የተገነዘበው መንግሥት ጠንካራ ጡጫ በማሳረፉ ነው፡፡ በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ተቆጣጣሪ ለመሰየም ፍላጎት ባላማሳየቱ ግን፣ ለአገር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ እንዳይሆኑ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ይህ ጥፋት መንግሥትን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሊያስቆጭ ይገባል፡፡

ለዓመታት ከድጡ ወደ ማጡ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ለውጥም ሆነ መሻሻል እየታየበት አይደለም፡፡ በአንድ ዓይነት መንገድ እየተጓዙ ስህተት ከሚደጋግሙ ግራ አጋቢዎች ጀምሮ፣ ሰብዓዊነት የማይሰማቸው የሥልጣን ጥመኞች የሚንጎራደዱበት ብልሹው የፖለቲካ ምኅዳር ለሰላማዊና ለሠለጠነ የሰጥቶ መቀበል መርህ አልገዛ እንዳለ ነው፡፡ በአብዛኛው የ1960ዎቹ ትውልድ ሰዎች የሚመሩዋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትን የማያከብሩ፣ ግልጽ የሆነ ራዕይና አጀንዳ የሌላቸው፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ሳይሆን ደም ለመቃባት የሚቅበዘበዙ፣ ለሥልጣንና ለጥቅም እንጂ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ህልውና የማይጨነቁ፣ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› እንዳለችው እንስሳ ለመጪው ትውልድ የማይጨነቁ፣ በጥላቻ፣ በቂም በቀልና በክፋት የተለከፉ፣ እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎቻቸውን በማታለል የተካኑ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በቀይና በነጭ ሽብር ያስፈጁት አንድ ትውልድ ደሙ ዛሬም ድረስ እየጮኸ፣ እነሱ ግን ከዚያ የአምባገነንነትና የጥፋት አባዜ ውስጥ ለመውጣት ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ ይባስ ብለው ከእነሱ የባሱ አክራሪ ብሔርተኞችን ፈልፍለው አገር ሲያምሱ ከርመዋል፡፡ በዚህ ዘመን በሺዎች ለሚቆጠሩ ንፁኃን ሞት፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ምስኪኖች መፈናቀልና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ እንዲሁም መጠኑ ከፍተኛ ለሆነ የአገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ በቅርቡ የገጠመን መራራ ሀቅ እንደሆነ አይካድም፡፡ ኢትዮጵያ መከራ ካሳዩዋት መካከል እነዚህ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከእነሱ ጎን ለጎን በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት ካባ ውስጥ በመደበቅ አክቲቪስት የሚባል መጠሪያ ያላቸው መሰሪዎች ደግሞ፣ ወጣቱን እንደ በግ እየነዱ እሳት ውስጥ ሲማግዱት ቆይተዋል፡፡ ሁሌም ቅራኔ በመፍጠር እሳት ለማቀጣጠል እንጂ፣ ለአገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ናቸው የፖለቲካውን ሠፈር እያመሱት ያሉት፡፡ እነሱ ጥቅማቸው አይጉደል እንጂ አገር ብትበታተን ደንታቸው አይደለም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አደጋ በደቀነበት በዚህ አስደንጋጭ ጊዜ፣ ከተለመደው ድርጊታቸው ለመውጣት የማይፈልጉ ወፈፌዎች አሁንም ሲፎክሩ ይሰማሉ፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ለማታለል ቢሞክሩም፣ ግብራቸው ግን ፀረ ሕዝብ እንደሆነ በአደባባይ የታየ እውነት ነው፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን በመፈብረክ ሕዝቡን ደም ለማቃበት ከፈጸሙት በደል በተጨማሪ፣ ለአገር የሚያስፈልጉ የተከበሩ ሰዎችን ስም በማጥፋትና ተሳትፎዋቸው እንዲገደብ በማድረግ ከፍተኛ በደል አድርሰዋል፡፡ ያልተፈጸመ ታሪክ እየፈጠሩ በሕዝቡ ውስጥ ቅራኔ መዝራት፣ በሃይማኖቶች ውስጥ በመግባት አለመተማመን መፍጠርና ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የቤተ እምነቶች ቃጠሎ ማድረስ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ነውሮቻቸው ናቸው፡፡ አሁንም የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የተዛቡ መረጃዎችን በማሠራጨት መርዝ እየተፉ ነው፡፡ እነዚህም አገርን አሳር ያሳዩ እኩዮች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን እነዚህንና ሌሎች ፈተናዎችን በሚገባ በመነጋገርና ወደ እውነት የሚወስደውን ጎዳና በመከተል፣ ከዚህ በኋላ ለፀፀት የሚዳርጉ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በኅብረት መነሳት አለባቸው፡፡ ዓለም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቁም እስረኛ ሆኖ በፅሞና ውስጥ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊያንም አገራቸው ለምን የመከራ ቋት ሆና እንደኖረች በአንክሮ መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፆታ፣ በማኅበራዊ ትስስርና በመሳሰሉት ልዩነት ሳያደርግ የሰው ልጅን እያጠቃ ካለው ኮሮና ቫይረስ መማር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አክብረው ለዘመናት አብረው መኖራቸውን ባለመቀበል ሊከፋፍሏቸውና አገራቸውን ሊበታትኑ ከሚሞክሩ መሰሪዎች መከላከል ይኖርባቸዋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ለማንም ምሕረት የሌለው ገዳይ መቅሰፍት መሆኑን በመረዳት በመተባበር ለመከላከል በአንድነት የቆሙት ኢትዮጵያዊያን፣ ከአሁን በኋላ ለዘመናት ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ የዘፈቁዋቸውን ለዘመኑ የማይመጥኑ አስተሳሰቦችን በጋራ መፋለም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸውና የሚደምቁት አብረው ሲሠሩ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ ሲታገሉ፣ እኩልነትና ነፃነት የሚረጋገጥበት ሥርዓት ሲገነቡ፣ በሰውነታቸው እንጂ በአጋጣሚ ባገኙት ማንነት ሳይኮፈሱ፣ በአንድ አገር ልጅነት ሲተሳሰቡና አገራቸውን ለመጪው ትውልድ እንድትመች አድርገው ሲያንፅዋት ብቻ ነው፡፡ ለዘመኑ የማይመጥኑ ኋላቀር አስተሳሰቦችና የክፋት ድርጊቶች ፋይዳ ቢስ ከመሆናቸውም በላይ፣ ዘመኑ ከደረሰበት ምጥቀት አኳያ የሚያስንቁና አንገት የሚያስደፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን አሁን እያሳዩ ያሉትን ደግነት፣ መተሳሰብና መተዛዘን ዘመን ተሻጋሪ ያድርጉት፡፡ ይህንን የከፋ ጊዜ መሻገር የሚቻለው ከዘመናት ፈተና በመማር ነው!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት