የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ ባስጠናው የቢፒአር ጥናት መሠረት፣ አዲስ የሠራተኞች ምደባ ከማድረጉ ውጪ አንድም ሠራተኛ እንዳላባረረ አስታወቀ፡፡
ቢሮውን ጨምሮ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ በቤቶች ዲዛይን ጽሕፈት ቤትና በቤቶች ግንባታ ኢንተርፕራይዝ ከሁለት ዓመታት እስከ 15 ዓመታት የሠሩ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራቸው መታገዳቸውን በሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የረቡዕ ዕትም ላይ መግለጻቸውን በመቃወም የቢሮው ኃላፊ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊዋ ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር) እንደሚሉት፣ በ2011 ዓ.ም. የቢፒአር ጥናት ተጠንቷል፡፡ በዚህም የሠራተኞች የድልድል ሥራ በዚያው ዓመት ተሠርቷል፡፡ የእነሱ ተቋም (ቢሮውና በሥሩ ያሉት ሦስት ተቋማት) ድልድል ያላደረጉበት ምክንያት አሁን ያሉት ተቋማት እንደ አዲስ በመደራጀታቸውና ሙሉ በሙሉ የአሠራር ባህሪያቸው በመቀየሩ ነው፡፡
‹‹ተቋሙ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው ስለሆነ ድልድሉን በቀላሉ አንዱን በሌላ የሚተካበት አይደለም፡፡ መረጃዎችን የማደራጀት፣ ትልልቅ ንብረቶችን ቆጥሮ የማስተካከል ሥራ፣ ቀደም ብለው የነበሩ አሠራሮችን ማስተካከል ስለነበረበትና የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከታመነባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ፣ የቤቶች ተቋም በመሆኑ የሠራተኛን ድልድል ባለፈው ዓመት ማድረግ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡
በቢሮው ሥር ሦስት ተቋማት ያሉ በመሆናቸውና አንደኛው ከሌላኛው ጋር የሚጣመሩ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ተቋማቱ እንደ አዲስ ሲፈጠሩ አብረዋቸው የተፈጠሩ አዳዲስ የሥራ መደቦች እንደ ነበሩም አክለዋል፡፡ አዳዲስ በተፈጠሩ የሥራ መደቦች ላይ አዲስ ሠራተኛ ከመቀጠሩ በፊት የውስጥ ሠራተኞች እንዲወዳደሩ መደረጉን የጠቆሙት ሰናይት (ኢንጂነር)፣ በተወሰኑት የሥራ መደቦች ላይ ውድድር መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የሽግግር ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ በማንኛውም የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ሕግ መሠረት በተቋማት ውስጥ ባለ ወይም በተፈጠረ የሥራ መደብ ላይ መጀመርያ ሠራተኛው እንዲወዳደር እንደሚደረግ ጠቁመው፣ እሳቸውም የሚመሩት ተቋም ያደረገው ተመሳሳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ሰናይት (ኢንጂነር) ገለጻ፣ ለአንድ የሥራ መደብ እስከ 40 ሠራተኞች ተወዳድረዋል፡፡ በሌላም አንድ የሥራ መደብ አንድ ሰው ተፈልጎ እስከ 140 ሠራተኞች ተወዳድረዋል፡፡ በአንዳንድ የሥራ መደቦች ላይ ደግሞ ያልተወዳደረም አለ፡፡ በዚህ መሠረት መሥፈርቱን አሟልተው የተገኙ ሠራተኞች መመደባቸውንና ሌሎቹ ደግሞ የወጣውን መሥፈርት ባለማሟላታቸው አለመመደባቸውን የሚገልጽ መግለጫ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጠፈ እንጂ፣ ሠራተኛ ተባሯል ወይም ተቀንሷል ተብሎ እንዳልተነገረ አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ቅሬታ ያለው ካለ ቅሬታውን እንዲያቀርብ ዕድል መሰጠቱን፣ ቅሬታውም ‹‹በመሥፈርቱ መሠረት ውጤት አሟልቼ እያለ፣ ከእኔ የማይሻሉ ስለተመደቡ ይታይልኝ›› የሚል መሆን እንዳለበት አክለዋል፡፡ ቅሬታውም በአግባቡ በምደባ ኮሚቴው እየታየ እንደሚስተናገድም አስረድተዋል፡፡
ተቋማቱ አሁን ከመደባቸው ሠራተኞች ውጪ ያሉ ያልተመደቡ ሠራተኞች፣ ፐብሊክ ሰርቪስ ባለው ክፍት የሥራ መደቦች ላይ በድጋሚ እንዲመደቡ እንደሚደረግም የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሠራተኛ በፈለገው ቦታ ላይ አልተመደበም ማለት ተባረረ ማለት አይደለም፤›› ያሉት ኃላፊዋ፣ ‹‹ሌሎች እነሱን የሚመጥኑ ብዙ የሥራ መደቦች ስላሉ ኮሚቴው ይመድባል፡፡ ፐብሊክ ሰርቪሱም እንዲመድብ ይደረጋል፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ ሠራተኞች አልተመደቡም ማለት ከሥራ ይወጣሉ ማለት ሳይሆን፣ የተወዳደሩበትን የሥራ መደብ ለማግኘት በነጥብ ስለተበለጡ መመደብ ባይችሉም በሚመጥናቸው የሥራ መደብ በሚመለከተው አካልና በመመርያው መሠረት ይመደባሉ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
‹‹ማንም አይባረርም፡፡ ደመወዛቸውም አይቋረጥም፡፡ ጥቅማ ጥቅማቸውም አይቋረጥም፡፡ የፈለጉትን የሥራ መደብ ግን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ለአንድ የሥራ መደብ አንድ ሠራተኛ ስለተመረጠ በሚመጥናቸው የሥራ መደብ ይመደባሉ፤›› ብለዋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ፐብሊክ ሰርቪስ አዋጁ ወይም ከጊዜው ሁኔታ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሰናይት (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ ከሥራ ስለመሰናበቱ የሚገልጽ ደብዳቤ የተሰጠው አንድም ሠራተኛ እንደሌለና የተመደቡትም ቢሆን ውጤታቸው ከመገለጹ ባለፈ፣ ስለተመደቡበት ሥራ የተገለጸ ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
ዘግይቶ ከመጀመሩ ውጪ ሌሎች በአስተዳደሩ ሥር ካሉ ተቋማት የተለየ የተሠራ ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡