Friday, December 1, 2023

ፌዴራል ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚጥሱ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀመርኩ አለ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሰብዓዊ መብት መጣሻ ሳይሆን ዜጎችን ከአደጋ መጠበቂያ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡ አዋጁን በሚጥሱት ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ጄኔራል ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው የአስቸኳይ አዋጁን አፈጻጸም በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን፣ አዋጁ የወጣው የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ለመጣስ እንዲያመች ተደርጎ እንሆነ የሚነገረው ወይም የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

በአንዳንድ በመገናኛ ብዙኃንና የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሠራጩ መረጃዎች ኅብረተሰቡን የሚያሳስቱና ከእውነት የራቁ በመሆናቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከመገናኛ ብዙኃን ጀርባ ሆነው የሚያስነግሩት ሐሰተኛ መረጃ መኖሩን ጠቁመው፣ መንግሥት ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድና ያንንም ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎችን ከወረርሽኝ መከላከያ መሆኑን ሕዝቡ ተገንዝቦ አስፈጻሚ አካላትን በመተባበር፣ ወደፊት ሊያጋጥሙ በሚችሉ ችግሮች ላለመጎዳት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በልጅነት የተሰጡ ክትባቶችና የአመጋገብ ሥርዓቶች፣ ወረርሽኙን እንደሚከላከሉ የሚነገረው ስህተት መሆኑን በመረዳት ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉትን ምክርና መንግሥት ያወጣውን አዋጅና መመርያ ተግባራዊ በማድረግ፣ ወረርሽኙን መከላከል አስፈላጊና ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይኼንን በማይፈጽሙ ላይ በሕጉ መሠረት ዕርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል፡፡ ዕርምጃውም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅና ከወረርሽኑ ለመከላል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣ ቢሆንም፣ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕጉን እያከበሩ አለመሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች፣ በመገበያያ ቦታዎች (ጃንሜዳ፣ አዋሬ፣ ሾላ ገበያ፣ በአደባባዮችና በትራንስፖርት መጠበቂያ ቦታዎች) አካባቢ የታየው የሕዝብ እንቅስቃሴ መራራቅን ሳይሆን የበለጠ መቀራረብን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ሕጉ ሊተረጎም ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በርክተዋል፡፡

ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 አንቀጽ 6(1) እና ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 466/2012 አንቀጽ 3(6) ተላልፎ ከተፈቀደለት የተሳፋሪ ቁጥር በላይ ጭኖ የተገኘ ተሽከርካሪ ተይዞ በገንዘብ ተቀጥቷል፡፡ አሽከርካሪው ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ላይ የመጫን አቅሙ 14 ሰው የነበረን የሰሌዳ ቁጥሩ 3-42247 ኦሮ ዶልፊን ተሽከርካሪ አሥር ሰዎችን ጭኖ ወደ ቡታጅራ ሲያመራ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰባተኛ አካባቢ ተይዞ በዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶበታል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ ወንጀል ችሎት የ1,500 ብር ቅጣት ወስኖበታል፡፡ ምንም እንኳን የገንዘቡ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ሕጉ መተግበር መጀመሩን ለሕዝቡ ማሳወቂያና ማስተማሪያ በመሆኑ፣ ማንኛውም ሰው እንዲጠነቀቅና ሕግ ጥሶ ከወንጀል ተጠያቂነት መዳን እንደማይቻል ማሳያ መሆኑን የሕግ አስከባሪዎች እያሳሰቡ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -