የኢትዮጵያ አየር መንገድ የውጭ ዕዳ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና አበዳሪ አገሮች ለአፍሪካ የንግድ ኩባንያዎች (ኮርፖሬሽኖች) ለሰጡት ብድር የክፍያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠየቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሉምበርግ በተባለው በአሜሪካ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሰሞኑን በግል ባቀረቡት ጽሑፍ ኃያላን አበዳሪ አገሮችና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በአፍሪካ ለሚገኙ የንግድ ኩባንያዎች የሰጡትን ብድር የመክፈያ ጊዜ ካላራዘሙ፣ የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጉዳት መቋቋም እንደማይቻል ገልጸዋል።
በማደግ ላይ የሚገኘው የአፍሪካ የኮርፖሬት ዘርፍ አደጋ ላይ እንደሆነ በጽሑፋቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ኃያላን አገሮችና የዓለም የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካ አገሮችን የውጭ ዕዳ የክፍያ ጊዜ ለማራዘም በጀመሩት የምክክር ሒደት ውስጥ የአፍሪካ ኮርፖሬሽኖች የውጭ ብድርን በተመሳሳይ እንዲመለከቱ ጠይቀዋል።
‹‹የአፍሪካ ኮርፖሬት ዘርፍን መታደግ ፈርጀ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ እነሱን መታደግ ማለት የቀጠሯቸውን ሠራተኞች መታደግ ነው፡፡ ይኼንን ማድረግም የዓለም ኢኮኖሚ በቫይረሱ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ዕድል ይፈጥራል፤›› ብለዋል። ይህንን ጉዳይ በተመለከተም የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ የቡድን 20 አገሮችና የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች ጋር በመመካከር መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በእነዚህ ዓመታት የድህነት ምጣኔ በግማሽ መቀነሱን፣ ገቢ በእጥፍ መጨመሩንና ሰላምና መረጋጋት መፍጠር እንደተቻለም አመላክተዋል።
የሚመሩት መንግሥት በቅርቡ በጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም እ.ኤ.አ. በ2030 የኤክስፖርት ገቢን በአሥር በመቶ ለመጨመር፣ ከውጭ የሚገኝ የሐዋላ ገቢን በ32 በመቶ ለመጨመር፣ እንዲሁም ሌሎች ዕቅዶች በአጠቃላይ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በ40 በመቶ እንደሚያሳድጉትና በዚህም የአገሪቱን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመቋቋም ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል። ነገር ግን አሁን በተከሰተው የኮሮና የቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚና ዕቅድ ከወዲሁ ፈተና እንደገጠመው ጠቁመዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገጠመውን ፈተና የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አየር መንገዱ አሁን እየሠራ የሚገኘው የአቅሙን 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ፣ በዚህ ሁኔታ አየር መንገዱ እንዲያሳካ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ውጤት ማረጋገጥ እንደማይቻልና ይህ መሰሉ ችግርም ሌሎችን የአፍሪካ አየር መንገዶች እንደገጠማቸው ገልጸዋል።
ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለ መንግሥት ዋስትና ተበዶሮ ያልከፈለው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ አለበት።
ኢትዮጵያ ያለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ኢትዮ ቴሌኮም ከቻይና መንግሥት ተበድረው ያልከፈሉት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የመክፈያ ጊዜ መንግሥት ባደረገው ድርድር እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።