Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እነሆ የኩዳዴ ፆም በሰላም ተጠናቆ የፋሲካ በዓል ላይ ደርሰናል፡፡ ለሁለት ወራት ያህል በፆምና በፀሎት ላይ የከረሙ ምዕመናን፣ ይህንን ታላቅ በዓል በከፍተኛ ስሜት እንደሚያከብሩት ይታወቃል፡፡ በፋሲካ የበሬ ቅርጫ፣ በግ፣ ዶሮ፣ ዳቦ፣ ጠላና ጠጅ ወዘተ. ዝግጅቶች የበዓሉ ዋነኛ ማዳመቂያ ናቸው፡፡ በዓሉ በከፍተኛ ሁኔታ የምግብ ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ በበርካታ ገጠመኞች የተሞላ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ከፋሲካ ጋር የተገናኙ በርካታ ገጠመኞች ይኖሩናል፡፡ ምንም እንኳ ዘንድሮ ዓለምን እያርበደበደ ያለው ኮሮና ቫይረስ በሌሎች አገሮችም ሆነ በኢትዮጵያ ፋሲካን ቢያደበዝዘውም፣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው የጥንቃቄ መመርያዎች ሳይዛነፉ እንደ ነገሩ በዓሉ ይከበራል፡፡ እኔም በዓላችንን በኮሮና መሰረቅ የለብንም በማለት ከዚህ ቀደም ካጋጠሙኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ እስኪ ትዝታዎቼን እንዲህ ተጋሩ፡፡

ከፋሲካ በዓል ጋር በተገናኘ ከማይረሱኝ ብዙ ነገሮች መካከል አንዱ ይኼ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ጎረቤቴ የሆኑ አዛውንት ለቅርጫ ያረድነው በሬ ሥጋ እየተመደበ ሳለ፣ ከሻኛው ቆረጥ እያደረጉ መጉረስ ይጀምራሉ፡፡ የቅርጫውን ታዳሚዎችም እንዲሁ ያጎርሳሉ፡፡ በዚህ መሀል እኚህ አዛውንት ጉሮሮአቸው ውስጥ ሥጋ ይወተፍና ነፍስ ግቢ፣ ነፍስ ውጪ ይሆናል፡፡ ሰውዬው ዓይናቸው ፈጦ ሲቃትቱ ድንጋጤ ይፈጠራል፡፡ ወዲያና ወዲህ ቢደረጉ ታፍነው ሊሞቱ ተቃረቡ፡፡ ደቂቃዎች እየነጎዱ ነው፡፡ ነገር ግን አዛውንቱን ለመታደግ አዳገተ፡፡ ማጅራታቸው ከመደብደቡ የተነሳም ተዝለፈለፉ፡፡ የአዋቂ ሰዎችን ከንቱ ሙከራ ሲታዘብ የነበረ አንድ ትንሽ ልጅ ወደ አዛውንቱ ቀረብ ብሎ አይቶአቸው፣ ድንገት ሳይታሰብ ጀርባቸው ላይ ዘሎ በሁለት እግሩ ሲወጣባቸው ጉሮሮአቸው ውስጥ የተወተፈው ትልቅ ሥጋ እንደ ጥይት በሮ ወጣ፡፡ አዛውንቱም ለጥቂት ከሞት ተረፉ፡፡ ያ ታዳጊ ልጅ ይህን ባያደርግ ኖሮ አልቆላቸው ነበር፡፡ አዛውንቱ ከዚያን ቀን በኋላ ቅርጫ ላይ ሥጋ መጉረስ ዕርም ብለው ነበር፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ከመጠን በላይ በልቶ ቁንጣን የያዘው ዘመዳችን መቆም መቀመጥ ያቅተውና ወደ ሆስፒታል ይወሰዳል፡፡ ተረኛው ሐኪም ይጠራና ይመጣል፡፡ አገላብጦ ካየው በኋላ የሚጠጣ መድኃኒት አዞለት ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡ ከዚያም መፀዳጃ ቤት ሄዶ ተንፍሶ ይመለሳል፡፡ በዘመዳችን ቁንጣን በጣም የተገረመው ሐኪም ምን በልቶ እንደነበር ይጠይቀዋል፡፡ ከሥቃዩ የተገላገለው ዘመዳችንም፣ ‹‹ጥሬ ሥጋ፣ ጥብስ፣ ዱለት፣ የዶሮ ወጥ፣ ቅቅል. . .›› እያለ ሲዘረዝር፣ ሐኪሙ ተናዶ፣ ‹‹በቃህ! አንተ ዝም ከተባልክ ድንች፣ በቆሎ፣ ንፍሮ፣ ቂጣ. . . ማለትህ አይቀርም፤›› ሲለው ጭንቀት ውስጥ ገብተው የነበሩ ቤተሰቦቻችን ሳይቀሩ ሳቅ በሳቅ ሆኑ፡፡ ያ ዘመዳችን በዚህ ምክንያት የሥጋ ዘር መብላት ከተወ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

አንዱ ጎረቤታችን ደግሞ በፋሲካ ዋዜማ ቀን ላይ መጠጣት ይጀምርና ሲመሻሽ በግ ለመግዛት ሾላ በግ ተራ ይሄዳል፡፡ ሞቅ እንዳለው መምጣቱን ያዩ የበግ ተራ ደላሎች ያዋክቡት ጀመር፡፡ በዚህም በዚያ ብለው አንዲት የከሳች ግልገል የምትመስል በግ በ600 ብር ይሸጡለትና ያሰናብቱታል፡፡ እሱ ከፊት በግ ተሸካሚው ከኋላ ሆነው ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ በሞቅታ ፈረስ ውስጥ የነበረው አጅሬ ሠፈሩ ደርሶ የግቢውን በር ከፍቶ ሲገባ ቤተሰቦቹ እየጠበቁት ነበር፡፡ ኮራ ብሎ፣ ‹‹በዚህ በኩል ግባ›› ብሎ ለበግ ተሸካሚው ትዕዛዝ መስጠት ሲጀምር ቤተሰቦቹ በመገረም ያዩታል፡፡ ድንገት ዞር ብሎ ሲመለከት በበግ ተሸካሚው ፋንታ ከኋላው የቆመው የእኔ ቢጤ ነበር፡፡ በግ ተሸካሚውና እሱ ገና ድሮ መንገድ ላይ ተለያይተዋል፡፡ አንድ ሰሞን የሰፈሩ ሰው መሳቂያ ሆኖ ከረመ፡፡

 ልክ የዛሬ ሰባት ዓመት የፋሲካ ዋዜማ አባወራው መሸትሸት ካለ በኋላ ቤቱ ይደርሳል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር መጠጥ ሲጨልጥ ስላመሸ ድክምክም ብሎታል፡፡ ባለቤቱ ዶሮ ወጥ እየሠራች ስለነበር ከትንሿ ልጁ ጋር ትንሽ ተጨዋውቶ እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ፡፡ ሌሊት ላይ ከእንቅልፉ ይቀሰቅሱትና እንፈስክ ይሉታል፡፡ የስካሩ ድካም ተጫጭኖት ስለነበር በስንት ጉትጎታና ውትወታ ይነሳል፡፡ ዓይኑን እያጨናበሰ፣ ‹‹ለመሆኑ ዶሮ ጮኸ እንዴ?›› በማለት ለባለቤቱ ጥያቄ ያቀርብላታል፡፡ ማታ ሰክሮ በመምጣቱ በጣም ተናዳበት ስለነበር፣ ‹‹ዶሮው ከጮኸ ዘመን አለፈው፣ ይልቁንስ ተነስና ታጠብ፣ አትንዘባዘብ፤›› ትለዋለች፡፡ አባወራው የሚስቱን ቁጣ ለማብረድ በመሞከር፣ ‹‹ዶሮ ሲጮህ እንዴት አልሰማሁም?›› ሲል የሰማችው ትንሿ ልጁ፣ ‹‹አባብዬ ምን ነካህ? ማታ የታረደው ዶሮ አሁን ከድስት ውስጥ ይጩህልህ ወይ?›› ብላ ስትስቅበት የተበሳጨችው ሚስቱ በሳቅ ተንፈራፈረች፡፡ በሕፃን ልጁ የተቀለደበት አባወራ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መጠጥ በቃኝ ብሎ ትቶታል፡፡ እኛንም በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ምክንያት የደረሰብንን ሰቆቃ ፈጣሪ በቃ እንዲለን፣ ተሳስበንና ተዛዝነን ይህን ፈታኝ ጊዜ ለማለፍ እንስማማ፡፡ ሀብታሞቹ አገሮችና የሥልጣኔ ጣሪያ ላይ ደርሰናል የሚሉትን ሊቃውንት እያንበረከከ ያለው ኮሮና፣ በብርቱ ጥንቃቄና በፈጣሪ ዕገዛ ብቻ ይወገዳል ብዬ ስለማምን አደራ ክፋትን አስወግደን በፍቅር እንኑር፡፡

(ሃይማኖት ዓምዴ፣ ከግንፍሌ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...