ከወደ ቻይና መነሻውን ያደረገው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ዓለምን በእጅጉ እየፈተናት የሚገኝ ሁለንተናዊ ቀውስ ሆኗል፡፡ የቫይረሱ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝነት በዓለም ጤና ድርጅት መታወጁን ተከትሎ ደግሞ፣ እያንዳንዱ የዓለም አቀፍ ተቋም ሆነ እያንዳንዱ አገር ዋነኛ ትኩረቱ ይህን ወረርሽኝ መከላከል ላይ ያተኮረ እንዲሆን አስግድዷል፡፡
በዚህም ምክንያት በርካታ ዕቅዶች እንዲስተጓጎሉና እንዲሰረዙ፣ ወይም ደግሞ ላልተወሰኑ ጊዜ እንዲራዘሙ እያደረገ ነው፡፡ የዚህም ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የሁሉም አገሮች ትኩረት በሽታውን መዋጋት፣ ዜጎችን ከወረርሽኙ መከላከል፣ በወረርሽኙ የተጠቁ ዜጎች በቶሎ እንዲያገግሙ ወይም ደግሞ ቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የሚያስችሉ አማራጮች መፈለግ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ቅድሚያ ሰጥተው እያከናወኑ በመሆኑ ነው፡፡
የዳበረ የኢኮኖሚ መዋቅር፣ የተደራጀ የፖለቲካና የአስተዳደር ሥርዓት፣ እንዲሁም የተጠናከረ የጤና ሥርዓትና ሽፋን ያላቸውን በርካታ አገሮችን የፈተነው፣ የሚመኩቡትን ሁሉ መና ያስቀረውና በተለይ ከጤና ሥርዓታቸውና ዝግጁነታቸው ጋር ያላቸውን የብቃት አቅማቸውን ያጋለጠው ይህ ወረርሽኝ ወደ አፍሪካ ከገባ ሰነባብቷል፡፡
ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅን መግቢያ አድርጎ ወደ አፍሪካ የገባው ይህ ቫይረስ፣ በአኅጉሪቱ ውስጥ ሁሉንም አገሮች አዳርሷል፡፡ ምንም እንኳን በሌሎች አገሮች በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ ያደረሰውን ያህል ጉዳት ገና ያላደረሰ ቢሆንም፣ የአኅጉሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ግን በከፍተኛ ሁኔታ አአስተጓጉሏል፡፡
በዚህም ምክንያት በቅድመ ኮቪድ ወረርሽኝ ሊከወኑ የታቀዱ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎች፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ሊደረጉ የታሰቡ ምርጫዎች ተሰርዘዋል ወይም ደግሞ ላልተወሰኑ ጊዜያት ተራዝመዋል፡፡
የቫይረሱ ሥርጭት በጣም ፈጣን በመሆኑ የተነሳ የዓለም መንግሥታት፣ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት አፋጣኝ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታትና የሚያደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ካሉ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ፣ ድንበር ተሻጋሪ የየብስም ሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን መከልከል፣ ትምህርት ቤቶችንና የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን መዝጋት፣ እንዲሁም በበሽታው የተጠቁና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በለይቶ ማቆያ ሥፍራ ማቆየት ይገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያም የቫይረሱ በአገሪቱ መከሰቱ ከተረጋገጠበት መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ትገኛለች፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ፣ እንዲሁም ደግሞ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረውን አጠቃላይ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ እስከ ማራዘም የደረሱ ውሳኔዎችን አሳልፋለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫን ለማድረግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ምርጫውን አስቀድሞ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማድረግ እንደማይችል ይፋ አድርጓል፡፡
ይህን ውሳኔ በመሠረታዊነት የተቃወመ የተቃዋሚ ፓርቲ ባይኖርም፣ ውሳኔውን ለማሳለፍ የተሄደበትን ሒደት ግን የተቃወሙ አሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ውሳኔው የተሰጠበትን ሒደት የተቃወሙ ፓርቲዎች ናቸው፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ከምርጫ ቦርድ ጋር ስለምርጫው ዕጣ ፈንታ አንድ ዙር ውይይት ማድረጋቸውንና ቦርዱም ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ለሌላ ዙር ውይይት እንደሚጠራቸው አሳውቋቸው እንደነበር በማስታወስ፣ ሁለተኛው ዙር ውይይት ሳይካሄድ በቦርዱ የተወሰነው ውሳኔ ግን አስተዛዛቢ ነው በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ግን ከአንዴም ሁለቴ ውይይት በማድረግ፣ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
ኮቪድ 19 እና የምርጫዎች መራዘም
የዚህ ወረርሽኝ ፈርጀ ብዙ ተፅዕኖዎች ለዓመታት የሚዘልቁ ቢሆንም፣ ከመነሻው ግን ፖለቲካዊ ተፅዕኖው እየታየ ነው፡፡ ይህም ማለት በዋነኛነት የምርጫዎች መራዘምን በበርካታ አገሮች አስከትሏል፡፡
ከመራጮች ምዝገባ እስከ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናና ሥምሪት ምርጫ በዋነኛነት የሕዝብን መሰባሰብ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህ ደግሞ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚመከሩ መንገዶች አንዱ የሆነውን አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚቃረን ስለሆነ፣ የምርጫዎች መራዘም ለምን የማያሰኝ ዋነኛ ዕርምጃ ሆኗል፡፡ እየሆነም ነው፡፡ የቫይረሱን ወረርሽኝ በቅርቡ መቆጣጠር የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ ወደፊት ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ዕርምጃዎች መውሰዳቸው አይቀሬ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታትና ለመቀነስ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች አጠቃላይ አገራዊ ምርጫዎች፣ እንዲሁም ሕዝበ ውሳኔዎች እንዲዘገዩ አልያም ደግሞ እንዲራዘሙ አድርገዋል፡፡
ምርጫዎች እንዲራዘሙ ወይም እንዲዘገዩ ካደረጉ አገሮች መካከል ደግሞ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ ካዛኪስታን፣ ካናዳ፣ ብራዚል ይገኛሉ፡፡ ከአፍሪካ አኅጉር ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዝያ፣ ቶጎ፣ ታንዛኒያ፣ ጊኒ፣ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ በተለያዩ ደረጃዎች ሊያደርጉዋቸው አቅደው የነበሩዋቸውን ምርጫዎች ሰርዘዋል፣ አልያም አራዝመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ መራዘም
ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መሠረት የተለያዩ ምክንያቶችን በዝርዝር በማቅረብ፣ በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ይህም የምርጫውን ጊዜ ወደፊት ይገፋዋል፡፡
ይህንን የቦርዱን ውሳኔ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፀጋ የተቀበሉት ቢሆንም፣ የወረርሽኙን መክሰም ወይም መቀነስ ተከትሎ ለሚኖረው እንቅስቃሴ ግን ከመንግሥት ጋር መደራደርና መወያየት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ቦርዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ‹‹የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አጠቃላይ ምርጫ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው የዳሰሳ ጽሑፍ ላይ፣ ወረርሽኞችን ለመግታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚያደርሱበትን የተፅዕኖ ግምገማ አቅርቧል፡፡
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ ላይ የአሥር ቀናት መዘግየት፣ ብዛት ያላቸው የኅትመት ውጤቶች ግዥ በአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል የተነሳ መዘግየት፣ 1,000 ሰዎችን ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሠልጣኞችን ሥልጠና ማከናወን፣ እንዲሁም ለ150,000 የምርጫ አስፈጻሚዎች የሚሰጥ ሥልጠናን በተመለከተ አስፈላጊ ተግባራትን ለማከናወን አለመቻል፣ በሚያስፈልገው መጠን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት አስቸጋሪ መሆን፣ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ የመራጮች ትምህርትና ቅስቀሳዎች የኮቪድ 19 ቫይረስን በተመለከተ በሚወጡ የማኅበረሰብ ጤና አስገንዛቢ መልዕክቶች ሊዋጡ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሠራጨት ሥራ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከሚደረገው እንቅስቃሴ አንፃር፣ በተለይም መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እንደሚሠራ ማስታወቁን ተከትሎ ችግር ሊገጥመው ስለሚችል የሚሉትን በምክንያትነት በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በምርጫው ሒደት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ አስመልክቶ የደረሰበትን መደምደሚያ አስመልክቶም ቦርዱ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በቀጣዩ የምርጫ አፈጻጸም ላይ ኮቪድ 19 የፈጠረውንና የሚፈጥረውን ችግር አስመልክቶ፣ ሕግ አውጪውን ጨምሮ ከመንግሥት የተለያዩ አካላት፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ኤክስፐርቶች፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከዓለም አቀፍ አገሮች ጋር ምክክር ማድረጉንም ሰነዱ ይጠቁማል፡፡
በዚህም መሠረት ከላይ በተዘረዘሩት ተፅዕኖዎች ምክንያት ቀጣዩ ምርጫ ሊከናወን የሚችልባቸውን አማራጭ የቢሆን ሁኔታ ግምቶችን አቅርቧል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ፣ ‹‹የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከሚያዝያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላም ሊቆዩ ይችላሉ የሚል ሲሆን፣ ይህ በሆነበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ምርጫውን ማስፈጸም አይችልም፤›› የሚል ነው፡፡
በዚህም መሠረት፣ ‹‹ከዚህም አኳያ የሰባት ወራት (210 ቀናት) ጊዜ ሰሌዳ የሚጀምረው በግንቦት 2012 ዓ.ም. ሲሆን አገራዊ ምርጫው ደግሞ በኅዳር 2013 ዓ.ም. ማብቂያ ወይም ታኅሳስ መጀመርያ ላይ የሚካሄድ ይሆናል፤›› የሚል አማራጭ አቅርቧል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚሳካ አይመስልም፡፡
በሁለተኛው የቢሆን ሁኔታ ግምት ደግሞ ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ አጠቃላይ ምርጫው በየካቲት 2013 ዓ.ም. ሊካሄድ እንደሚችል በአማራጭነት አቅርቧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ መታወጅን ተከትሎ ደግሞ ማንኛውም የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ስብሰባዎችና እንቅስቃሴዎች የሚታገዱ ከመሆናቸው አንፃር፣ በቀጣይ የምርጫው ሒደትና ወቅት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖን በማስመልከት በርካታ ሐሳቦች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አንፃር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል የሚጠይቁ ድምፆች በርክተዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በጉዳዩ ላይ መረባረብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሁሉም በየፊናው እንዲረባረብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
‹‹የሚወሰዱ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎች ለታለመላቸው የጤናና ተጓዳኝ ጉዳቶችን ለመከላከል ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ ለሌላ የፖለቲካ ፍጆታ፣ እንዲሁም በዚህ አዋጅ ስም ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ሌላውን ዒላማ ማድረግ ተቀባይነት አይኖረውም፤›› በማለት ሥጋት አዘል አስተያየቱን አቅርቧል፡፡
የምርጫውን መራዘም ተከትሎ ከሚደመጡ በርካታ ድምፆች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ሰኔ ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ ከዚያ በኋላ የሚኖሩ ቀጣይ አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሒደቶችን፣ እንዲሁም ምርጫን የተመለከቱ ተግባራት በመንግሥት ብቻ መወሰን እንደማይኖርባቸውና የጋራ አሠራር የሚዘረጋበት መንገድ እንዲመቻች ወደ መምከር ያዘነበሉ ናቸው፡፡
ለዓለም አቀፉ የሳይንስና ምርምር ማኅበረሰብ የቫይረሱ ሥርጭት ለምን ያህል ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ከመሆኑም ባለፈ፣ የቫይረሱ ሥርጭትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመሆኑ አንፃር፣ ቫይረሱ በዚህ ጊዜ ይቆማል ወይም መድኃኒት ይገኝለታል ማለት የማይቻል ነው፡፡ በመሆኑም ምርጫ ከማራዘም በዘለለ ለቀጣይ አገራዊ መግባባት ሊያገለግሉ የሚችሉ መሠረቶች እንዲጣሉ መደላድሉ እንዲሠራ የሚያሳስቡ ወገኖችን አስተያየት ከግምት ማስገባት፣ ድኅረ ኮሮና የሚኖረውን የፖለቲካ መስተጋብር ለመቃኘት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል የሚሉ አሉ፡፡