Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበእምነት ተቋማትና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በገበያ ቦታዎችም መደረግ እንዳለበት ተጠቆመ

በእምነት ተቋማትና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በገበያ ቦታዎችም መደረግ እንዳለበት ተጠቆመ

ቀን:

አዋጅ ተላልፈው የተገኙ 268 አሽከርካሪዎች ላይ ቅጣት ተጣለ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ሲባል መንግሥት በእምነት ተቋማትና በአሽከርካሪዎች ላይ እያደረገው ያለውን ቁጥጥር፣ በመገበያያ ቦታዎችም ላይ ሊተገብረው እንደሚገባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለይ ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ የአዲስ አበባ መገበያያ ቦታዎች ላይ የነበረውን የሕዝብ ትርምስ የተመለከቱ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ኮሮና ጠፋ ነው ተስፋፋ?›› የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአዲስ አበበ ፖሊስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊ፣ ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ወረርሽኙ ምን ማለት እንደሆነና ከገባቸው ወገኖችና ጉዳት ከደረሰባቸው አገሮች ትምህርት የወሰዱ ሁሉ በተገኘው መገናኛ መንገድ እንደሚያስረዱ ገልጸው፣ ‹‹የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ ከሌሎች ከተሞችና ከገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ ግንዛቤ አላቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ በመሆኑም የወረርሽኙ መተላለፊያ መንገድ ጭምር ምን እንደሆነ እየተነገራቸው ‹የሚሰጥ ነገር አለና እንዳትቀሩ የተባሉ ይመስል፣ በተለይ ዋና በሚባሉ የገበያ ቦታዎች ሲተራመሱ ማየታቸውን መስክረዋል፡፡

አዋጁን ለማስፈጸም ቀላል ቢሆንም የበለጠ ትርምስ እንዳይፈጠርና በዓሉንም ታሳቢ በማድረግ በፖሊሶች በኩል የተወሰነ መዘናጋት መፈጠሩን ገልጸው፣ ካሁን በኋላ ግን ሕግን ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነትና ጤና ሲባል ማስፈጸም ግዴታው የሆነው አስፈጻሚ አካል ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ካልጠበቃት በስተቀር ከሰሞኑ የሕዝቡ እንቅስቃሴ ወረርሽኙ በቀላሉ የሚተላለፍ ከመሆኑ አንፃር እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎች፣ ‹‹ለኃጢያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል›› እንዲሉ፣ አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው ተቀላቅሎ ቢገኝ ውጤቱን ከወዲሁ መገመት ስለማያስቸግር መንግሥት ለሕዝቡና ለአገሪቱ ሲል ሕጉን ማስፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ፖሊስ አስቸኳይ አዋጁን ተከትሎ በተሽከርካሪዎች ላይ  የተላለፈውን መመርያ አላከበሩም ወይም ተላልፈው ተገኝተዋል ያላቸውን 268 አሽከርካሪዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንዛቤ ማሳደጊያ ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ በኮሚሽኑ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መምርያ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ቁጥጥር፣ 195 አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው በላይ ተጨማሪ ሰዎች በመጫን፣ 73 አሽከርካሪዎች ደግሞ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ በማስከፈል አዋጁን ተላለፈው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና ለመቆጣጠር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እንደ ተሽከርካሪዎቻቸው መቀመጫ ግማሹን በመቀነስና እጥፍ በማስከፈል እንዲሠሩ የተላለፈውን መመርያ ጥሰው መገኘታቸውንም አክለዋል፡፡ በመሆኑም ሕጉን ሳያከብሩ ጥሰው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው 5,000 ብር ቅጣት መጣልና እስከ መንጃ ፈቃድ መንጠቅ የሚደርስ ዕርምጃ መወሰዱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...