Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ ብድርና ጋምቤላ መሬት ከወሰዱት ውስጥ የ285 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰረዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሁሉም ነገር በአዋጅ በታገደበት ወቅት ዕርምጃ መውሰድ ፍትሐዊ አይደለም››

ባለሀብቶች

ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በእርሻ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከሌሎች ባንኮች ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማስፈቀድ ከ630 ሔክታር በላይ መሬት ከወሰዱ 700 ባለሀብቶች ውስጥ፣ የ285 ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመሰረዝ መሬቱን ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱን የጋምቤላ ክልል መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት በኩል ለመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፉት መረጃ እንዳስረዱት፣ ለኢንቨስትመንት የእርሻ መሬት በ2000 ዓ.ም. የወሰዱ ከ700 በላይ ባለሀብቶች ነበሩ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 285 ያህሉ ምንም ዓይነት ልማት ያላከናወኑ መሆናቸው በመረጋገጡ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው መሰረዙን፣ ከ200 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ከ285 ባለሀብቶች ውስጥ 36 ያህሉ ከልማት ባንክ ብድር የወሰዱ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ባለሀብቶች መሬት ተረክበው ወደ ሥራ ያልገቡ፣ ሥራ ጀምረው ያቆሙ፣ የመሬት መጠቀሚያ ግብር ያልከፈሉና ብድር ቢወስዱም ወደ ሥራ አለመግባታቸው የተረጋገጠባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በጋምቤላ የእርሻ መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች የክልሉ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ አውግዘዋል፡፡ የጋምቤላ እርሻ ባለሀብቶች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ የማነ ሰይፉ ክልሉ የወሰደውን ዕርምጃ በሚመለከት ለሪፖርተር እንደተናገሩት ዕርምጃው ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ‹‹ክልሉ ይህንን ጊዜ ለምን መረጠ?›› በማለት ጠይቀው፣ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ባለሀብቱም ሆነ ሌላው የአገሪቱ ሕዝብና ተቋማት ሥራ አቁመው፣ በማንኛውም ነገር ላይ ዕርምጃ መውሰድ ኢፍትሐዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት ጉዳይ ተደጋጋሚ ችግሮች መነሳታቸውን ያስታወሱት አቶ የማነ ችግሮቹ የክልሉ፣ የፌዴራል መንግሥትና የባለሀብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር ማስቆም ባለመቻሉ፣ ለባለሀብቶች ቃል የገባውን የማበረታቻ፣ የብድር ማራዘሚያና ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ባለማከናወኑ ችግሩ ጊዜ እየቆጠረ እዚህ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቶች ብድር ይዘው እንደጠፉ የሚነገረው ትክልል አለመሆኑንና እንዲህ የሚወራው አመራሩን ለማደናገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደዚህ የሚወራባቸው ባለሀብቶች የሥራ ማስኬጃ ጠይቀው ያልተለቀቀላቸውና የብድር ወለድ በዝቶባቸው ‹‹ክፈል አልከፍልም›› በመባባል በንግግር ላይ ያሉ እንጂ፣ ጠፍተው እንዳልሆነ አቶ የማነ አስረድተዋል፡፡

ከልማት ባንክ ተበድረው ሳይከፍሉ እንደጠፉ የሚነገረው 71 ባለሀብቶች እንደሆኑ አስታውሰው፣ እነዚህ ብቻ ከሆኑ የእነሱ መሬት ተወስዶ ሌላውን ማስቀጠል ሲገባ ይህንን አስከፊ ጊዜ ጠብቆ ፈቃድ መሰረዝ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወቅቱ ስብሰባ የተከለከለበትና ፍርድ ቤቶች የተዘጉበት ከመሆኑ አንፃር መንቀሳቀስ ስለማይቻል ምንም ማድረግ ባይችሉም፣ ወቅቱ ሲፈቅድ መብታቸውን በሕግ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል፡፡

ስለጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስትመንት የሚያጠና 14 አባላትን ያካተተ ኮሚቴ ጥናት እንዲያጠና ተደርጎ ጥናቱ በ2009 ዓ.ም. የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በጥናቱም በክልሉ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ 623 ባለሀብቶች 630 ሺሕ ሔክታር መሬት በሊዝ እንደተላለፈላቸው፣ ይኸውም 409 ሺሕ ሔክታር መሬት ከክልሉ መንግሥትና 220 ሺሕ ሔክታር መሬት ከፌዴራል መንግሥት በውክልና መተላለፉን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ግን 76.8 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ መልማቱንና ባለሀብት መሬቱን አልምቶ ለመጠቀምና ለመጥቀም ሳይሆን፣ በአቋራጭ የባንክ ብድር ለማግኘትና ከውጭ የሚያስገባቸውን መሣሪያዎች (ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ) ከታክስ ነፃ ለመጠቀም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ 29 ባለሀብቶች መሬትና ብድር ወስደው መጥፋታቸውን፣ በአጠቃላይ ባለሀብቶቹ 4.98 ቢሊዮን ብር ከልማት ባንክና ሌሎች ባንኮች መበደራቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

በወቅቱ ለስምንት ዓመታት ልማት ባንክን ሲመሩ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ባህረን አቶ ኃይለ ማርያም በድንገት ከኃላፊነታቸው አንስተው፣ ለበርካታ ዓመታት ብሔራዊ ባንክን በምክትል ገዥነት ያገለገሉትን አቶ ጌታሁን ናና መተካታቸው ይታወሳል፡፡ ልማት ባንክ ለእርሻ ባለሀብቶች በሰጠው ብድርና በሌሎች ምክንያቶች የተበላሹ ብድሮች መጠን ከ26 በመቶ በላይ መድረሱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች