Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥት ውሳኔዎች ግራና ቀኙን ያማተሩ ይሁኑ!

መንግሥት በዚህ ጥድፊያና ሁካታ ባለበት ጊዜ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን እንዳያስተላልፍ መጠንቀቅ አለበት፡፡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም የሚወጡ መመርያዎች ትኩረት በሕዝብ ጤና፣ ደኅንነትና በአገር ጥቅም ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ሰሞኑን የግል አውቶሞቢሎች በሙሉና በጎዶሉ ሰሌዳ ቁጥሮች በመለየት በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ መመርያ ሲወጣ፣ ምክንያቱ ግልጽ ባለመሆኑ በግል አውቶሞቢሎች ባለቤቶች ላይ ግርታ ፈጥሯል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ ዕርምጃዎች በመወሰዳቸው ምክንያት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ በጣም ቀንሶ እያለ፣ በምን አመክንዮ ነው ይህ መመርያ የወጣው የሚሉ ጥያቄዎች በዝተዋል፡፡ ለሥራ ከቦታ ወደ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ረጅም ርቀቶችን እንዴት አድርገው ነው አቅም በሚፈትን ወጪ የሚሸፍኑት ከሚለው ጥያቄ በተጨማሪ፣ ድንገተኛና አጣዳፊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለሚደርሰው ችግር ምን ዓይነት መፍትሔ ታስቧል? ሥራ በጣም በተቀዛቀዘበት በዚህ ጊዜ ከአምስቱ የሥራ ቀናት ላይ ተጨማሪ ቀናት ተቀንሰው ይቻላል ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የነዳጅ እጥረት ባላጋጠመበትና መንገዶች ጭር ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ውሳኔው በጥድፊያ ወጥቶ ከሆነም እንዲመረመር ሐሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡ አጣዳፊ ላልሆኑ ጉዳዮች መጣደፍ አይገባምና፡፡ ናይጄሪያ ይህንን መመርያ ብታወጣም ከቀናት ሙከራ በኋላ ለምን እንደተወችው ምክንያቱን ማወቅ እንደሚገባ ማሳሰቢያ እየቀረበ ነው፡፡

ሰሞኑን በትንሳዔ በዓል ምክንያት መንግሥትና ባለሥልጣናት የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ ያሳዩት ተነሳሽነት የብዙዎችን ድጋፍ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ትስስርንና ሰብዓዊነትን ለማጉላት የሚደረግ ጥረት ግን በዚህ መንገድ መቀጠል አይኖርበትም፡፡ በተቋምና በሲስተም የማይመራ አሠራር በርካታ ህፀፆች እንደሚያጋጥሙት የሚታወቅ ስለሆነ፣ መንግሥት ያሰባሰበውን ሀብት በጠንካራ ተቋምና ኃላፊነት ከሙያዊ ሥነ ምግባር ጋር በተላበሱ ባለሙያዎች ማስተዳደር ይጠበቅበታል፡፡ በፌዴራልም፣ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በተለያዩ ክልሎች የሚከናወኑ የሀብት ማሰባሰብም ሆነ የዕርዳታ ክንውኖች፣ በሚገባ ለታሰበላቸው ዓላማ የሚውሉት ሥርዓት ባለው መንገድ ሲመሩ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ተግባር ለብልሹ አሠራርና ለዝርፊያ ነው የሚያጋልጠው፡፡ የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ በሲስተም መመራትን፣ ጠንካራ አመራር ማግኘትን፣ ሥራን ከባለሙያ ጋር ማገናኘትን፣ ኢሞራላዊ የሥነ ምግባር ዝቅጠቶችን ማስወገድንና ጤናማ ማኅበረሰብና አገር እንዲኖር ማስቻልን ዓላማ የማድረግ አስፈላጊነትን ለማስገንዘብ ጭምር ነው፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ሌላው መረሳት የሌለበት፣ ለአገር አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ወገኖች ጉዳይ ነው፡፡ በሕክምናውና በሌሎች ማኅበረሰባዊ መስኮች በጎ ፈቃደኞችን ከማሰባሰብ በተጨማሪ፣ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ሊያቀርቡ የሚችሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በርካታ ልሂቃን ስላሉ እነሱን ማፈላለግ ተገቢ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በቀድሞው የዕርዳታ ማስተባባሪያ ኮሚሽን፣ በተለያዩ ታዋቂ የምርምር ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሎጂስቲክስና ትራንስፖርትና በሌሎች መስኮች የካበተ ልምድ ወገኖችን ማግኘት በጥድፊያ ጊዜ ከሚፈጠሩ ስህተቶች ለመማር ይረዳል፡፡ በልምድ ማነስና በዘፈቀደ ውሳኔዎች ላይ ላለመድረስ ያገለግላል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ኢቦላና ኮሌራ የመሳሰሉ ወረርሽኞች ባጋጠሙዋቸው አገሮች የሠሩ፣ ወይም ለእነሱ ዕገዛ ካደረጉ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ወገኖች ሳይቀሩ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የሕግ ባለሙያዎች መመርያዎችን በማውጣትና በተግባራዊነታቸው ጊዜ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል ስለሚረዱ፣ እንዲሁም በዘፈቀደ ሊፈጸሙ የሚችሉ ድርጊቶችን ለማስቆም ዕገዛ ስለሚያደርጉ ብቃት ያላቸውን ማፈላለግ ይገባል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ የጤናና የኢኮኖሚ ፈተና መጋረጡ ይታወቃል፡፡ መንግሥታት በተናጠል ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ትብብር እየተጠየቀም ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ በጤና መስክ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፣ ኢኮኖሚው ያንዣበበበት አደጋ አስፈሪ ስለሆነ ከተለያዩ የመስኩ ባለሙያዎች ጠንከር ያለ ድጋፍ ማሰባሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ምን ዓይነት የፖሊሲ ዕርምጃዎች ቢወሰዱ የፋይናንስ ዘርፉን ከኪሳራ መታደግ ይቻላል? የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ በምን ዓይነት ስትራቴጂ ቢመራ ከቀውስ መታደግ ይቻላል? የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በምን ዓይነት አመራርና አሠራር ከወቅቱ ችግር ያገግማል? የግብርናው ዘርፍ እንዴት ቢደረግ ምርታማ ሆኖ ይህንን ችግር ያልፋል? የአነስተኛና ጥቃቅንና መሰል ንግዶች ከወላፈኑ እንዴት ሊያመልጡ ይቻላቸዋል? ወዘተ ተብሎ ዘርፍ በዘርፍ መፍትሔ ለማግኘት ብቁ ባለሙያዎችን ማፈላለግ የግድ ነው፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ አመራሮች በመናበብ ወረርሽኙን የመከላከል ስትራቴጂውን ለመምራት የሚችሉት፣ ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸውን በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎችን የመጠቀም ዕድሉን ስታገኝ ነው፡፡ የአመራር ጥበብ መለኪያው ሁሉንም ሥራ ለማሳየት መትጋት ሳይሆን፣ መሥራት የሚችሉ ሰዎችን በሚመጥኑበት ቦታ ላይ በማስቀመጥ የሥራ ፍሬያቸውን እንዲያሳዩ ዕድሉን ማመቻቸትና የጎደለውን ለመሙላት መቻል ነው፡፡ በዚህ ወቅት በጣም ብዙ ክህሎት፣ ዕውቀት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎችን ለማግኘት አዳጋች አይደለም፡፡ መንግሥት ደመወዝ ወይም አበል ሳያስብላቸው አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች አሉ፡፡ ዳር ሆነው ከመተቸት ዕገዛ በማድረግ ስህተቶችን ለማረም የሚሹም አሉ፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነት በሙያና በልምድ የበለፀጉ ወገኖችን ከያሉበት ማፈላለግ ይጠበቅበታል፡፡ በከንቱ የሚባክን ፀጋ ይዞ መቸገር የለበትምና፡፡ እዚህ ላይ አሜሪካ ሰሞኑን የገጠማትን ፈተና እንደ ምሳሌ ማውሳት ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥትና በጤና ተቋማት አማካይነት ተግባራዊ የተደረገውን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ ቤት መቀመጥን በመቃወም አሜሪካውያንን በማሳመፅ ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አገሪቱን በቅርቡ ለመክፈት የጀመሩት እንቅስቃሴ አደገኝነት ውግዘት እያስከተለባቸው ነው፡፡ ከቻይና፣ ከዓለም የጤና ድርጅትና ከዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ጋር እሳትና ጭድ የሆኑት ትራምፕ፣ አሜሪካውያን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ ቤት መቀመጥን በመቃወም የተቃውሞ ሠልፍ እንዲወጡ በትዊተር ቅስቀሳ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ አሜሪካ በቅርቡ ወደ ሥራ መመለስ አለባት የሚሉት ትራምፕ ስቴቶችን የመክፈት ሥልጣን የእኔ ነው በማለት ከገዥዎች ጋር ቅራኔ ውስጥ ስለከተታቸው ነው እንዲህ ዓይነት ነውጥ ውስጥ የገቡት፡፡ ድርጊታቸው ወደ ሥራቸው በቶሎ ለመመለስ በሚፈልጉ ዘንድ ድጋፍ ቢያስገኝም፣ ከ700 ሺሕ በላይ በኮሮና የተጠቁ፣ ከ42 ሺሕ በላይ ሞተውና አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚሞቱባት አሜሪካ፣ የትራምፕ ድርጊት ሥርዓተ አልበኝነት ነው ተብሎ በብዙዎች እየተነቀፈ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በየግዛቱ የሚኖረው ሕዝብ አገሩን እንደሚወድና ፍላጎቱ ከቤት ወጥቶ መሥራት ስለሆነም መታፈን የለበትም ብለው ሙግት ማቅረባቸው፣ መንግሥት ለመምራት ጨርሶ ኃላፊነት የማይሰማቸው እንደሆኑ እየተነገረ ነው፡፡  ከብዙዎችም ወቀሳና ትችትም እየቀረበባቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ውዝግብ ውስጥ ይገባል ተብሎ ባይጠበቅም፣ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ለውዝግብ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ እንደማይጠፉ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ በየጊዜው በተለዋወጡ መንግሥታት የሚታወቁት ደንታ ቢስነት፣ መርህ አልባነትና ማናለብኝነት ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሲያደርጉ መኖራቸው አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች በዚህ ዘመን ማጋጠም ስለሌለባቸው በተቻለ መጠን በባለሙያዎች ዕገዛ፣ ሁሉንም ወገኖች የሚያግባባና በወረርሽኙ ላይ የተጀመረውን የመከላከል ዘመቻ የሚያቀላጥፍ አሠራር መዘርጋት ይጠቅማል፡፡ መንግሥት መመርያዎችን ሲያወጣም ከጥድፊያና ከሁካታ ይልቅ በጥናት ላይ ስለሚመሠረት አሠራሩ ግልጽ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል፡፡ ከማኅበረሰቡ የሚገኘው ግብረ መልስም ለበለጠ ሥራ ያነሳሳዋል፡፡ ወቅቱም የሚፈልገው በአስተዋይነት ላይ የተመሠረተ አሠራርና አመራር ስለሆነ፣ መንግሥት ውሳኔዎቹ ግራና ቀኙን ያማተሩ እንዲሆኑ መትጋት አለበት! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...