Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ የተበደረው የተወሰነ ዕዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲተላለፍ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከንግድ ባንክ የተበደረው ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት አሥርት ዓመታት ላከናወናቸው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሮ መመለስ ያልቻለው የተከማቸ ዕዳ፣ ከፊሉ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲዛወር መንግሥት መወሰኑ ታወቀ።

ውሳኔውን ያሳለፈው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኘውና በቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በኋላም በአሜሪካ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ሰብሳቢነት የሚመራው፣ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ኮሚቴ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

በውሳኔው መሠረት የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ አማራጮች ተበድሮ ለመክፈል ካልቻለው የተከማቸ ዕዳ ውስጥ የተወሰነው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲተላለፍ፣ የተቀረው ዕዳም ደረጃ በደረጃ የመክፈል ኃላፊነት ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚተላለፍ ለማወቅ ተችሏል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ከፍተኛ ኃላፊ እንዳስረዱት፣ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲዘዋወር የተወሰነው ዕዳ በቀጥታ ከባንኩ የተወሰደ ብድር ባለመሆኑ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር የሚተላለፍ እንደሆነ፣ በዚህ መንገድ የሚስተናገደው ዕዳም ለባንኩ የሚከፈል ሳይሆን መንግሥት በኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የሚኖረው አዲስ የኢንቨስትመንት ድርሻ እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል።

ይህ የሆነበትም ምክንያት የተወሰነው የኮርፖሬሽኑ ዕዳ መንግሥት ከተለያዩ የገንዘብ ምንጮች ያገኘውን የልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመልሶ ማበደር እንዲያስተዳድር በሰጠው ኃላፊነት መሠረት፣ ኤሌክትሪክ ኃይል የተበደረው በመሆኑ ነው። ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ ተበድሮ ያልከፈለው 32 ቢሊዮን ብር በዚህ ዓመት ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲዘዋወር እንደሚደረግ ኃላፊው ተናግረዋል።

የተቀረውና በቀጥታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንድ ተበድሮ ያልተከፈለው ዕዳ 20 በመቶውን የመክፈል ኃላፊነት፣ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ደረጃ በደረጃ እንዲዘዋወር እንደተወሰነም ጠቁመዋል።

ኤሌክትሪክ ኃይል ከባንኩ ያገኘው ቀጥታ ብድሮች የመክፈያ ጊዜ መንግሥት በተለያዩ ወቅቶች ባሳለፋቸው ውሳኔዎች በተደጋጋሚ የተራዘሙ በመሆኑ፣ ይኸውም በዋናው ብድር ላይ የሚከፈለውን የወለድ ክፍያ በማናሩ አጠቃላይ የዕዳ መጠኑን ከፍተኛ እንዳደረገው ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት ዕዳውን መክፈል እንዳልቻለ፣ ከዚህ በተጨማሪም ከአገር ውስጥ ብድር በላይ የሆነ የውጭ ብድር የመክፈል ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የተከማቸ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልመለሱት የዕዳ መጠን ወለድን ጨምሮ 425 ቢሊዮን ብር እንደሆነ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣው የአገሪቱ አጠቃላይ ዕዳ የሚዘረዝር ሰነድ ያመለክታል።

ከዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፣ ከተቀረው የዕዳ መጠን ውስጥ አብዛኛው የሚመለከተው የስኳር ኮርፖሬሽንንና የባቡር ኮርፖሬሽንን እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ኃይልን ዕዳ የመክፈል ኃላፊነት እንዲወስድ መወሰኑ በቀጣዮቹ ዓመታት የሚኖረውን የመንግሥት ወጪ እንደሚያንርና የዋጋ ንረት በኢኮኖሚው የማስከተል አቅም እንዳለው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን፣ ይኼንን አለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ባንክን ጤናማነት እንደሚጎዳው አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች