የግል ትምህርት ቤቶችና ወላጆች በመመካከር ችግር እንዲፈቱ ተጠየቁ
የኢኮኖሚውን ዘርፍ መዳከም ሊያራዝሙ ከሚችሉ ሁኔታዎች አንዱ ተመጣጣኝ የሆነ የኅብረተሰብ ጤና ዕርምጃ አለመውሰድ ነው ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት አስታወቁ፡፡ ‹‹ለኢኮኖሚያችን መረጋጋት ሲባል በሕክምናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ፣ ተመጣጣኝ የመከላከል ዕርምጃ መውሰዳችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን የከፋ ጫና ለመከላከል አስፈላጊ ዕርምጃዎች መውሰድ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና ማስጠበቅ፣ ዘላቂ በሆነ መንገድ ገቢ እንዳይቋረጥ ማድረግ፣ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚያደርጉ አሠራሮችን ማስፋፋት፣ የመሠረታዊ አቅርቦቶችን የግብይት ሥርዓት ማረጋጋት፣ እንዲሁም ለአምራች ዘርፎች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
‹‹ለምግብ ዋስትናችን የግብርናውን ዘርፍ አምራችነት ማረጋገጥ ወሳኝነት አለው፡፡ ምንም ዓይነት የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ እንዲሁም የፀረ ተባይ መድኃኒቶች አቅርቦት ሳይቆራረጥ የሚቀጥል ይሆናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የግል ትምህርት ቤቶች ከተማሪዎች ወላጆች ጋር በመመካከር ወቅታዊ ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱ ትምህርት ሚኒስቴር ጠየቀ፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች ጉዳይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማስመልከት ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶ/ር) ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከልና ከፍተኛ አደጋ እንዳይደርስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በግል ትምህርት ቤቶችና በወላጆች የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ሳቢያ በአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ጥናት በማድረግና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር፣ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ማሳለፉንና የውሳኔውም ዋና ዓላማ በግል ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው ትምህርቱ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል፣ የግል ትምህርት ቤቶች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከወላጅ ኮሚቴ ጋር በመሥራት ችግሮችን በጋራ እንዲወጡ ለማስቻል፣ በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ መምህራንና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ችግር እንዳይጋለጡ ለማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የተማሪዎች ጤንነትና የትምህርት ተደራሽነትን፣ እንዲሁም የትምህርት ቤት ክፍያን በተመለከተ ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ችግሩን ምክንያት በማድረግ ወላጆች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ሳይሆን፣ በጋራ ተረዳድተው በመመካከር ችግሩን መፍታት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ለሚያስተዳድሯቸው ሠራተኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ደመወዝ መክፈል እንዳለባቸው በውሳኔው የተካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡