መንግሥት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል ይቻል ዘንድ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ መንግሥታዊና የግል ተቋማት እንዲሁም ባለሀብቶችና አትሌቶች መንግሥት ለሚያደርገው ቅድመ መከላከል ሥራ የሚያደርጉት ድጋፍና ዕገዛ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ የዓለምና የኦሊምፒክ ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር መገናኛ አካባቢ ያስገነባችውን ባለ 12 ፎቅ ሕንፃ መንግሥት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ለተያያዘ አገልግሎት በጊዜያዊነት እንዲጠቀምበት አበርክታለች፡፡ መሠረት ሕንፃውን ለንግድና መሰል አገልግሎት ለመጠቀም ኪራይ ለከፈሉ ግለሰቦች የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ማድረጓም ተነግሯል፡፡ አትሌቷ ከወገኔ የሚበልጥ ነገር የለም በሚል ፎቋን ለሦስት ወራት ያስረከበችው ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ነው፡፡ ዋና ዓቃቤ ሕጓ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፣ መሠረት ደፋር ያደረገችው ተግባር በተለይ መንግሥት በወረርሽኙ ለሚጠቁ ወገኖች ማቆያ ቦታ እጥረት እንዳይገጥመው ያለመ፣ ወገንን በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡