Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኮቪድ 19ን ለመከላከል የስፖርት ቤተሰቡ የሰጠው ምላሽ

ኮቪድ 19ን ለመከላከል የስፖርት ቤተሰቡ የሰጠው ምላሽ

ቀን:

ኮቪድ 19 በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እያስከተለ ባለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት አገሮች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መከላከል ይቻል ዘንድ የሚደረገው ድጋፍና ዕገዛ በተጠናከረ መልኩ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ዕገዛውም ሆነ ድጋፉ ከታይታ በፀዳ አግባብ ማዕከላዊነት ያለው እንዲሆን የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ባደረገው ጥሪ መሠረት ከስፖርቱ ዘርፍ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ቫይረሱን ለመከላከል ዕገዛና ድጋፍ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት ይጠቀሳል፡፡ አሶሴሽኑ በአባላቱ አማካይነት ከተለያዩ ክለቦችና ተጫዋቾችና ሙያተኞች ያሰባሰበውን 6,316,829.90 ብርና የተለያዩ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለዕርዳታ አሰባሳቢ ብሔራዊ ኮሚቴ አስረክቧል፡፡

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች (ዋሊያዎቹና ሉሲዎቹ) አሠልጣኞችና ሌሎች ሙያተኞች ቀደም ሲል በተከናወኑ ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ለዚሁ ዓላማ ያሰባሰቡትን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና የእግር ኳሱ ዘርፍ በዚህ መልኩ በተበታተነ አካሄድ ሳይሆን ማዕከላዊነቱን ጠብቆ መሆን ነበረበት ሲሉ የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

ዓላማው በአንድም ሆነ በሌላ የተቀደሰና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ “እንደ አካሄድ በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ውክልናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ለሁሉም ክልሎች መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፤” በማለት ድጋፉም ሆነ ዕገዛው ማዕከላዊነትን ጠብቆ ቢከናወን ለዘርፉም ሆነ ለድጋፉ ጥንካሬ ይበል የሚያሰኝ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ድጋፉን ያደረገው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ሚያዝያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም  ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተሰባሰበው ደግሞ፣ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች፣ ከከፍተኛ ሊግና ሌሎችም ቡድኖች እንዲሁም በአሶሴሽኑ የባንክ አካውንት በመጠቀም በአጠቃላይ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወረርሽኙን ለመከላከል ለተቋቋመው ብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ አስረክበዋል፡፡ ሰብሳቢው ከስፖርቱ ዘርፍ የተደረገው ድጋፍ በዚህ እንደማያበቃ፣ ይልቁንም አትሌቶቹና ሙያተኞቸ ተሰሚነቱና ዕውቅናው ስላላቸው ወደ ኅብረተሰቡ ወርደው ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ  የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር እንዲሁም የአሶሴሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ መስፍን በሥነ ሥርዓቱ ተገኝተዋል፡፡ ኮሚሽነሩ አቶ ኤልያስ ሽኩር ድጋፉን አስመልክቶ፣ “ይህን ክፉ ጊዜ እርስ በርስ በመተሳሰብ መንግሥት፣ የሕክምና ባለሙያዎችና የእምነት አባቶች የሚሰጡትን መልዕክት ተቀብለን ሥራ ላይ ማዋል ከተቻለ በአሸናፊነት የምንወጣው ሲሆን፣ ካልሆነ ግን አላስፈላጊ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ሁሉም ልብ ሊል ይገባል፤” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በአሶሴሽኑ ትብብር የተጀመረው ድጋፍና ዕገዛ ቀጣይነት እንደሚኖረው እምነታቸው መሆኑን ያስታወቁት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ “አንዳንዶች በወረርሽኙ ምክንያት የተቋረጠው እግር ኳስ መቼ እንደሚጀምር የሚጠይቁኝ አሉ፣ እውነት ነው በግሌ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴያችን በፍጥነት መመለስ እንዳለብን እመኛለሁ፣ ሆኖም አሁን ላይ ቅድሚያ ሰጥተን ልንታገለው የሚገባው ወረርሽኙን ነው፤” በማለት የእግር ኳሱ ቤተሰብ ለዚህ አሳሳቢ ወረርሽኝ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...