Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኮሮናና የቤት ኪራይ ጣጣ!

ኮሮናና የቤት ኪራይ ጣጣ!

ቀን:

በብሩክ ፈለቀ

‹‹በዚህ የኮቪድ 19 ወቅት መፍራትና መጨነቅ መኖሩ ምንም አይደለም፡፡ ስለሚሰማን ነገር መነጋገር ደግሞ ጭንቀትን ያረግባል፤›› የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮና ወረርሽኝን አዕምሮአዊ ተፅዕኖውንና ላያችን ላይ ያረበበውን የፍርኃት መንፈስ በተመለከተ በድረ ገጹ ላይ ያሠፈረው የመነሻ ሐሳብ ነበር፡፡ በእርግጥም በዚህ ወቅት በፍርኃት መሸበባችን፣ ሁሌም ስለበሽታው ማውራታችን ምክንያታዊ ነው፡፡ በጽሑፉ ላይ እንደሰፈረው ስሜቶቻችንና ልምዶቻችንን መለዋወጥ በትንሹም ቢሆን አዕምሮአዊ ሸክማችንን ቀላል እንደሚያደርገው ዕሙን ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ላይ ደግሞ ‹የቤት ኪራይ ደረሰ!› ጭንቀት ተጨምሮበት ስሜቱ ምንኛ ከባድ ይሆን?

ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የገጠመኝን ልናገር፡፡ ከአንድ ጫማ ጠራጊ (ሊስትሮ) ጋር ጫማዬን እያስጠረግኩ ወግ ይዘናል፡፡ ያው በዚህ ሰሞን  እንደተለመደው ሥራ እንዴት ነው? ወረርሽኙ እንዳይተላለፍብህ ምን ጥንቃቄ እያደረግህ ነው? የሚሉትን ሐሳቦች ተለዋወጥን፡፡ በእርግጥም በሽታው ለዕለት ጉርስ የሚሮጡትን ለፍቶ አዳሪዎችን ገቢ በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉ ዕሙን ነው፡፡ ይኼ ልጅና መሰሎቹም ራሳቸውን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ ከቤት መዋል ያልመረጡበት ዋነኛ ምክንያት ግን፣ የቤት ኪራይ ጉዳይ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ ‹‹የቤት ኪራይ ቅናሽ ፍለጋ የምንኖረው ሱሉልታ ከተማ  ነው፡፡ ሰሞኑን ትራንስፖርት ስለተዘጋ ከቤታችን እዚህ ድረስ በእግራችን ነው የምንመጣው፡፡ እቤት ውለን የቤት ኪራይ ከምናችን ልንከፍል ነው?›› ብሎኛል፡፡ ታዲ ያ የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ላይ የቤት ኪራይ ደረሰብኝ ጭንቀት ተጨምሮ ስንቱን አናውዞት ይሆን?  ከወር ደመወዝተኛው እስከ ቀን ሠራተኛው፣ ከባለሱቁ እስከ ድርጅት ባለቤት ከኮቪድ 19 ቫይረስ ጎን ለጎን የቤት ኪራይ ዋነኛ አጀንዳው አይመስላችሁም?

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው ትልልቅ ከተሞች የመኖሪያ፣ የንግድና  የቢሮ ኪራይ ዋጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ የከፋ ሁኔታ በወረርሽኝ፣ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በመሳሰሉት ድጋፍ ሲያገኝ ደግሞ ማኅበረሰቡን የከፋ ችግር  ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባችን ትልቁ የዋጋ ንረት (Infilation) መገለጫ የቤት ኪራይ፣ የቤት ሽያጭና የመሬት ዋጋ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በእርግጥም በአዲስ አበባችን አንድ ካሬ ሜትር በ350 ሺሕ ብር ወይም ከአሥር ሺህ ዶላር በላይ መሸጡን ተመልክተናል፡፡ ይህም ዋጋ ከተማችንን እንደነ ኒውዮርክ ካሉ ከተሞች በላይ ዋጋዋ የናረ መሆኑን አሳይቶናል፡፡

የመኖሪያ ቤት ተከራዮች

እንደሚታወቀው ባለፉት 28 ዓመታት የተፈጠረው በተለይም ደመወዝተኛው የማኅበረሰብ ክፍል መኖሪያ ቤት ተከራይቶ የሚኖር ነው፡፡ በፊውዳሉ ዘመን የከተሜው ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር፣ አገሬው ለመኖሪያ የሚሆነውን ቤት በከተማ ለመገንባት መሬት ከመንግስት፣ ከከበርቴው በጣም በርካሽ ዋጋ መግዛት ይችል ነበር፡፡ በደርግ ዘመንም ቢሆን የመንግሥት ሠራተኞች በረጅም ጊዜ በሚከፈል የመንግሥት ድጋፍ የማኅበር ቤት ይገነቡ ነበር፡፡ ለዚህም ማስረጃ መጥቀስ ካስፈለገ የአውራ ጎዳና፣ የማረሚያ ቤት፣ የቴሌ፣ የመብራት ኃይል፣ ወዘተ. ሠራተኞች ሠፈር፣ ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣ መገናኛ፣ ገርጂ፣ ሳሪስ፣ ወዘተ ዞር ዞር ቢሉ ሚጢጢዋ ጡረታቸው ባትበቃቸው ባላቸው ሰርቪስ ቤት ቢጤ ገንብተው በማከራየት ኑሮአቸውን የሚገፉ ብዙዎች አሉ፡፡ የኪራይ ቤቶችም ተገነብተው በነፃ በሚባል ኪራይ ቀርቦ የመጠለያ ፍላጎትን ለማሟላት ተሞክሯል፡፡ 

ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ግን ባልጠፋ ቦታና መሬት በፖሊሲ፣ በቢሮክራሲ፣ በሙስና፣ ወዘተ. ደሃውና ደመወዝተኛው የመሬት ያለህ እንዲል ተደርጓል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ ተሞክሮ የነበረው የቤት ማኅበር እንዲቆም ተደርጎ መሬት እየተሸነሸነ በሊዝ ብቻ እንዲቸበቸብ ተደርጓል፡፡ ይህም መሬትን የተወሰኑ ቡድኖችና አቅም ያላቸው ብቻ እንዲቀራመቱት ምክንያት ሆኗል፡፡ በ1997 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ነዋሪ መኖሪያ ቤት ካሰኘው ፎቅ ላይ መንጠልጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው ተብሎ ሲወሰንበት በብዙ ሺዎች ለምዝገባ ተመሙ፡፡ ፕሮግራሙ ድፍን 15 ዓመታት ቢሞሉትም በግንባታው መጓተት፣ በጥራት ችግር፣ በዕጣ አወጣጥ አድሎአዊነት፣ የባለዕጣው የቅድሚያ ክፍያ ለመክፈል እጅ በማጠር፣ ኮንዶሚኒየሙን ከተረከቡ በኃላ ዕዳውን ለመክፈል ባለመቻልና በተለያዩ ምክንያቶች ባለ ብዙ መሬቶቹ፣ ባለብዙ ቤቶቹ፣ ባለብዙ ፎቆቹ ብዙዎቹን ቤቶች በእጃቸው አስገብተዋቸዋል፡፡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራምም ቢመጣም እነዚሁ አካላት በዘመድ አዝማድ ስም ተመዝግበው፣ ሙሉ ክፍያ የመክፈል አቅምም ስላላቸውም  ዕድለኛ ሆነዋል፡፡ ወጣም ወረደ ታዲያ የአዲስ አበባን የቤት ኪራይ ዋጋን የሚተምኑት እነዚሁ አካላት ሆነዋል፡፡

ለማንኛውም ደመወዝተኛውም ሆነ ለፍቶ አዳሪው የደመወዙንና የገቢውን ከግማሽ ፐርሰንት በላይ ለቤት ኪራይ ክፍያ የሚያውለውን የአገሬ ሰው ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ‹እኛ እንዲያውው ለፍተን ለቤት ኪራይ ነው!› እያለ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚኖረው ብዙ ነው፡፡ እኔ ራሴ የማውቀው በጥሩ የሙያ ዘርፍ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ ወዳጄ የደመወዙን 75 በመቶ ለቤት ኪራይ እንደሚከፍል አጫውቶኛል፡፡ ‹የፊልድ ሥራ በጠፋ ግዜና በውጭ የምሠራቸው የማማከር ሥራዎች በማይገኙ ጊዜያት ወር መድረስ  እንደ ተራራ ያህል ከባድ ይሆንብኛል፤› ብሎኝ ያውቃል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ለደመወዝተኛም ሆነ ለለፍቶ አዳሪዎች ኮሮና ቀናቸውን አጨልሞባቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ ታዲያ እንዴት እንለፈው?

የንግድ ቤቶች

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የአንድ የንግድ ተቋም ባለቤት የሆነ ወዳጃችን፣ ‹‹የእኛ ማገገም በሥራችን የምናስተዳድራቸው ሠራተኞች ህልውና ነው፡፡ አከራዮቻችን የአንድ ወርና የሁለት ወር ቢተውን፣ ቢቀንሱልን ወይም ይኼ ጊዜ እስኪያልፍ ቢታገሱን ከሕይወታቸው ላይ አንዲት ነገር አይቀንሱም፡፡ እኛ ግን ካቃተን ከራሳችን ቤተሰብ ባለፈ የሠራተኞቻችንንም ሕይወት እናቃውሳለን፤›› ነበር ያለው፡፡ ይህ ወዳጃችን ከአሥር በላይ ሠራተኞች እንደሚያስተዳድር ልብ ይሏል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ ባለትዳሮችም ሆኑ የሚረዱዋቸው ቤተሰቦች ያላቸውን በትንሹ በሦስት ብናባዛው የሰላሳ ሰዎች ሕይወት ተቃወሰ ማለት ነው፡፡

የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ገባ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ የከተማችን የንግድ ተቋማት ቀስ በቀስ ባዶ እየሆኑና እየተዘጉ እንደሆነ ከእኛ በላይ ማን እማኝነት ይቆማል? እኔ የምንቀሳቀስበት ከሃያ ሁለት፣ ኤድና ሞል፣ ቦሌ ድልድይ ድረስ ያሉት ብዙ የንግድ ተቋማትን ያቀፉ ፎቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሻይ ቤቶች፣ ልብስ ቤቶች፣ ወዘተ. ወና ሆነው እንደሚውሉ አስተውዬአለሁ፡፡ ታዲያ በቀጣይነት የቤት ኪራያቸውን በምን መንገድ ሊከፍሉ ይችላሉ?

ምን ይሻላል?

ይኼንን አስቸጋሪ ጊዜ ልናልፈው የምንችለው በአካል ተራርቀን በመንፈስ ግን አንድ ሆነን ከቆምን ብቻ ነው፡፡የእያንዳንዳችን ሀብት የሁላችን፣ የእያንዳንዳችን ችግር የሁላችን መሆን አለበት፡፡ ›ምን ይሻላል? ብዬ ላነሳሁት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  በተመለከተ በፌስቡክ ገጻቸው ካኖሩት ጽሑፍ ላይ መልሱን ስላገኘሁት እንደ ወረደ ገልብጨዋለሁ፡፡ ‹‹በዚህ አጋጣሚ ስማቸውን ባለመያዜ ይቅርታ እየጠየቅኩ የድሬዳዋ አከራይ እናት፣ አንድ በአዲስ አበባ አፓርትመንት የሚያከራዩ አባት፣ አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬና ቤተሰቡ፣ አንዳንድ የኮንዲሚኒየም አከራዮች፣. . . ሌሎችም እንደምትኖሩ በመተማመን ፈር ቀዳጅ የሆነ ወቅታዊና የጀግና ዕርምጃ ወስዳችኋልና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!›› በነገራችን ላይ ይኼንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ መደምደሚያዬ ላይ ለመንግሥትም ‹ከራስ በመጀመር ምሳሌ መሆን አለባችሁ› የምትል መልዕክት ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ ሳለሁ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለተከራዮች በግማሽ መቀነሱን ሰማሁ፡፡  የተለያዩ አከራይ ባለሀብቶችም ይኼን ያህል ገንዘብ ረዱ፣ የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎችን ለገሱ፣ በደጃቸውም ላይ ነዳያንን አበሉ. . . የሚሉ ዜናዎችን በሚዲያዎች እየሰማን ነው፡፡ በእጃችሁ ላይ ያሉትን ተከራዮችንስ ምን አሰባችሁላቸው  ብለን ልንጠይቃቸው ይገባል፡፡

ዓለማችን ብዙ ከባድ ጊዜዎችን አልፋለች፡፡ እንዲሁም የኮሮና ወረርሽኝን እናልፈዋለን፡፡ የቤት ኪራይ ንረትንስ? በተለይም የአዲስ አበባ ሕዝብ ከሚመገበው፣ ከሚጠጣው ውኃና ከሚጠቀምበት የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ ከሚለብሰው፣ ወዘተ በላይ አቅም ያሳጣው የመጠለያ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት ፖሊሲውን፣ መመርያውን፣ ዕቅዱን መመርመር ይጠበቅበታል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመለከትነውም ነባራዊ እውነታ ካለፉት 28 ዓመታት ትምህርት የተወሰደበት አይመስልም፡፡ የሊዝ ሽያጭ ቆሟል፡፡ በምን አግባብ እጃቸው እንዳስገቡት ባናውቅም ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን አጥረው ግንባታ የጀመሩ ተመልክተናል፡፡ 15 ዓመታት የቆጠቡ የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች ግራ ተጋብተዋል፡፡ አዲስ የተሠሩት ይቅርና በኦዲት የተገኙ ሕገወጥ የሆኑ ከሦስት ሺሕ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣም አልወጣባቸው፡፡ ለማን እንደተለገሱም አልታወቀም፡፡ የኮዬ ፈጬና ሌሎች ቦታዎች ባለዕድለኞች ከብዙ ግርግር በኋላ የማስተላለፍ ሥራው ተጀመረ ሲባል ቆሟል፡፡ ለቀሪዎቹ 20/80 ተመዝጋቢዎችም መሀል ከተማ ይገነባል ተብሎ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ ከዚያ ባለፈ የሰማነው ነገር የለም፡፡ ተሳክቶ ቢሠራስ ይገባቸዋል ብለው ይሰጡናል ወይ? ይህ የሁሉም ተስፈኛ ጥያቄ ነው፡፡

ለማንኛውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለማምጣት ጠንክሮ ሊሠራ ይገባል፡፡ የተለያዩ አማራጮችም ሊታዩ ግድ ይላል፡፡ የወቅቱን የተከራዮች ጭንቀት ለመጋራት ግን፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን መረዳዳቱና መደጋገፉ ነው፡፡ ድሆችን እንርዳ፡፡ በአካቢያችን ላሉት አቅመ ደካሞች እንድረስላቸው፡፡ የቤት ተከራዮቻችንን ዕዳ እንካፈላቸው፡፡ ከቻልን አናስከፍላቸው፡፡ ካልቻልን ቅናሽ እናድርግላቸው፡፡ ያም ካልሆነ ይህ ጊዜ እስኪያልፍ እንታገሳቸው፡፡ በዚህ ወቅት ተከራዮችን ከቤት ማስወጣት ፈጣሪም፣ ታሪክም፣ ሕግም ይቅር የማይሉት ወንጀል ነው፡፡› ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካስተላለፉት መልዕክት ላይ በድጋሚ ተዋስኩ፡፡

እግዚሐብሔር ኢትዮጵያን ይማር!!!

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...