በሀብታሙ ግርማ ደምሴ
ይህችን ጽሑፍ ለማዘጋጀቴ ምክንያቱ የሕወሓት አፈ ቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ አስመልክቶ የግል ዕይታዬን ባሰፈርኩበት አንድ የማኅበራዊ ድረ ገጽ (Facebook) ጽሑፌ ላይ የማከብረው ጓደኛዬና የሥራ ባልደረባዬ ተፈራ ተክሌ የሰጠው አስተያየት ነው። ለዚህኛው ጽሑፌ ጭብጥ መነሻው የቀደመው ጽሑፌ በመሆኑ አንባቢያን መነሻ ሐሳብ ይይዙ ዘንድ በፌስቡክ ገጼ ላይ ሊያገኙት ይችላሉ።
ሕወሓትና ግራ የመጋባት ፖለቲካው
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፣ በተለይ ሕወሓት በከፍተኛ የፖለቲካ ግራ መጋባት ሕመም እየማቀቀ ነው። የዚህች ጽሑፍ ጭብጥ ሕወሓት የገባበትን የፖለቲካ ቅርቃር በደበበ ሰይፉ ዝነኛዋ ግጥም ‹ለምን ሞተ ቢሉ› መነሻ (ዳራ) እና ይዘት መግለጽ ነው፡፡ ዓላማዬም ሕወሓት ከገጠመው የፖለቲካ ግራ መጋባት ችግር ይወጣ ዘንድ ምክር ቢጤ ለመስጠት ነው፡፡ የጽሑፉ መንፈስ ግልብ ተቃውሞ ወይም ጭፍን ጥላቻ ሳይሆን የግል አስተሳሰብን በቅንነትና በነፃነት መግለጽ ብቻና ብቻ ነው። በእኔ ግንዛቤ ሕወሓት የገባበትን የፖለቲካ ቅርቃርና ከዚህ የመውጫ ቀዳዳ በደበበ ሰይፉ ግጥም መነሻ (ዳራ) ውስጥ እናገኘዋለን።
ገጣሚ፣ መምህር፣ ደራሲና ሐያሲ ደበበ ሰይፉ (1942 እስከ 1992)
ኮሙዩኒስቱ ደበበ ሰይፉ እንደሚታወቀው በሕይወት ሳለ ብዙ በደል ደርሶበት ነበር፡፡ በተለይም ረጅም ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢያስተምርም ጡረታውን እንኳ አላገኘም (የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ግን ደበበ ጡረታ ያልተከበረለት የመንግሥት አሠራር በሚያዘው መሠረት የአስተዳደር ኃላፊ ሆኖ በሠራበት ዓመታት በስሙ ተመዝግቦ የወሰዳቸውን የሕዝብ ንብረት ለመመለስ ፈቃደኛ ስላልነበረ ነው ይላሉ)።
የሆነ ሆኖ ደበበ ብሶተኛ አልነበረም፣ በበደሉት ሰዎች ላይ አላቄመም፡፡ ምናልባት በሕይወቱ ጉዞ አንዳንድ ቅሬታዎች ቢኖሩትም፣ ለጥፋቶቹ የእርሱ ድርሻ እንደ ነበረበት ያመነ ይመስለኛል። ይህም ሆኖ ግን ደበበ ‘በዳዮቹን’ ከመውቀስ፣ በእነርሱ ላይ ከመዛት ይልቅ ወደ ራሱ ተመለከተ፡፡ እናም ከራሱ ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ተማከረ፡፡ የምክክሩ ውጤት ይህ ነበር፡፡
‘. . .እኔ አንድ ሰው ነኝ፣ የማምንበት ሐሳብ አለኝ፣ ነገር ግን የእኔ አስተሳሰብ ዘመኑን እንዲዋጅ ተፅዕኖ ፈጥሬ ዘመኑን መቀየር አልችልም፣ የማላሸንፈውን ጨዋታ አልጫወትም፣ አንድ ምርጫ ነው ያለኝ፣ ወይ በአቋሜ መሞት አልያም አቋሜን ቀይሬ ዘመኑን መስሎ መኖር።’ በነገራችን ላይ ደበበ ወግ አጥባቂ ኮሙዩኒስት (Old Communist) የሚባል ዓይነት ሰው ነበር፡፡ እርሱ ከኮሙዩኒስት አስተሳሰብ ውጭ ሌላውን ለመቀበል ቀርቶ መስማት የማይፈልግ አክራሪ ማርክሲስት ሌኒኒስት ነበር።
ደበበ ኮሙዩኒስት እንደ መሆኑ በዚህ ርዕዮት የተጠመቀ ሰው አንዱ መገለጫ ደግሞ ሐሳብን ከዘመን ጋር ማስተካከል አለመቻሉ ነው፡፡ ኮሙዩኒዝም ለተከታዮቹ እኮ ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ በሃይማኖት መንገድ ደግሞ ለእምነት መሞት ፅድቅ ነው፡፡ ደበበ ለኮሙዩኒዝም ሲል ከዘመኑ ጋር ተኳረፈ፡፡ እናም የዘመን ኩርፊያው ጠንቶበት ሞተ። እንግዲህ ደበበ ለእምነቱ ሲል ከዘመን መጣላት ነበረበት፡፡ ከዘመን መጣላት የማያሸንፉት ጨዋታ መሆኑ ገብቶታል፡፡ የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም የሚለውን አገርኛ አባባል ደበበ ተቀብሎታል፡፡ በመሆኑም ለእምነቱ ቀናዒ ስለነበር ዘመኑን ከመምሰል ይልቅ ሞቱን መረጠ።
ደበበ የዘመን (የጊዜን) አሸናፊነትን ተቀብሎ፣ ነገር ግን በአቋሙ መፅናቱን በአንድ የገለጸበትን ‹. . .ለምን ሞተ ቢሉ. . .› ግጥሙን ጻፈ፡፡ ይህ ግጥም በደበበ ሰይፉ ሐውልት ላይ ተቀርጿል።
‹‹ለምን ሞተ ቢሉ. . .
‘ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ
ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ››
ሕወሓትና ደበበ ሰይፉ ምንና ምን ናቸው?
አንድነታቸው ሁለቱም ኮሙዩኒስቶች ናቸው፡፡ በኮሙዩኒስት አስተሳሰባቸው ምክንያት እናምንበታለን ከሚሉት ሐሳብ ውጪ ሌላን ሐሳብ የመስማት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ደበበ ሰይፉና ሕወሓት አንድ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው። ደበበ ከአቋሙና ከዘመን መታረቅ አንዱን መርጧል፡፡ እንደ ግለሰብ ለቆመ ሰው ይህን መምረጥ ይችላል፡፡ የደበበ ምርጫ አቋሙ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚከፈለውን ለመክፈል ፈቃደኝነቱ ነበረው፣ እንደሚሸነፍ ቢያውቀውም ምርጫው ነበር።
እነ ጌታቸው ረዳ ግን ሁለት ወደዱ፡፡ አንዱ የሕይወት ሕግ መምረጥ መሆኑን ዘነጉት፡፡ ከምንም በላይ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ረሱትና የግል አቋማቸውን በግድ የሕዝብ ለማድረግ ሞከሩ፣ እየጣሩ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ የሚፈልገው ሌላ እነርሱ የሚሉት ሌላ፡፡ በመሠረቱ በግል አቋም አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተቀብሎ መኖር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ እንደ ፖለቲከኛና እንደ ድርጅት በዚህ ሐሳብ ቢያንስ ኢትዮጵያን መምራት አይቻልም።
ፖለቲካ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የራስን ሐሳብና ምቾት መስዋዕት መሆንን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ቢቻል ራስን ከዘመኑ ጋር አርቆ (አስታርቆ) የፖለቲካ መስመርን መቀየር ነው። እንዳለ መታደል ሆኖ ግን ለጌታቸው ረዳና ጓዶቹ ይህ አይቻልም፡፡ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተምህሮ ሃሳብ መቀየር (ከዘመን ጋር ማስታረቅ) አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ አድኃሪነት (Reactionary) ነው።
በመጨረሻም
በመጨረሻም አንድ የሚገርመኝን ወይም የሚያሳዝነኝን ነገር ለአንባቢያን ላካፍል፡፡ ይህም በሕወሓት ቤት አንድ መካሪ መጥፉቱና ወይም ምክር የሚሰማ አለመኖሩ ነው።በእኔ እምነት ነፍሱን ይማረውና መለስ ዜናዊ በሕይወት ቢኖር ኖሮ አሁን ዶ/ር ዓብይ የሚመሩትን ለውጥ ያህል እንኳ ባያመጣ፣ ነገር ግን ቢያንስ አብዮት እንዳይነሳ (ሕወሓት እንዳይወርድ) የሚያስችል መለስተኛ ለውጥ አድርጎ ድርጅቱን ይታደግ ነበር። እነ ጌታቸው ረዳ ግን በተበላ ዕቁብ ማልቀስ አላቆሙም ‹Timeout› እንደሆነባቸው አልተረዱም።
እኔም የሕወሓት የፖለቲካ ግራ መጋባትን በደበበ ሰይፉ ግጥም አማካይነት ለማሳየት ያደረግሁት ጥረት ሕወሓቶች ደበበ ሰይፉ እንዳደረገው ወይ እምነታቸውን እንዲለውጡ ወይም ጊዜውን እንዲመስሉ፣ ሁለት ወዶ እንደማይኖር፣ በተለይም ከዘመን ጋር መጣላት ለሞት መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡