Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርወደ መሠረታዊ ነገሮች የማተኮር አስፈላጊነትና አስቸኳይነት

ወደ መሠረታዊ ነገሮች የማተኮር አስፈላጊነትና አስቸኳይነት

ቀን:

በሰሎሞን በላይ ፋሪስ (ዶ/ር)

በኮሮና ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች ብዙ ነገር ሲሉ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦች እንዳሉ ሁሉ ብዙዎቹ ሐሳቡን መሠረታዊ ችግሮችን የማይመረምሩና ሩቅ የማይመለከቱ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ስለዚህም እኔም በውይይቱ ለመሳተፍ የሚቀጥሉትን ሐሳቦች እሰጣለሁ፡፡ የዚህ የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን መከሰትና መስፋፋት፣ በዚያም ምክንያት የተፈጠረው ግርግር፣ እንዲሁም ስለምንም ነገር እርግጠኞች ለመሆን አለመቻላችን ብዙ ነገር በቤቴ ተቀምጨ እንዳሰላስል ገፋፍቶኛል፡፡  ‹ግርግር ለቀጣፊ ይመቻል› እንደተባለው በሰዎች ሥቃይ ለመክበር የተዘጋጁ እንዳሉ አሳይቶናል፡፡

ቀጣፊነት ግን በሁሉም አቅጣጫ ነው፣ የሐሳብ ቅጥፈትም እንዴት ከዳር እስከ ዳር እንደተስፋፋና እርግጠኝነት እንዴት እንደጠፋ ተመልክተናል፡፡ በበጎ ወገኑ ደግሞ ‹ችግር የብልኃት ምንጭ ናት› እንዲሉ ብዙ በጎ የፈጠራ ሥራዎች ሲከናወኑ ዓይተናል፡፡ ይኼ ደግሞ ‹. . .መከራ አምላካዊ ጥበቃ ነው፣ ላዩ የእሳትና የበቀል መልክ አለው፣ ውስጡ ግን ብርሃንና ምሕረት ነው› የሚለውን አባባል አስታውሶኛል፡፡ ምናልባትም በዚህ የጥፋት እሳት በሚመስል ነገር ውስጥ ያለውን ብርሃና ምሕረት መፈለግ ጊዜው አሁን ይሆን? ሁሉም ነገር እንዳለፈው ኮሮናም ያልፋል፡፡

- Advertisement -

ትልቁ ሐዘንና ጥፋት የሚሆነው የተሰቃየነውን ያህል ተሰቃይተንና የምናጣውን ያህል አጥተን መማር ያለብንን ሳንማር ከቀረን ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ለሚመጡት ምዕተ ዓመታት እስከ ዛሬ ይዘናቸው የመጣናቸው አስተሳሰቦችና አሠራሮች እንደማይጠቅሙ መረዳትና ልንላቀቃቸው የማስፈለጉን ግንዛቤ የማግኛ ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ኮሮናን እንደ ምክንያት አድርገን ልንማራቸውና ልናተኮርባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነገሮች ምን እንደሆኑ ከዚህ ቀጥሎ እዘረዝራለሁ፡፡

በዚህ ግርግር ሁሉ መሀል የተማርነው ነገር ቢኖር ማኅበረሰባችን በእጅጉ የተከፋፈለ መሆኑን ነው፡፡ በማኅበረሰባችን ውስጥ በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ‹በሁሉም ነገሮች ተስማምተዋል ሊባሉ የሚችሉ ሁለት ሰዎች እንኳን አይገኙም፡፡› ይህ መከፋፈል በኮሮና ላይ ስለምንወስደው ዕርምጃ እንኳ መነጋገርና መደማመጥ እስኪያቅተን ድረስ ሆኗል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ፣ ነጋዴዎችና ሸማቾች፣ ተቋማትና ግለሰቦች እንዴት አይጥና ድመት እንደሚጫወቱ ዓይተናል፡፡ ይህም አለመነጋገርና አለመደማመጥ በዓለማችን ላይ እንዴት መጥፋት የሌለባቸው ሕይወቶች እንዳጠፋ ዓይተናል፡፡

ስለዚህ የሰው ልጆች በመጀመርያ ደረጃ በመሠረታዊነት የአንድ ፈጣሪ ፍጡሮች መሆናችንን ልንቀበልና ልንተገብረው ይገባል፡፡ በየትምህርት ቤቱ ልጆች መጀመርያ የሚማሩት ነገር የሰው ልጆች አንድነትን ሊሆን ይገባል፡፡ የተለያየ መልክና ታሪክ ቢኖረንም፣ የተለያየ ቋንቋ ብንነጋገርም እነዚህ የውበት መገለጫዎች እንጂ እውነተኛ ልዩነቶች እንዳልሆኑ ልንማር ይገባል፡፡ ሰው መኩራት ያለበት መሰሉን የሰው ዘር በመውደዱ እንጂ ለብሔሩ፣ ለሃይማኖቱ ጠበቃ ሆኖ በመቆሙ አይደለም፡፡ መላው ዓለም እንደ አንድ መንደር እየጠበበችና አንዱ ሰው የሚያስበውና የሚሠራው ሌሎችን በጣም እንደሚነካ በተረዳንበት በአሁኑ ጊዜ የሰው ዘር አንድነትን አለመቀበልና የአንዱ ደስታና ሐዘን የሌሎቻችንም እንደሆነ አለመገንዘብ የድንቁርና ጣሪያ ነው፡፡ ስለዚህም ከራሳችን ይልቅ ስለሌሎች ማሰብና ሌሎችን ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ከእነ ብሔራቸው፣ ከእነ ቋንቋቸው፣ ከእነ ማንነታቸው የመቀበል መንፈሳዊ ግዴታ እንዳለብን ልንረዳ ይገባል፡፡ እንደ ቀድሞው ‹የእኔ ብሔር ብቻ የጠራ ደም ያለው ነው›፣ ‹የእኔ ሃይማኖት ብቻ ቀጥታ ከእግዜር የመጣ ነው፣ ወደ ገነት የሚያስገባ ነው›፣ የእኔ፣ የእኔ፣ የእኔ. . . የሚሉት አባባሎች 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን ዓለም አቀፋዊ አንድነትና ልማት አያመጣም፡፡ ለነዚህ መነሻ የሆኑትን የየባህሎቻችንንና የየመጽሐፍ ቅዱሶቻችንን አባባሎች እንደ ገና ተመልሰን መመልከት ያለብን ጊዜ ነው፡፡

ለአንድ ወቅትና ቦታ የተነገሩ አባባሎችን አሁን ከ21ኛው ክፍለ ዘመንና ባሻገር፣ ለመላው ዓለም እንደሚያገለግሉ እውነታዎች አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ስናስብና ስናደርግ የነበራትን ጥንታዊ ነገሮች ሁሉ ለአዲሱ ዘመን መቃኘት የሚያስፈልገን ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች የአንድ ፈጣሪ ፍጡራን እንደሆኑ፣ ሁሉም በሥራውና በፀባዩ መጠን እንጂ በፆታው፣ በተከተለው ሃይማኖት፣ በተወለደበት ብሔር፣ ወዘተ. እንደማይዳኝ ልንገነዘብ የሚገባን ጊዜ ነው፡፡ ከጥንታዊነት ወደ አዲሱ ዘመን ልንወስዳቸውና ልናስቀራቸው የሚገቡ አስተሳሰቦችና አሠራሮችን መመርመሪያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ከእነ ግብስብስ አስተሳሰባችንና አሠራራችን 21ኛው ክፍለ ዘመን ለመግባት አይቻልም፡፡ አንዱ ጥንታዊ ግብስብስ ሐሳብ ቻይናውያን ለኢጣሊያን ኮሮናን ለመዋጋት ዕርዳታ ሲልኩ የጠቀሱትን ሐሳብ አለመቀበል ነው፡- ‹እኛ የአንድ ዓለም ነዋሪዎች፣ የአንድ ባህር ሞገዶች፣ የአንድ አትክልት ሥፍራ አበቦች ነን›

የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥም የሚያሳስበን ይኼንኑ ተያይዘን የተሠራንና አንድነት የኑሯችን መሠረት የመሆኑን ጉዳይ ነው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተከሰቱት ችግሮች ለምን እንደሆኑ አስበን (ዛፍ ከመትከል ባሻገር) መሠረታዊ መፍትሔ ሰጥተናቸው ቢሆን ኖሮ የኮሮና ችግር ስለመከሰቱ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥና ችግሮቹ በተደጋጋሚ ያሳየን ነገር ቢኖር፣ ዓለም አንድ አገር እንደሆነችና ሁላችንም የዚያች ዓለም ዜጎች እንደሆንን ነው፡፡ ሰዎች እርስ በርሳችን ተያይዘን የመሠራታችን እውነታ ብቻ ሳይሆን እኛ ከወንዙ፣ ከተራራው፣ ከዛፉ፣ ከእንስሳቱ ጋር ተያይዘን የተሠራን የመሆኑ እውነታ ግልጽ የወጣበት ሁኔታ ነው፡፡ ‹አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል› እንዲሉ እያሳደድን የምንገላቸው እንስሳት፣ ያለ ርህራሔ የምንቆርጣቸው ዛፎች ሁሉ የሰው ዘር መጥፋትን ያፋጥኑ እንደነበር ተገንዝበናል፡፡ ሳይንቲስቶች አሁን የተፈጥሮ ዓለምን እየጎዳን ባለንበት ሁኔታ ከቀጠልን በጥቂት አሥርተ ዓመታት ልንጠፋ እንደምንችል፣ የቤት ሥራቸውን ሠርተው አሳይተዋል፡፡ የሰው ልጅ አሁን የያዘውን አስተሳሰብ ቀይሮ ለአዲስ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት የሚመጥን አመለካከት እንዲያዳብር ወትውተዋል፡፡ የሚያሳዝነው ፖለቲከኞችና ወግ አጥባቂዎች ከሳይንቲስቶች ፊት ስለቆሙ ዓለም የሚያስፈልጋትን ዕርምጃ ልትወስድ አልቻለችም፡፡ ዛሬም ስግብግብ ነጋዴዎች ለተፈጥሮና ለቀጣይ ልማት ትኩረት ሳይሰጡ የዓለማችንን ሀብት አላግባብ መበዝበዝ ቀጥለዋል፡፡

የድሮ ፖለቲካ (በፓርቲ ተደራጅቶ እንደ መጨቃጨቅ የመሰለ)፣ እኔ ከሌሎች እበልጣለሁ ምረጡኝ ብሎ አደባባይ የመውጣት ትህትና የሌለው የድርቅና ፖለቲካ ሁሉ ሊከለስ የሚገባው እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ከእኔ አውቅልሃለሁ ይልቅ ‹ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ያውቃሉ፣ አቅማቸውን ከገነባን የሚፈልጉትን ያደርጋሉ፣ የልማታቸውና የትምህርታቸው ባለቤት መሆን ይችላሉ› የሚለው አመለካከት እንዲሰርፅ፣ እውነተኛ የልማት አዋቂዎች መወትወት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በሕዝብ ስም ለምነው የግል ኪሳቸው የሚከቱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ ኢፍትሐዊ በሆነ የሀብት ክፍፍል ያላግባብ ኪሳቸውን በገንዘብ የሚያደልቡ ባለሀብቶችና ሙሰኞች አዲሱ የዓለም ሥርዓት እንዳይወለድ እንቅፋት ሆኑ እንጂ፣ ዓለማችን የፍትሕና የእውነት ያለህ ካለች ቆየች፡፡ አሁን እንደምናየው ለማወቃችንና በጤና ለመኖራችን ምክንያት የሆኑ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ሙያችንን እናዳብር፣ በፍትሕ ይከፈለን፣ ክብር ይሰጠን ሲሉ ችላ ያለ ዓለም አሁን ቤት ሲዘጋበት ባልኮኒ ላይ ሆኖ ለጤና ባለሙያዎች፣ ያጨበጭባል፡፡ በአገራችን እንኳ በቅርቡ የሥራና የኑሯችን ሁኔታ ይሻሻል ብለው ድምፃቸውን ያሰሙ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄያቸው ደንቆሮ ጆሮ ላይ ማረፉ የትናንት ታሪክ ነው፡፡ ለችግሮቻችን መሠረታዊ መፍትሔ መስጠት ላይ አትኩረን እንዳልነበር ኮሮና አጋለጠ፡፡ በአጭሩ ዓለማችን አዲስ አስተሳሰብና አዲስ አሠራር እንደሚያስፈልጋት ማመላከት ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ የሚያሳዝነው ግን ስለራሳችንና ስለአካባቢያችን ያለን አስተሳሰብ ገና ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የነበረውን ዓይነት የ‹ረግጠህ ግዛ› ሁኔታ ነው፡፡ እንድንነቃ ምን ዓይነት መቅሰፍት ያስፈልገናል?

ከሰው ዘር አንድነትና የአንድ ፈጣሪ ልጆች ከመሆን ጋር ተያይዞ ልንቀበለው የሚገባን እውነታ የሴቶችና የወንዶች እኩልነት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት በተለያዩ ምክንያቶች ሴቶች ከወንዶች በታች ናቸው የሚለውን አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ኖረናል፡፡ ለነበርንበት የጨለማ ዘመንም የተወሰነ ሥርዓት አስገኝቶለት ይሆናል፡፡  ይሁንና ያለንበትና መጪው ዘመን ይህን ኋላቀርና ጎታች አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋትን ይጠይቃል፡፡ ይልቁንም ሴቶችን አቅማቸውን በመገንባት ወደ አመራር የሚመጡበትን መንገዶች ልንቀይስና፣ በውስጣቸው ያለውን የፍቅርና የርህራሔ ችሎታ ለሰላምና ለአንድነት መጠቀም የምንችልበትን ሥልቶች ልናስብበት የሚገባ ወቅት ነው፡፡ አሁንም ገና እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር ወንዶች በሴቶች ላይ የበላይነት አለን፣ በመንገድ ላይ ሲሄዱ ልንሰድባቸውና ልናንጓጥጣቸው እንችላለን፣ በሕግም በህሊናም ተጠያቂነት የለብንም ብሎ በሚያስብ አገር መከራችን እንዳልተፈጸመ እንረዳለን፡፡ ኮሮናም ቢጠፋ እነዚህን አስተሳሰቦች በግዴታ የሚያጠፉ መቅሰፍቶች ይመጣሉ፡፡  በኢኮኖሚ ጥቅምና በክፍያ፣ በሕግና ማኅበራዊ ፍትሕ ፊት ሴቶች ከወንዶች በታች እስከ ታዩ ድረስ የለቅሷችን ዘመን መራዘሙ አይቀሬ ነው፡፡ ወንዶችም ለደስታችንና ለተሟላ ኑሯችን የሴቶች እኩልነት ጉዳይ የእኛም ጉዳይ እንደሆነ እስካልተቀበልን ድረስ የጥፋታችንን ጊዜ እያረዘምን ነው፡፡ ስለዚህ ሴቶችም ለደረጃቸውና ለክብራቸው የሚመጥነውን ባህሪ ከማሳየት ግዴታቸው ባሻገር፣ ወንዶችም በምንም ዓይነት ሁኔታ ሴቶችን የበታች አድርጎ የማየት ልማዳችንን ልናስወግድ ይገባል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ የሴቶች ጥቃትና ጭቆና ማለት ወደ 55 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በጭቆና ሥር አለ ማለት ነው፡፡ ጭቆና አለ ማለት ደግሞ ጨቋኙም ተጨቋኙም ሰብዓዊነታቸውን አጥተዋል ማለት ነው፡፡ ሰብዓዊነት በጠፋበት ዓለም ደግሞ ደስታና ጥንካሬ ጠፍቶ ሐዘንና ደካማነት ይሰፍናል፡፡ የኢኮኖሚና የትምህርት ፍትሕ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ መጥቷል፡፡ ሁለቱን አንድ ላይ ያያዝኩበት ምክንያት አለኝ፡፡ አሁን ዓለማችን ወይም አገራችን የተደራጀችው ኢኮኖሚን የሕይወት ማዕከል አድርጋ ነው፡፡ ሁሉ ነገር የሚለካው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ዓለም ክብሯን የሰጠችው ለኢኮኖሚ ባለቤቶች እንጂ ለዕውቀት ባለቤቶች አይደለም፡፡ በብዙ መድረኮችና አሠራሮች ከየትና እንዴት እንዳመጡት እንኳ ጥያቄ ሳይኖር፣ ውዳሴ የሚደረደረው ለኢኮኖሚ ባለሀብቶች እንጂ ለዕውቀት ባለሀብቶች አይደለም፡፡  እንደኛ ዓይነት አገርም በሽታው በጣም ሥር የሰደደ መሆኑን የምናውቀው ‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ› በሚለው አባባል ነው፡፡ ይህ አባባል የነገሠው ደግሞ ‹ሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል› የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን በሚል አገር ነው፡፡ በሙያና በጠንካራ ሥራ የሚገኝ ሀብትን ለጊዜው አመሥግነንና ወደጎን ትተን፣ አብዛኛው ሀብት የሚገኘው ለሠራተኞች ተገቢውን ባለመክፈል፣ የመንግሥት ግብርን በማጭበርበርና በተለያዩ የሙስና ዘዴዎች እንደሆነ እናውቃለን፡፡

በዚህም ሁኔታ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከእያንዳንዱ ምድራዊ ሀብት ጀርባ እጅግ የበዛ ፍርኃትና አደጋ እንደተደበቀ ነው፡፡ በተጨማሪም ምድራዊ ሀብት በአንድ ሌሊት ንፋስ እንደ በረሃ አሸዋ ከአንዱ ደጅ አንስቶ ሌላው ደጅ ላይ የሚከምረው በመሆኑ በውስጡ ያለውን እርግጠኝነት አጥፍቶታል፡፡ በዚህም የተነሳ ስታትስቲክስ መፈለግ ቢኖርብኝም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ምድራዊ ሀብትና ማፍራትና ማቆየት የብዙ በሽታዎች ምንጭ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ በተቃራኒው አንድ አገር ዕውቀትን ለሚያፈልቁና ለሚተገብሩ ክብርና ፍትሕ ስትሰጣቸው እርግጠኝነት ይስፋፋል፡፡ እውነተኛ ሀብት ማለት ሰው ከድንቁርና ሲወጣና በዕውቀት ሲኖር ማለት ነው፡፡ መጪው ዘመን ደግሞ የዕውቀት ዘመን ስለሆነ፣ ለሚያውቁና ለሚያሳውቁ ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትክክለኛ ትኩረት አድርገን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ብዙ የሚያውቁና ብዙ የሚከፈላቸው ሰዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነበር የምናገኛቸው፡፡ አሳዛኙ ነገር ዛሬ በአብዛኛው ትንሽ የምናውቀውና ትንሽ የሚከፈለን ነን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለነው፡፡ ሌላው አገር ለቆ ተሰድዷል፣ ወይም የተጋነነ ጥቅም በሚሰጡ ድርጅቶች ተቀጥሯል፡፡ ተጨማሪው አሳዛኝ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ዕውቀት በሚያስፈልቅና በሚተገብር ሥርዓት ውስጥ ስላልሆኑ የጋን መብራት ሆነው ለጋራ ጥቅም ሳይሆን ለግል ኑሯቸው ብቻ ቆመዋል፡፡ ስለዚህ እንደ እርግማን ሁሉም ቦታውን ለቅቆ፣ የእውነትና የፍትሕ ፀሐይ በሐሰትና በጭቆና ደመና ተጋርዶ ሥቃያችን በዝቷል፡፡

ስለዚህ እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥትና እንደ አገር ዘመኑ የሚጠይቀውን ለዕውቀትና ለአዋቂዎች ተገቢውን ቦታ መስጠትን መማር አለብን፡፡ ሀብት ጠቃሚ ቢሆንም በዕውቀትና በሥራ እንዲገኝ ማድረግ፣ ደረጃውም ሁለተኛ እንደሆነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ ዕውቀት ዘላቂና ቋሚ ነው፣ ሀብት ግን መጪና ሂያጅ፣ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ትኩረት ደግሞ ለዘላቂና ቋሚ ነው፡፡ የመጪው ዘመን አቅጣጫ በዕውቀት የተገነባ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ስለዚህ ለመሠረቱ ዕውቀት ተገቢውን ትኩረት ልንሰጥ ግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ጋሪው ከፈረሱ ፊት ይሆንና ጉዟችን እንዳይሆን እንዳይሆን ይሆናል፡፡

አሁን የተረዳነው ነገር ቢኖር ከሚለያዩን ነገሮች አንድ ለሚያደርጉን ነገሮች ትኩረት መስጠት እንዳለብን ነው፡፡ ለምሳሌ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለምሳሌ ለአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር፣ ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ([WHO])፣ ለዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል፣ ለዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትና ለመሳሰሉት ትኩረት ሰጥተን ዘመኑ የሚፈልገውን ዕውቀትና መሣሪያ ሰጥተናቸው ቢሆን ኖሮ አሁን የገባንበት ቀውስ ውስጥ ላንገባ እንችል ነበር፡፡ ብንገባም በመረጋጋት ከቀውሱ ልንወጣ የምንችልባቸውን ዘዴዎች እናገኝ ነበር፡፡ ከጎጥ አደረጃጀቶች ይልቅ ለብሔራዊ አደረጃጀቶች፣ ከብሔራዊ አደረጃጀቶች ይልቅ ለዓለም አቀፋዊ አደረጃጀቶች ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ከእናት ቋንቋችን በተጨማሪ ካሉት መርጠን ወይም አዲስ ፈልስፈን አንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ቢኖረንና ሁላችንም በትምህርት ቤቶቻችን ተምረነው ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በቀላሉ ሊያስተባብሩን ይችሉ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሰነድ በብዙ ሺሕ ቋንቋዎች መተርጎም አይኖርበትም ነበር፡፡ እያንዳንዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለትርጉም የሚወጣው ወጪ ለሌላ ቁም ነገር ይውል ነበር፡፡ ይህንን ቋንቋ ካጠናን በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንጓዝ እንግድነት አይሰማንም ነበር፡፡

ሩሲያ ስንሄድ ሩሲያኛ፣ ፈረንሣይ ስንሄድ ፈረንሣይኛ፣ አሜሪካ ስንሄድ እንግሊዝኛ ማወቅ አይጠበቅብንም ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ዓለም አቀፋዊ የመገበያያ ገንዘብ፣ አንድ ዓለም አቀፋዊ የመለኪያ ሥርዓት፣ አንድ ዓለም አቀፋዊ የቀን አቆጣጠር ይዘረጋና እንደ ባቢሎን ዘመን ከመደነባበር እንወጣ ነበር፡፡ ዓለም እንደ አንድ አገር እየሆነችና እኛም እንደ አንድ አገር ዜጎች (ማታ እራት አዲስ አበባ በልተን ጠዋት ቁርስ ዋሺንግንተንና ቶሮንቶ እየበላን) እየኖርን ዘመኑ የሚጠይቀውን ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብና አሠራር አለመቀበልና አለመተግበር ጥፋታችንን ማፋጠን ነው፡፡ አሁን ከጥፋት የሚያድነን የኖህ መርከብ ይህ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብና አሠራር ነው፡፡ አገሮች በመጠኑም ቢሆን ብሔራዊ ሉዓላዊነት የሚለውን አሠራር ዓለም አቀፋዊ ሉዓላዊነት ማካፈል አለባቸው፡፡ አገሮች ቀስ በቀስ የአንዲት ዕለም ክፍለ አገሮች ሆነው መደራጀት መቻል አለባቸው፡፡ የአገር ክልሎች ደግሞ እንደ ወረዳዎች፡፡ የተወለደው ዓለም አቀፋዊነት እንዲያድግ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

የምክክር ባህል እንዲዳብር አስፈላጊው ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ዓለምና እውነታ ውስብስብ በመሆናቸው አንድ ሰው፣ አንድ ወገን፣ አንድ ቡድን፣ አንድ ፓርቲ፣ አንድ ሃይማኖት ብቻውን እውነታን ተረድቻለሁ፣ እውነት ያለው እኔ ዘንድ ብቻ ነው ለማለት አይችልም፡፡ በቀድሞ ዘመን የሚታወቀው አንድ መንደር በነበረ ጊዜ አንዱ አምባገነን (ወይም አንድ አዋቂ) እኔ በምለው ሂዱ ማለት ሠርቶ ይሆናል፡፡ አሁን ግን በዓለማችን ላይ ብዙ መንደሮች እንዳሉ ባወቅንበት ጊዜ፣ ወሰን አልባ ዕውቀት እንደ ቀትር ፀሐይ በፈነጠቀበት፣ የነገሮችን እውነታ በብዙ መልክ ልናይ በምንችልበት ወቅት ‹እኔ ያሰብኩትና ያልኩት ብቻ ነው ትክክል፣ ሌላው ሁሉ የተሳሳተ ነው› ማለት የሰላምና የአንድነት ጠንቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች በጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጠው የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል ማዳበር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም አሠራር ‹ምክክር› ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡ በዚህ ወይም በዚያ ምክንያት ‹እኔ ብዙ አውቃለሁ፣ ብዙ ልምድ አለኝ፣ ብዙ ጉልበትና ገንዘብ አለኝ ስለዚህ የምለውን ስሙ› የሚለው እምነት ‹እኔ የማውቀው ውስን ነው፣ ልምዴም በተወሰኑ ጉዳዮች ነው፣ ጉልበትና ገንዘብ የትም አያደርሱም› በሚል ትህትና መተካት ይኖርባቸዋል፡፡

ሁሉም የማንነቱን ውስንነት ተረድቶ ከሌሎች በሚመጣ ዕይታ የተሟላ ለመሆን ከተጋን፣ የምክክርን ትክክለኛ አቅጣጫ ይዘናል ማለት ነው፡፡ በዚህ አሠራርና ለጋራ ጥቅም በሚደረግ ምክክር በጓዳ በኩል (በኋላ በር) የሚደረግ ድርድር፣ የራስን አጀንዳ ለመግፋት የሚደረግ ጥረት፣ ከዕውቀትና ከሐሳብ ጥራት ይልቅ በማስፈራራትና በማባበል የሚፈለግ ‹አሸናፊነት› ቦታ የለውም፡፡ በእውነተኛ ምክክር ውስጥ ትህትና፣ የምኞት ንፅህና፣ መላቀቅና ደግነት የመሳሰሉ መንፈሳዊ ባህሪያት አስፈላጊ ናቸው፡፡ ትልቁ ግባችን  የጋራ ጥቅም ነው፡፡ በጋራ ጥቅም ውስጥ ሁላችንም የየድርሻችንን ጥቅማችንን እናገኛለን በሚል እምነት መሞላት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሐሳብ ከተናጋሪው ወይም ከአቅራቢው ከመጣ በኋላ የሐሳቡን ዋጋ ነው መመርመር ያለብን፡፡ ሐሳቡና አቅራቢው አንድ ላይ የተሰፉ ይመስል ሐሳቡን ለማጥፋት ሰውዬውን ማጥፋት ያለብን የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡ ሰውና ሐሳቡ ግንኙነታቸው ሕይወታዊ (ዳይናሚክ) ነው፡፡ ሐሳብ በሰው ውስጥ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል፡፡ ሰውዬው ግን የእኛ ማንነት አካል ሆኖ መኖሩን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ሐሳቡ በተነሳበት ወቅት ለምን እንደተነሳ፣ እንዴት እንደሚታይ፣ የተሻለ ሐሳብ ሊኖር መቻሉን መመርመር እንጂ ያሰበውን ሰው በደፈናው ማንቋሸሽና ማሳነስ ሰብዓዊነት አይደለም፡፡ እንዲያውም ሐሳቦች እንዲበዙ፣ እንዲታሰቡ፣ እንዲታዩ ማድረግ የመጪው ዘመን ፍላጎት ነው፡፡ ራሳችንን በውስን ሐሳቦች ባጠርን ቁጥር ፈጠራንና ዕድገትን እያቀጨጭን ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሐሳብን የማያበረታታ አገር ከድህነት ሌላ የሚተርፈው የለም፡፡ ሐሳብና ሐሳብ ሲፋጩ ዕውቀትና እውነት ይገለጻል፡፡ ሐሳባቸው በሐሳብ የተሸነፈ ሰዎች ለዘለዓለሙ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ሐሳባቸው በጭቆና የተሸነፈ ሰዎች ጠላታችን ሆነው ይኖራሉ፣ ጊዜም ጠብቆ ሐሳባቸው እንደ ገና ብቅ ይልና ይፈታተነናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ፍቱን መድኃኒቱ በማንኛውም ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን የምንመካከርበትን መንፈስ ማዳበር ነው፡፡ በምክክር ሁሉም ያመነበትን ሐሳብ ወስደን መተግበር ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ይሆናል፡፡

በመጨረሻ ይኼ ኮሮና የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ ያደረገው ነገር ቢኖር፣ ስለሳይንስና ሃይማኖት ያሉን የተሰነካከሉ አመለካከቶችን ነው፡፡ በአንድ ወገን በጣም ምክንያታዊ (ራሽናል) ለመሆን ጉጉት ያላቸው ሰዎች ሳይንስን የመጨረሻው የዕውቀት ጣራና ሚዛን አስመስለው ሳይንስን ብቻ ዕመኑ ይሉናል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሳይንስ ዕውቀት እንዳልሆነና የዕውቀት ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ሁሉ አንዳንዶች ሳይንስን ካዱና ሃይማኖትና መንፈሳዊነትን ብቻ ተከተሉ ይላሉ፡፡ ጥቂቶች ሳይንስና ሃይማኖትን ለማስማማት በሚያደርጉት ጥረት ‹ግመልህን እሰር ለአላህ ጥበቃም ስጥ› የሚለውን አባባል ሊያስታውሱን ሞክረዋል፡፡ በአጠቃላይ ነገሩ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሃይማኖተኞችና የሳይንቲስቶች ብሽሽቅ መስሏል፡፡ ምናልባትም ጉዳዩ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በሁለቱም ወገኖች የምክክር ባህልን የማጣት መገለጫ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሊረዱ ይገባቸዋል ብዬ የማምነው ሃይማኖትም ሳይንስም ዕውቀቶች ናቸው፡፡ ዕውቀት ደግሞ ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ የእኛ ጥፋት የትኛው ዕውቀት ለየትኛው እንደሆነ አለመረዳታችን ነው፡፡ ወይም ደግሞ ዕውቀቶች ተፈላላጊና ተደጋጋፊ መሆናቸውን አለመገንዘባችን ነው፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ዕውቀት ሕይወት ያለው (የሚወለድ፣ የሚያድግና የሚሞት) መሆኑን በመዘንጋት፣ የመጨረሻና የማይሻሻል አድርገን ስናስበው ነው፡፡ እንዲህ አድርገው የሚያስቡ ደግሞ ሳይንስ ወይም ሃይማኖት ወይም ሁለቱም አልገቧቸውም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ የሃይማኖት ዕውቀት ማደግና መሻሻል ባይኖርበት ኖሮ፣ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ በአብርሃም በኩል ዕውቀትን ሁሉ አምጥቶ ያበቃ ነበር፡፡ ወይም በሩቅ ምሥራቅ ክሪሽና ስለመንፈስ እንዳስተማረ ባበቃ ነበር፡፡ ይሁንና ከእነርሱ በኋላ ሙሴ፣ ክርስቶስ፣ መሐመድ፣ ቡድሃ መነሳታቸው የሃይማኖትም ዕውቀት እንደሚያድግ መረጃ ነው፡፡ ይህ ክርክር ሊያስነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ይሁንና የየሃይማኖታችንን ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚገባና በትዕግሥት ብንመረምር (ያለማንም አመላካችነትና አስገዳጅነት) ሁሉም ሃይማኖቶች ካለፈው ግልጽነት የቀፀሉ፣ ከእነርሱም ቀጥሎ ሌላ እንደሚመጣ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ከሙሴ በኋላ ማንም አይመጣም ብለው ላሰቡ አይሁዶች በእስልምና ‹አይሁዶች የእግዚአብሔር እጅ ታስሯል ይላሉ. . .ይሁንና ሁለቱም የእግዚአብሔር እጆች እንደተዘረጉ ይኖራሉ› የሚል መልስ ተሰጥቷል፡፡ 

ውቅያኖሶች ወደ ቀለም ቢለወጡና ዛፎች ሁሉ ወደ ብዕር ቢለወጡ የእግዚአብሔር ዕውቀት ተጽፎ ያልቃል ማለት የምናመልከውን አምላክ ማሳነስ ነው፡፡ የእኛን ውስን የመረዳት አቅም የሃይማኖታችን መለኪያ አድርገን ማቅረብ ለኢአማንያን ምክንያታዊነት ማገዶ መሆን ነው፡፡ ጥሩው ነገር የሳይንስን ዕውቀት ማደግና መለወጥን ብዙ አዋቂዎች ይቀበላሉ፡፡ ሳይንስ ሁሉንም ነገር በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚያስቀምጠው ለቀጣዩ ሐሳብ ቦታ ለመስጠት ነው፡፡ ይሁንና የሳይንስ ታሪክ እንደሚያሳየው ብዙ ሳይንቲስቶች አዲስ ሐሳብ ሲያመጡ ተዘናግተን ተሳልቀንባቸዋል፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ ያልኩት ሁላችንም ያለን ዕውቀት የመጨረሻው አለመሆኑና እውነታን የሚገልጸው፣ የእኛ ዕውቀት ብቻ አለመሆኑን የመረዳትን አስፈላጊነት ለማሳየት ነው፡፡ እንደ እኔ አመለካከት የሃይማኖት መዳከም ማለት የሥነ ሥርዓት፣ የግብረ ገብና የንፅህና መዳከም ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ራሱን በተለያዩ ወረርሽኝና ቀውስ ይገልጻል፡፡ የኮሮና መምጣት የሃይማኖት መዳከም መገለጫ አይደለም ብሎ መከራከር ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ወደ ሃይማኖት ተመለሱ፣ ፀልዩ ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና ለምሳሌ ንፅህና መንፈሳዊና አካላዊ ነገር ነው፡፡ አካላዊ ነገሩን የሚነግረን ደግሞ የሳይንስ ዕውቀት ነው፡፡ የንፅህና መጥፋት እንዴት አድርጎ በሽታውን እንዳስፋፋውና ንፅህናን መጠበቅ እንዴት በሽታውን እንደሚያጠፋው የሚነግረን ሳይንስ ብቻ ነው፡፡

የወቅቱ ሳይንስ የነገረንን አለማዳመጥና አለመተግበር ሃይማኖታችንን አለመረዳትና አለመተግበር ነው፡፡ ባይሆን ሁላችንም ቁጭ ብለን የሳይንስና የሃይማኖትን ዕውቀት ተጠቅመን በሽታውን እንዴት ልናጠፋው እንደምንችል የተሻለ መንገድ መፈለጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው ዓለም የሳይንስን ዕውቀት ብቻ ሲጠቀም እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር የሳይንስንም የሃይማኖትንም ዕውቀት በተደጋጋፊነት ተጠቅሞ፣ እንዴት በሽታውን በአጭር ጊዜ እንዳጠፋ ማየት ለዓለም ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ይህን በሽታ በጋራ ምክክር ካለፍን በኋላ ላሉብን ሌሎች ችግሮችም የሳይንስና የሃይማኖትን ዕውቀት በተፈላላጊነትና በተደጋጋፊነት መጠቀም እንማር ይሆናል፡፡ አራት ኪሎ ያሉት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋኩልቲ ሳይንቲስቶች ትህትና ታጥቀውና በመሀላቸው ያለውን መንገድ ተሻግረው፣ ለረጅም ዓመታት አጠገባቸው ያለውን የቲዮሎጂ ኮሌጅ በሕንፃው ሥር ሻይ ከጠጡ በኋላ ሕንፃው ውስት ገብተው ከሃይማኖት ምሁራን ጋር መነጋገር ይጀምሩ ይሆናል፡፡ ከበረቱ ደግሞ በግቢያቸው አንድ ቢሮ ከፍተው ሃይማኖታዊ ትምህርት አለን ከሚሉ ማናቸውም ወገኖች ጋር በሳይንስና በሃይማኖት መንገዶች ትብብር የኢትዮጵያን ትንሳዔ ስለማስገኘት ቢያወጉ ምን ይላቸዋል?!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...