Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተስፋ አለን!

ከፒያሳ ወደ መገናኛ የሚያመራው ታክሲ ውስጥ ተጭነናል፡፡ በበዓል ማግሥት ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ ሰጥተንና የመንግሥትን የጥንቃቄ መመርያ ለማክበር እየተጣጣርን፣ ለማይቀረው የኑሮ ትግል ጎዳና ወጥተናል፡፡ ‹‹ኑሮና ታክሲ ሞልቶ አያውቅም፣ ግቡ. . . ግቡ. . .›› እያለ ወያላው በዞረ ድምር ውስጥ ሆኖ ያገኘውን ሰው ሁሉ ለማስገባት ይጣራል፡፡ ‹‹አብዛኛው ሰው ኑሮው ጎሎበት እንጂ ሞልቶለት አያውቅም. . .›› እያለም ስለሰው ችግር ያወራል፡፡ እሱ የሚዘነጋው ግን በዚህ የፍራቻ ዘመን ታክሲ በግማሽ አቅሙ እንዲጭን መደረጉን ነው፡፡ እሱ በፊት 12 ተሳፋሪዎችን መጫን የነበረበትን 20 ሰዎች መጠቅጠቅ ነው፡፡ በዘመነ ኮሮና ግን ከሰባት በላይ መጫን የለበትም፡፡ ወያላው ደግሞ ነገር ዓለሙን ረስቶ ታክሲውን ለመጠቅጠቅ የቆረጠ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ‹ኧረ አስቸኳይ አዋጁን ተላልፈሃል ብሎ ፖሊስ ይይዝሃል› ሲሉት፣ ‹‹ፖሊስ አጎቴ ነው፣ እንዲያውም ከታክሲዋ ገቢ የተወሰነ ድርሻ አለው፡፡ ስለዚህ ትርፍ ካልጫንኩ ሊከሰኝ ይችላል፤›› ብሎ አረፈው፡፡ አንድ ሙሉ ልብስ የለበሰ ሰው ታክሲዋን አስቁሞ፣ ‹‹ቦታ አለህ?›› ሲለው ወያላው ለሾፌሩ፣ ‹‹እለፍ. . . እለፍ. . .›› እያለ ለሰውዬው ደግሞ በመስኮት በኩል፣ ‹‹ቦታ እንኳን አዲስ አበባ ሰንዳፋም የለም. . .›› እያለ አላገጠ፡፡ ታክሲውን እንደ በፊቱ መጠቅጠቅ ተከልክሎ በብስጭት ከተማው ውስጥ ቦታ ጠፍቷል፣ ሰንዳፋም አይገኝም ሲል ከቀልቡ ያለ አይመስልም፡፡ እንዲያው ለነገሩ በዘመነ ኮሮና ብዙዎች ከቀልባቸው ጋር መሆናቸው ያጠራጥራል!

ሁለት ሴቶች የቡና ዋጋ ከመጠን በላይ መወደዱ እያንገፈገፋቸው ያወራሉ፡፡ አንደኛዋ፣ ‹‹አሁንማ አረንጓዴ አልማዝ መባል ነው የቀረው፤›› አለች፡፡ ቡና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን በመላው ዓለም ቡና ቢጠጣም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አብረው ተሰብስበው ቡና እየጠጡ ችግራቸውን፣ ደስታቸውንና ሐዘናቸውንም የሚወያዩበት ከፍተኛ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው ባህላዊ እሴታችን ነው ያሉም አልጠፉም፡፡ እንደ ዘመኑ ፌስቡክና ትዊተር የማኅበራዊ ግንኙነት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ አንደኛዋ ሴት በቡና ላኪ ነጋዴዎች እየተበሳጨች፣ ‹‹ለአገር ውስጥ ገበያ አንድ ፍሬ እንኳን ሳያስቀሩ ሁሉንም ለቃቅመው መላካቸው ምን የሚሉት ራስ ወዳድነት ነው?›› አለች፡፡ ሌላኛዋ ሴት ደግሞ፣ ‹‹ዶላር ነዋ! ዶላርዬ! ለዶላር ሲባል እንኳንስ ከገበያ ከማሳው ላይ ያለውንም በሙሉ ገዝተውታል፤›› አለች፡፡ አንደኛዋ፣ ‹‹መንግሥት ቡናን እንደ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃ አለመቁጠሩ የሚያሳዝን ነው፡፡ ለእኛ ከሻይ በላይ የሚያስፈልገን ቡና ነው፡፡ ቡና እየጠጣን ስናወጋ የኮሮናን ሥጋት ያረግብልናል፤›› አለች፡፡ የዋጋው መናር ሳያንሰው በገበያ ውስጥ አለመገኘቱ አናዷታል፡፡ በስንቱ ተናዳ ትችለው ይሆን?

አንደኛው ተሳፋሪ የሴቶቹ ወሬ ላይ ጣልቃ ገብቶ አስተያየቱን ሰነዘረ፣ ‹‹እንኳንስ አዲስ አበባ ይቅርና የቡናው አገር ጅማ ላይ እንኳን አንድ ኪሎ ግራም ቡና 75 በብዙ ብር እየተሸጠ ነው፤›› አለ፡፡ አንዲት እናት፣ ‹‹ቱ. . . ቱ. . .ቱ. . .፣ አበስኩ ገበርኩ ታዲያ አዲስ አበባ ውስጥ ስንት ሊሆን ነው?›› አሉ፡፡ አንደኛዋ ሴት፣ ‹‹ባይሆን ውጭ አገር ያሉ ዘመዶቻችን ሲመጡ ቡና ይዘው እንዲመጡ እንማፀናቸዋለን እንጂ፣ እዚህማ ዋጋውም አቅርቦቱም የሚቀመስ አይሆንም፤›› አለች፡፡ ወያላው፣ ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና. . . ቡና. . .›› እያለ ማንጐራጐር ጀመረ፡፡ ሾፌሩ የወያላውን መዝሙር ሰምቶ፣ ‹‹አይ ድምፅ! ይህንን ሻካራ ድምፅህን ለምን አታስሞርደውም?›› አለው፡፡ ወያላውም እውነት መስሎት፣ ‹‹የት?›› አለው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ሥጋ ቤት!›› ብሎ በፌዝ አሳሳቅ ቀለደበት፡፡ የሾፌሩ ድምፁ ከመጎርነኑ የተነሳ ጆሮ ይጠልዛል፡፡ ጆሮ የማይችለው የለ አትሉም ታዲያ!

ወያላው መልሶ፣ ‹‹መጀመርያ እኮ የቡናን ቅጠል ስትቅም የተገኘችው ፍየል ናት፤›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ምን ቡናን ብቻ ጫትንም ሆነ ሻይ ቅጠልን ከፍየል ውጪ ማንም ሊያገኘው አይችልም፤›› አለ፡፡ አንዳንዶች ቡና ካልጠጡ በሥራ ላይ የሚያመጣባቸው ተፅዕኖ አለ፡፡ ሰው ሥራውን በትጋት እንዳይሠራ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ፡፡ ለነገሩ የቡና ዋነኛው ጠቀሜታ ይኸው ነው፡፡ ማነቃቃት፣ ማነቃቃት፣ ማነቃቃት፡፡ ወያላና ሾፌር የፍየልንና የቡናን ታሪካዊ ግንኙነት ሲተርኩ ቆይተው ወደሌላ ርዕስ አመሩ፡፡ ወያላው እያሾፈ፣ ‹‹አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ቡና በኪሎ መሸጣቸውን ትተው እየቆጠሩ መሸጥ ጀምረዋል፤›› አለ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ልጆች ሲላኩ፣ ማነሽ እስቲ አሥራ አምስት ፍሬ ቡና ገዝተሽ ነይ፤›› ይባላሉ እያሉ ተሰምቶ የማይታወቅ ወሬ ጀመረ፡፡ አንዲት ተሳፋሪ የወያላው ንግግር አልመሰጣቸውም፡፡ ‹‹እባክህን እስቲ አታሟርትብን፣ ቡናችን መለማመኛችን ነው፤›› አሉት፡፡ ወያላው ማንን ይሆን የሚለማመኑበት ብሎ ዙሪያ ገባውን ሲያይ፣ እሳቸውም አፍጠው እያዩት መልስ ቢጠብቁ ዝም አለ፡፡ ‹ዝም አይነቅዝም ነው መሰል› ነገሩ!

ዝምታውን በመስበር፣ ‹‹ኋላ አፍ እከፍታለሁ ብለህ ለአባብዬ ነግሬው ዘጠኝ መርፌ ነው ግንባርህ ላይ የሚተክልልህ፤›› አሉ እየተውረገረጉ፡፡ ሌሎች ደግሞ፣ ‹አባብዬዎች አሁንም አሉ እንዴ?› በሚል ስሜት ሲያጉተመትሙ፣ ‹‹ማዘር እንደሚመለከቱት ግንባሬ በጣም ጠባብ ናት፣ እንኳን ለዘጠኝ መርፌ ቀርቶ ለሁለት መርፌም አትበቃም፤›› እያለ ማዘርን ወያላው አበሳጫቸው፡፡ ማዘር ቆጣ እያሉ፣ ‹‹ልብ አድርግ ዘጠኝ መርፌ.. . . ዘጠኝ መርፌ. . . ዘጠኝ መርፌ. . . ብያለሁ፤›› አሉ፡፡ ወያላው እንኳን ሊደነግጥ፣ ‹‹ለመሆኑ አባብዬ ማናቸው? ባህላዊ መርፌ ወጊ ናቸው? ታዲያ ከመቼ ጀምሮ ነው መርፌ ግንባር ላይ የሚወጋው? ትንሽ ብርድ ቢጤ እያስቸገረኝ ስለሆነ ጭኔ ላይ ይሁንልኝ፤›› አላቸው፡፡ ወያላው ነገሩ ቢገባውም እያላገጠ ነው፡፡ አንዳንዶች ወያላው ዝም እንዲል ለመኑት፡፡ ወያላው ግን ቢያንስ የመናገር መብቴን ልጠቀም ያለ ይመስላል፡፡ በመጨረሻም፣ ‹‹በዚህ ዕድሜዎ ያውም በዘመነ ኮሮና መርፌ፣ አባብዬ ከሚሉ በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ፕሮግራም ቢፀልዩ አይሻልዎትም?›› አላቸው፡፡ በንዴት ተንተከተኩ፣ ‹‹ታየዋለህ በቅርብ ቀን፣ በቅርብ ቀን ጠብቅ፤›› አሉ፡፡ ወያላው፣ ‹‹ምን? የሚመረቅ ፊልም ነው?›› እያለ አፍ አፋቸውን ብሎ ዝም አሰኛቸው፡፡ ጉደኛው ወያላ ጠብቅ እየተባለ ማስፈራሪያ ሲሰጠው፣ አዲስ የሚመረቅ ፊልም ይጠብቃል፡፡ ለነገሩ ነቢያት ነን ብለው ስንቶች በስንቶች ሕይወት እየቀለዱ አይደል!

አንዲት ሴት ታክሲውን ስታስቆም ወያላው፣ ‹‹ላግባት?›› አለ፡፡ ተሳስቶ ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ ‹‹ላግባት?›› ማለቱ ላስገባት በማለት ፋንታ ሆን ብሎ እንደሆነ ተገለጠልን፡፡ የወያላው ንግግር የገረማቸው አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው፣ ‹‹ወይ ልጄ ማግባት መቼ እንደዚህ ቀላል ሆነ? ትዳር ማለት እኮ. . .›› ብለው የጀመሩትን ሳይጨርሱ በሐሳብ ጭልጥ ብለው ሄዱ፡፡ ወያላው እዚህ ላይ ሌላ ነገር አመጣ፣ ‹‹ይቅርታ አባት ዘንድሮ ለማግባት የሚያስፈልገው ገንዘብ ሳይሆን ምላስ ብቻ በቂ ነው፤›› ሲል ሁላችንም ፀጥ አልን፡፡ ይኼ ወያላ በቃ መልስ አያጣም ማለት ነው? ወያላው ለምንም ነገር ግድ አይመስልም፡፡ ሾፌሩ በዕድሜ ላቅ ያለ ቢሆንም እሱም ግዴለሽ ነገር ነው፡፡ ሴትየዋ በወያላው አነጋገር ስለተበሳጩ አሁንም አሁንም ‹‹የለህማ. . .›› እያሉ ብቻቸውን ያወራሉ፡፡ ከፊታቸው የተቀመጠች ወጣት፣ ‹‹ማዘር ማንን ነው የለህማ የሚሉት?›› ስትላቸው፣ ‹‹ምን አገባሽ?›› ብለው መለሱላት፡፡ ወያላው በሁለቱ ንግግር ለመዝናናት እየፈለገ፣ ‹‹ፋሲካን ተደብራችሁ ነው መሰል ያሳለፋችሁት. . .›› እያለ ሲናገር፣ ‹‹እንኳን እኔ አንተም አልተባልክ ጫታም. . .›› ስትለው ወጣቷ ሴትየዋ ደግሞ፣ ‹‹ዕድሜ ለጀበናዬ ቅብርር ብዬ ነው ያሳለፍኩት፣ አንተ አለህ እንጂ ገበጣ ፊትህን አመድ ያስመሰልከው. . .›› ሲሉት የታፈኑ ሳቆች ተሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜማ እንዴት ተደርጎ ይሳቃል!

ይኼን ጊዜ ሾፌሩ ወያላውን መተንኮስ ጀመረ፡፡ ‹‹አየህ ይህንን ታንክ የሄደበት የመሰለ ፊትህን ይዘህ አፍ መካፈት የሚያመጣውን? በመጀመሪያ ደረጃ እሳቸው እንዳሉህ የፊትህን ገጣባ ቀንስ፡፡ ሁለተኛ ከጫት ቀጥሎ በአደገኛ ሁኔታ የተፀናወተህን ነገር ፍለጋ አስተካክል፡፡ ሦስተኛ ብዙ ከማውራት ብዙ ለማዳመጥ ረስህን አዘጋጅ…›› በማለት ጨዋ ቢጤ ምክር ቢጤ ጣል አደረገለት፡፡ ወያላው የሚበገር አልሆነም፡፡ ‹‹ፈሪ ስለሆንክ እኔን ለመተቸትም ሆነ ለመምከር የሞራል ብቃት የለህም፡፡ ዝም ብለህ በአዘዝኩህ አቅጣጫ ንዳ፤›› በማለት ምላሽ ሰጠ፡፡ የታከተው ሾፌር የታክሲውን ሬዲዮ ሲከፍት በታክሲ ቀጣና ሥምሪትና ታሪፍ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ አንደኛው አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹የቀጣና ሥምሪት አስፈላጊ ቢሆንም በርካታ ታክሲዎች ሊጨመሩ ይገባል፡፡ ዝም ብሎ ታሪፍ መጨመር ፌር አይደለም. . .›› እያለ ይናገራል፡፡ ወያላው እያሽሟጠጠ፣ ‹‹እንኳን አዳዲስ ታክሲዎች ሊጨመሩ አሁን ያሉትም በዬት በኩል በወጣን እያሉ ነው፡፡ የግብር፣ የመለዋወጫ፣ የነዳጅ፣ የቅባት፣ የጋራዥ ወጪ እንዲህ በናረበት ጊዜ ተጨማሪ ታክሲ ከየት ሊገኝ ነው?›› አለ፡፡ ሁሉም ብሶቱን ካወራ እኮ ለመስማትም ይከብዳል!

የታሪፍ ጭማሪ ያሳሰባቸው የሚመስሉ አዛውንት፣ ‹‹አሁን ልክ ተናገርክ ልጄ! ገበያው እንደ እሳት እየተጋረፈ ነው፡፡ የዘይትና የሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ምክንያት አልቀመስ ብሏል፡፡ አንድ ኪሎ ቡና ያውም ብጣሪ የሞላበት 125 ብር ይሸጣል፡፡ የዋጋ ቅናሽ ተደረገባቸው የተባሉ ምርቶችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስኳር ብርቅ ሆኖብናል፡፡ የማብሰያ ከሰል ዋጋው ንሯል፡፡ በጡረታ ገቢ ኑሮ ከብዶ ታክሲም ታሪፍ ጨምሮ ጠበቀን፡፡ ለጤናችን ሲባል ቢሆንም ታሪፉ ግን ሊታሰብበት ይገባል. . .›› እያሉ እርር ትክን አሉ፡፡ ‹‹ፋዘር  ልክ ነዎት ሆቴል ቢሄዱ እዚህ ግባ የማይባል ሽሮ 60 ብር ይጠየቅበታል፡፡ ቃሪያ የሌለው በየዓይነቱ ዋጋው በእጥፍ አድጓል፡፡ የበርጫ ዋጋ በጣም ሲጨምር መጠኑ አንሶ. . .›› ሲላቸው፣ ‹‹በል ዝም በል ሰማሁህ፡፡ ካልጠፋ ነገር እሱም ተወደደ ብለህ ታማርራለህ?›› አሉት፡፡ ‹‹አይ ፋዘር አንዳንዴ እኮ እሱን ቅመን ነው ያለ እራት የምናድረው፤›› ሲላቸው፣ ‹‹እውነትህን ነው ስትመረቅን የጠገብክ ስለሚመስልህ ለአንተ ሁሉም ነገር ቀላል ነው፤›› ብለውት ወራጅ አሉ፡፡ እየወረዱም፣ ‹‹ልጄ›› ሲሉት ‹‹አቤት አባቴ?›› አላቸው፡፡ ‹‹ግን ምርቃና ከዚህ ሌላ እንዴት ያደርጋል?›› ሲሉት፣ ‹‹አንዳንዴ አገር የሚያስተዳድሩ እስኪመስልዎት ድረስ ልብ ይደፍናል፤›› አላቸው፡፡ ሰውዬው እያማተቡ ተለዩን፡፡ ምን ይበሉ ታዲያ!

ሾፌሩ በመገረም ዞሮ እያየው፣ ‹‹ብለህ ብለህ ጫት ልብ ይደፍናል ማለት ጀመርክ እንዴ? ባለውለታህን?›› እያለ የመገረም ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ወያላው ሾፌሩን አፍጥጦ እያየው፣ ‹‹እንዳንተ ዓይነቱን ፈሪ እንደ ክኒን ያሟሟዋል፣ እንደ ሲባጎ ያከረዋል እንጂ ታውቀው የለ እንዴት ፏ እንደሚያደርግ?›› ሲለው ሁላችንም ሳቅን፡፡ ሾፌሩ እየተገረመ፣ ‹‹ጋዜጣ ወይም መጽሐፍ አታነብም፣ ለመሆኑ ይህንን ሁሉ ነገር ከየት ነው የምታመጣው?›› አለው፡፡ ‹‹ማታ፣ ማታ አንተ አረቄ ቤት ስትጣድ እኔ ቀን ገዝቼ ያስቀመጥኩትን ጋዜጣ አነባለሁ፡፡ አንተ በዞረ ምድር እየተደናበርክ ስትመጣ እኔ ራሴን በዕውቀት ቻርጅ አድርጌ ብቅ እላለሁ፡፡ ስለዚህ ልዩነታችን የተፈጠረው በዚህ ምክንያት ነው፤›› በማለት የዕውቀቱን መገለጫ ምንጭ ጠቀሰለት፡፡ ሾፌሩ ሰው ፊት ጠጪነቱ በመጋለጡ የተናደደ ይመስላል፡፡ ‹‹ለማያውቅሽ ታጠኚ የተባለው ለአንተ መሰለኝ. . .›› እያለ በብሽቀት እየተናገረ መገናኛ ስንደርስ ‹‹መጨረሻ›› ተብለን ወረድን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ምንም ሳይናገር የነበረ ጎልማሳ፣ ‹‹በዓሉን እንደ ምንም ብለን በሰላም አሳልፈናል፣ ኮሮና ቫይረስም እንዲሁ እንዲያልፍልን ተስፋ እናደርጋለን. . .›› እያለ መንገዱን ሲቀጥል እኛም በተስፋ ተሞልተን ወደ ጉዳያችን ቀጠልን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት