Wednesday, March 22, 2023

የኮሮና ወረርሽኝ ትንበያዎች ሥጋትና የጎንየሽ ችግሮች 

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱ ትንበያ ወደ እውነት ከተለወጠ በአፍሪካ በሺዎች ቤት  ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ቁጥር፣ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ አሥር ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ተሰምቷል፡፡ ምንም እንኳ የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ቁጥሩ ጊዜያዊና ሊቀየር የሚችል ትንበያ መሆኑን ቢገልጽምና በኢቦላ ወረርሽኝ ጊዜ የተተነበዩት ሁሉ አለመሳካታቸውን ቢያስታውስም፣ የከፋው ሊመጣ ይችላል በማለት በሰዎች ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳ ግን አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል እንግሊዝ የሚገኘው የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለአፍሪካ በጣም በተሻለ የቢሆን ግምት እስከ 300 ሺሕ ሰዎች በቫይረሱ እንሚሞቱ ሲያስታውቅ፣ ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ደግሞ ቫይረሱን ለመከላከል ምንም ጥረት ባይደረግ ባለው የከፋ ግምታዊ ቢሆን ደግሞ እስከ 3.3 ሚሊዮን ሰዎች ሲሞቱ፣ 1.2 ቢሊዮን ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡  

በአፍሪካ 24 ሺሕ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ ሁለት ሺሕ የሚሆኑት መሞታቸው ሪፖርት ሲደረግ፣ ስድስት ሺሕ ያህሉ ደግሞ አገግመዋል ተብሏል፡፡ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮና ደቡብ አፍሪካ በመጠቃትም ሆነ በሞት ትልቁን ድርሻ ሲይዙ፣ በሌሎች አገሮች በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የአፍሪካ ቁጥር ከአውሮፓና ከአሜሪካ አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ቢመስልም፣ በማናቸውም ጊዜ በጣም ሊያድግና የብዙዎችን ደሃ አገሮች የጤና ተቋማት አቅም ሊያሽመደምድ እንደሚችል ፍራቻ አለ፡፡

የብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የኑሮ ሁኔታ በጣም የተጎሳቆለ በመሆኑና በተለይ በከተማ የሚኖሩ ሰዎች በተፋፈጉ ጭርንቁስ መኖሪያዎች ስለሚኖሩ፣ የኑሮ ዘይቤውም ከፍተኛ ጥግግት ስላለበት፣ መደበኛ ባልሆኑ የሥራ ዘርፎች የዕለት ጉርስ ለማግኘት የሚማስኑ በርካታ ሚሊዮኖች ስለሆኑ፣ እንዲሁም በገበያዎችና በእምነት ሥፍራዎች ስለሚተፋፈጉ ሁኔታዎች ካልተቀየሩ የከፋ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ነው የቢሆን ትንበያዎች በተለያዩ አካላት እየወጡ ያሉት፡፡

ከተወሰኑ አገሮች በስተቀር በብዙዎቹ ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ ሰዎችን ቤት እንዲቀመጡ ማድረግ በማይቻልባት አፍሪካ የጥንቃቄ መመርያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሳያሰልሱ ማስተማር አስፈላጊነት ላይ ብዙዎች ቢስማሙም፣ እየተስተዋሉ ካሉ ግድ የለሽነቶችም ሆነ ከግንዛቤ ጉድለቶች አኳያ መንግሥታት ጠንከር ያሉ የክልከላ ዕርምጃዎች ለመውሰድ መዘጋጀት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ከመከላከልና የጤና ተቋማትን ከማጠናከር በተጨማሪ፣ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ የባህሪ ለውጥ እንዲያደርጉና ወረርሽኙ እስኪገታ ድረስ እንቅስቃሴያቸውን በተቻለ መጠን እንዲገድቡ አስገዳጅ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ሲሉም ማሳሰቢያቸውን ያጠናክራሉ፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በትንሳዔ በዓል ዋዜማ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹…ከገጠመን የበለጠ ፈተና እንዳይገጥመን እንደ መንግሥትና ሕዝብ እስከ ምን ድረስ ራሳችንን ማዘጋጀት እንዳለብን፣ ሁላችንም በአንድ ልብ መክረንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባናል…›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹…ፈተናውን የምናልፈው ግን በዝግጅታችን መጠንና ለተግባራዊነቱ ባለን ፅናት ልክ ነው…›› ቢሉም፣ በበዓሉ ዋዜማ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በገበያዎችና በተለያዩ ሥፍራዎች የተስተዋሉት መጨናነቆችና መተፋፈጎች፣ ችግሩን በሥጋት ለሚመለከቱ ወገኖች መደናገጥን የፈጠሩ ነበሩ፡፡ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የተሰሙ የሥጋት አስተያየቶች በፎቶግራፎች ጭምር የታጀቡ ነበሩ፡፡

የስቅለት መታሰቢያ ዕለት በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ለምዕመናን ማሳሰቢያ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት በቤተ ክርስቲያኗና በመንግሥት የወጡት መመርያዎች እንዲከበሩ አሳስበው ነበር፡፡ ‹‹ቤታችን ሆነንም ስንፀልይ አምላካችን ይሰማናል፣ ይህ ችግር እስኪያልፍ ድረስ ታግሰን መመርያዎችን እናክብር፤›› ቢሉም፣ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ምዕመናን ከፀጥታ አስከባሪዎች አቅም በላይ ሲሆኑ ተስተውለዋል፡፡ በቀበና ምሥራቅ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቄስ አበባው ምንዳ፣ ‹‹የስቅለት ዕለት ቆራቢዎችን ካስተናገድን በኋላ፣ ድንገት ሳናስበው ከውጭ ተንጋግተው በገቡ ምዕመናን ስንጨናነቅ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ሰው በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሲነገረው ካልሰማና የመንግሥት መመርያ ካልተከበረ፣ ከፊታችን ከባድ ፈተና እንዳለ መጠራጠር አይገባም፤›› ሲሉ ነበር ሥጋታቸውን በጭንቀት የገለጹት፡፡ መንግሥት ሕግ ማስከበሩ ላይ መበርታት አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡

ከ30 ዓመታት በላይ ስድስት ኪሎ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ መክብብ ጥሩነህ፣ አትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ በጊዜያዊነት መዛወሩ በመንግሥት መወሰኑን እንደሚደግፉ ገልጸው፣ ገበያው በአንድ ጊዜ በሕዝብ እንዲጨናነቅ መደረግ አልነበረበትም ብለዋል፡፡ ‹‹ወቅቱ ከባድ እንደ መሆኑ መጠን ደንብ አስከባሪዎችን በማሰማራት ገበያተኞች ርቀታቸውን ጠብቀው በፍጥነት የሚፈልጉት ሸምተው እንዲወጡ መደረግ ነበረበት፤›› ብለው፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ክፍላተ ከተሞች ሥራ ፈተው ያሉትን ደንብ አስከባሪዎች ቢያሰማሩ ኖሮ፣ ለማየት የሚያስደነግጥ የሰው መጨናነቅ በጃንሜዳ አናይም ነበር፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአቶ መክብብን ሐሳብ የሚጋራው ወጣት በጎ ፈቃደኛ መስፍን የሻነው በበኩሉ በጃንሜዳ መግቢያ በር ላይ ለገበያተኞች በገመድ መግቢያና መውጫ ተዘጋጅቶ መስተንግዶ ቢደረግም፣ ለግብይት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በጣም ብዙ በመሆኑ ለምን የአካባቢው ወረዳዎች ዕገዛ እንደማያደርጉ ግራ የሚያጋባ ነው ብሏል፡፡ ‹‹ከጃንሜዳ ፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ አባላት በተጨማሪ፣ በአካባቢው ያሉት ወረዳዎች ደንብ አስከባሪዎችን ቢያሰማሩ ኖሮ ጭንቅንቁን በማስወገድ ያለ ሥጋት ሥራችንን እናከናውን ነበር፤›› ሲል አስረድቷል፡፡ የከተማው አስተዳደር ይህንን ጉዳይ ያስብበት ሲልም አክሏል፡፡

ተቋርጦ የነበረው የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በዓሉ ዋዜማ እንዲቀጥል ከተወሰነ በኋላ፣ ለበዓል ወደ ተለያዩ ክልሎች ለመሄድ መናኸሪያዎችን ያጨናነቁ መንገደኞች ብዛት አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለጉዞ የተሰናዱት አውቶቡሶች ከሚያስተናግዱት በላይ በመናኸሪያዎች የነበረው መተፋፈግ ያስደነገጣቸው ሰዎች፣ መንግሥት በዚህ አስፈሪ ጊዜ እዚህ ውሳኔ ላይ ለምን ደረሰ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ አዲስ ከተማ የሚገኘው መናኸሪያ ፊት ለፊት ከሚገኘው መደብሯ ውስጥ ሆና ለማየት የሚያስፈራውን የሰው ማዕበል በመገረም ስትመለከት የነበረችው ሰላም ሙሉጌታ፣ ‹‹እኔ ማለት የምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በአንድ እጁ እየገነባ በሌላው የሚያፈርስ እየመሰለኝ ስለሆነ፣ ፈጣሪ አምላክ ምሕረቱን ያውርድልን እንጂ አያያዛችን ለኮሮና እጅ የሚያሰጥ ነው፤›› ስትል ነው ሥጋቷን የተናገረችው፡፡ ብዙዎቹ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱና በአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ሥጋቷን ገልጻለች፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ያወጣቸውን መመርያዎች እንዲያከብር ሲያሳስብ፣ አንዳንድ ዕርምጃዎቹ ግን መቀልበስ ለሚያዳግቱ አደጋዎች እንዳያጋልጡ የሚያስቡ አሉ፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመፍቀድ በፊት በቂ ተሸከርካሪዎች ለሥምሪት ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት መተፋፈግ እንዳይፈጠር መሥራትና በቂ የፀጥታ አስከባሪዎችን መመደብ ተገቢነት ላይ በብዙዎች በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቶች ተሰምተዋል፡፡

የግል የቤት አውቶሞቢሎች በፈረቃ እንዲነዱ የወጣው ድንጋጌ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ ለምን እዚህ ውሳኔ ላይ ሊደረስ እንደተቻለ የሚመለከተው አካል ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡ በማብራሪያው መሠረት ሚዛን የሚደፋ ውሳኔ ከሆነ ለመቀበል፣ ካልሆነ ደግሞ ውሳኔው እንዲታጠፍ የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ድንጋጌውን ሲያወጣ ምክንያቱን ባለመናገሩ በሥራዬ ላይ ችግር ተፈጥሮብኛል፡፡ ሰኞ ዕለት ጎረቤቴ ምጥ አጣድፏት ሆስፒታል ማድረስ ሲኖርብኝ የእኔ ሰሌዳ ቁጥር ጎደሎ በመሆኑ፣ ለኮንትራት ታክሲ ወጪ ተዳርጋለች፡፡ ምክንያታዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች እየተላለፉ በሌሎች ችግሮቻችን ላይ ተጨማሪ ችግሮች ባይደረቡብን…›› ሲሉ በምሬት የተናገሩት ልደታ ኮንዶሚኒየም ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዓለሙ ናቸው፡፡ መመርያዎች ሲወጡ ዙሪያ ገባ ችግሮችን ቢያገናዝቡ መልካም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደሳቸው ሁሉ ሌሎችም የቤት አውቶሞቢል ባለቤቶች መንግሥት የውሳኔውን ምክንያት ያሳውቀን በማለት ጠይቀዋል፡፡ አቶ መሐመድ ፋሪስ የተባሉ የተባሉ ገርጂ አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ደግሞ፣ ‹‹ይኼ መመርያ የወጣው በአጉል አማካሪዎች ነው እንጂ፣ በትክክለኛ አማካሪዎች ቢሆን ኖሮ ምክንያቱ ይነገረን ነበር፡፡ መንግሥት በፍጥነት ጉዳዩን እንዲመረምር ድምፄን ማሰማት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት የነዳጅ እጥረት ገጥሞት ቢሆን ኖሮ በግልጽ ማየት ይቻል ነበር ያሉት አቶ መሐመድ፣ የተወሰደው ዕርምጃ አሳማኝ ካለመሆኑም በላይ የመንግሥትን ኮሮና ቫይረስ የመከላከል ጥረት ጥላሸት የሚቀባ ነው ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ለሙስና እንደሚያጋልጥም ገልጸዋል፡፡

ምርጫ 2012 በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ብዙዎቹ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልክ እንደ ምርጫ ቅስቀሳ ማኅበረሰቡን የጥንቃቄ መመርያዎችን ሲያስገነዝቡ አለመታየታቸው ብዙ እየተባለበት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በዚህ ጊዜ ወጣ ብለው በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የቫይረሱ ሥርጭት እንዲገታ ከማድረግ ይልቅ፣ አልቀረብንም ለማለት ያህል አንድ ወይም ሁለት መግለጫ አውጥተው ጥፍት ማለታቸው አነጋጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አባላትና ደጋፊዎችን በበጎ ፈቃደኝነት በማሰማራት ማኅበረሰቡ በተጨባጭ የማያየው ተግባር ሳያከናውኑ፣ ለመጪው ምርጫ እንዴት ዝግጅት ያደርጋሉ የሚለውም እንዲሁ፡፡ በሌላ በኩል ምርጫው በችግሩ ምክንያት መተላለፉ አልዋጥ ብሎአቸው ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ለወቀሳና ለትችት የሚጠቀሙትም ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ይልቁንም በእነሱ በኩል የሚፈለግባቸውን ወቅታዊ ኃላፊነት እየተወጡ በመንግሥት በኩል የሚታዩ ክፍተቶች እንዲደፈኑ ዕገዛ ማድረግ ሲገባቸው፣ የሥልጣን ጥማት ውስጥ ሆነው የሚቃዡ ነው የሚመስሉት የሚሉ ድምፆችም ይሰማሉ፡፡

ሰሞኑን ክራይሲስ ግሩፕ የተባለው ተቋም መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ያወጣውን የቢሆን ትንተና መነሻ በማድረግ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው፡፡ ክራይሲስ ግሩፕ መጪው ምርጫ በመተላለፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት በሕግ የተቀመጠለት የሥልጣን ጊዜው ሲያበቃ፣ ከዚያ በኋላ በሥልጣን ለመቀጠል ምን ዓይነት ዝግጅት ይኖረዋል የሚለው አሳሳቢ ይሆናል ይላል፡፡ ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቢያራዝመው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሥልጣን እንደሚራዘም መከራከሪያ እንደሚቀርብ፣ ነገር ግን የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ሊያነሱ ስለሚችሉና ይህም ግጭት ለመቀስቀስ ምክንያት እንደሚሆን ይዘረዝራል፡፡ ሐሳቡ መነሳቱ መልካም መሆኑን የሚያወሱ ወገኖች ግን፣ መጀመርያ መቅደም ያለበት የሰው ሕይወት ስለሆነ ትኩረቱ እሱ ላይ ይሁን ይላሉ፡፡

እዚህ ላይ መነሳት አለበት ተብሎ በዚህ ርዕስ መነሻ እንደ ክርክር የሚቀርበው መንግሥትም ሆነ ብልፅግና ፓርቲ፣ እንዲሁም ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሕግ የበላይነት መከበር ትኩረት እንዲሰጡ ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች አጥቅቶና 180 ሺሕ የሚሆኑትን ገድሎ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት በፈጠረበት በዚህ ጊዜ፣ ሁሉም ነገር በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን ከመቼውም ጊዜ በላይ ስምምነት መፍጠር እንዳለባቸው ነው ማሳሰቢያ እየተሰጠ ያለው፡፡

ከዚያ ውጪ የራስን የቤት ሥራ ሳያከናውኑ በውጭ ኃይሎች በሚፈበረኩ የሴራ ትንተናዎች መጠለፍ፣ ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ከተጋረጠው ወረርሽኝ በተጨማሪ ለአላስፈላጊ ትንቅንቅ በመዳረግ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ያስገባል ሲሉም ያስስባሉ፡፡ ወደፊት ሕይወት በነበረበት መንገድ እንኳ ባይሆን ወቅቱ በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት የሚቀጥል ቢሆንም፣ መጀመርያ የኮሮና ቫይረስ ቀውስ እንዳይፈጥር በርትቶ መከላከል እንደሚገባና ለዚህም ሕጋዊ አካሄዶች ጠቃሚ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ኮሮና ቫይረስ ዓለምን እያስጨነቀ እያለና መጪው ጊዜ ለአፍሪካ ሊከብድ ይችላል ተብሎ ሲተነበይ፣ ያሉትን ችግሮች በውል አውቆ ለመፍትሔ በአንድነት መሠለፍ ብቸኛው አማራጭ ነው የሚለው፣ በኢትዮጵያም በተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም ሆነ በመላው ዓለም በአገር መሪዎች፣ በጤና ባለሙያዎች፣ በእምነት መሪዎችና በሚመለከታቸው አካላት የሚተላለፍ ዋነኛው መልዕክት ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፍም ሆነ በአኅጉር ደረጃ ትብብርን በማጠናከርና በመረዳዳት የኮሮና ተፅዕኖን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ፣ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ብቻ ያለመ ተግባር ላይ መገኘትና መፈጸም ያለባቸውን የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን ወደ ጎን ማለት፣ እንዲሁም ክልከላ የተደረገባቸው ድርጊቶችን ማከናወን በሥጋት ትንበያዎች አቅጣጫ በመንደርደር የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚለው ሐሳብ ሚዛን እንደሚደፋ ከበርካቶች አስተያየት መገንዘብ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -