የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በመከሰቱ ምክንያት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ጸሎታቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲያደርሱ በተላለፈው ውሳኔ ምክንያት፣ ከ200 በላይ ገዳማትንና አድባራትን ለከፋ ችግር እንደሚያደርጋቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ዓርብ ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የወረርሽኙን ተስፋፊነት ለመግታት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ቤተ ክህነት በታላቅ መንፈሳዊ አምልኮ የምታከብረውን ዓብይ ፆምና ዓበይት በዓላት፣ ምዕመናን በቤታቸው ተወስነው ጸሎታቸውን እንዲያደርሱ መወሰኑንና መንፈሳዊ አገልግሎት በውስን አገልጋዮች ብቻ እንዲመራ ማድረጓንም፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ቦርድ ሰብሳቢ መልአከ ሕይወት ቆመስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያደርጉት የነበረውን የዕለት ተዕለት ግንኙነት እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡ ምዕመናኑ ደግሞ ከእምነት ቦታቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ሲቋረጥባቸው ከሚፈጠርባቸው መንፈሳዊ ሐዘንና ቁጭት ስሜት በተጨማሪ፣ በእነሱ አስተዋጽኦ የሚገለገሉ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ ከ200 በላይ ገዳማትንና አድባራትን የሚያገለግሉ ካህናትና ቤተሰቦቻቸው ለከፋ አደጋ የሚዳርጋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ገንዘብና ደረቅ ምግቦችን የመሰብሰብ ተግባር የሚያከናውን ኮሚቴ መዋቀሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ደረቅ ምግቦችን፣ ገንዘብና የንፅህና ቁሳቁሶችን በጊዜያዊነት የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለምና ቅዱስ ዮሐንስ ካቴድራል፣ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣ ደብረ ጽጌ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንና ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የገንዘብ ዕርዳታ የሚያደርጉ ምዕመናን ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል በተከፈተው ዝግ የሒሳብ ቁጥር 1000328711404 ገቢ እንዲያደርጉም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዝ ሦስት ሚሊዮን ብር መስጠቱን፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆችም ለሕሙማን ማቆያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡