Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ ኢትዮጵያ የገቡ መንገደኞች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በምርመራ ሳይረጋገጥ ከማቆያ ማዕከላት እንዳይወጡ...

ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መንገደኞች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በምርመራ ሳይረጋገጥ ከማቆያ ማዕከላት እንዳይወጡ ተወሰነ

ቀን:

በራሳቸው ወጪ በማቆያ ሆቴሎች ለሚገኙ ከ14 ቀናት በኋላ ወጪ መንግሥት ይሸፍናል

 ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸው በላብራቶሪ ምርመራ ሳይረጋገጥ፣ ከማቆያ ሆቴሎችና ከሌሎች ማዕከላት እንዳይወጡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወሰነ።

ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ወይም የሚመለሱ መንገደኞች ለማቆያነት በተመረጡ ሆቴሎች በራሳቸው ወጪ፣ እንዲሁም መንግሥት ባዘጋጃቸው የማቆያ ማዕከላት ለ14 ቀናት ተገልለው እንዲቆዩ በተወሰነው መሠረት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገሮች ዜጎች ይገኛሉ።

ቁጥራቸው በርከት ያለ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መንገደኞችና  ወደ አገራቸው ለአጭር ጊዜ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን የ14 ቀናት ቀይታቸውን በማቆያ ማዕከላቱ ቢያጠናቅቁም፣ ከማዕከላቱ እንዳይወጡ መደረጋቸውንና ይህም ችግር እንደፈጠረባቸው በቅሬታ ለሪፖርተር ጠቁመዋል።

አንዳንዶቹ ለአጭር ጊዜ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ገልጸው፣ ከ14 ቀናት በላይ በማቆያ ማዕከላቱ እንዲቆዩ በመደረጉ የመጡበትን ጉዳይ ሳይፈጽሙ የመመለሻ ጊዜያቸው እየደረሰ መሆኑን አንዳንዶቹም ከዚህ በኋላ ጉዳያቸውን ለመፈጸም የሚያስችል ጊዜ እንደሌላቸው በመግለጽ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አጭር ምላሽ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱና የገቡ መንገደኞች የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ሲባል ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሳይዙ ከማቆያዎች እንዳይወጡ መወሰኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በማቆያ ማዕከላት ለ14 ቀናት የቆዩ ቢሆንም ነፃ መሆናቸው በምርመራ ሳይረጋገጥና ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰርቲፊኬት ሳይዙ፣ ከማዕከላትም ሆነ ለዚሁ ዓላማ ከተለዩ ሆቴሎች መውጣት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በራሳቸው ወጪ ለ14 ቀናት በሆቴሎች እንዲቆዩ የሚደረጉ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የምርመራ ውጤት ካልደረሳቸው፣ ከ14 ቀናት በኋላ ለሚኖረው ቆይታቸው የሚያስፈልገው ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በመለያ ማዕከላትና በሆቴሎች እንዲቆዩ የተደረጉ መንገደኞች ብዛት ከፍተኛ በመሆኑ የላቦራቶሪ ምርመራው ላይ መጠነኛ ጫናና መዘግየት መፍጠሩን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

‹‹ከማቆያ ማዕከላት ከመውጣታቸው በፊት ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን የቫይረሱ ሥርጭት ለመከላከል እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ፣ የሚፈጠሩ መጠነኛ ጉድለቶችን መንገደኞች በመረዳት ሊያግዙን ይገባል፡፡ መንግሥትም ምግብና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ከመሸፈን ባሻገር ችግሩን ለመቅረፍ ይሠራል፤›› ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቱ ትኩረት ያደረገው ከውጭ  ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ በሚገኙት ላይ ነው።

ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሚደረግላቸው መለስተኛ የጤና ምርመራ ከቫይረሱ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ምልክት ከታየባቸው ወደ ለይቶ ማቆያ (Isolation) ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡ ምልክቱ ያልታየባቸው፣ ሌሎች መንገደኞች ደግሞ ለ14 ቀናት ማቆያነት እንዲያገለግሉ በተዘጋጁ ሆቴሎች በራሳቸው ወጪ እንዲቆዩ፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ ለዚሁ ዓላማ እንዲያገለግሉ ተብለው በተሰናዱ ሦስት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲቆዩ እየተደረገ ነው፡፡

በሚደረግላቸው ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ግለሰቦች በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው ይታወቃል፡፡ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ለኮሮና ቫይረስ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከመረጋገጡ በፊት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በቫይረሱ ለተያዙ ሕክምና መስጫ የሚያገለግሉ 600 አልጋዎች አሉት።

ከዚህ በተጨማሪ ቦሌ የሚገኘው ሚሊኒየም አዳራሽ ለሕክምና መስጫ አገልግሎት እንዲውል የተሰናዳ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት ከ1,500 በላይ የሕክምና መስጫ አልጋዎች ገብተውለት ታካሚዎች በማጠባበቅ ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር እስከ ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 117 የነበረ ሲሆን፣ ሦስቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ሁለት የውጭ አገር ዜጎች ደግሞ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

እስከ ዓርብ ድረስ በአጠቃላይ 11,669 ሰዎች ምርምራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል ሁሉም በለይቶና በማቆያ ማዕከል የሚገኙ ናቸው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...