በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የሚገኝ ትውልድ ለመጪው ትውልድና ታሪክ የማይመች ድርጊት ሲፈጽም ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ አገርና ሕዝብ ከባድ ፈተና ገጥሟቸው በነበረበት ወቅት ሲሆን ደግሞ፣ መቼም ቢሆን ይቅር የማይባል ወንጀል ይሆናል፡፡ አሁን እያጋጠመ ያለው ፈተና እንዲህ ዓይነት በመሆኑ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በመላው ዓለም ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ከፍተኛ አደጋ በደቀነበት ወቅት ዝም ማለት አይገባም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚከፋ ፈታኝ ጉዳይ የለም ተብሎ ትኩረቱ ሁሉ ወደዚያ ቢደረግም፣ አሁንም በየጥጋጥጉ የሚፈጸሙ ሰብዓዊነት የጎደላቸው አሳዛኝ ድርጊቶች በተለያዩ ሥፍራዎች ይስተዋላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘግናኝ የሆነ ዕልቂት ያስከተለው ይህ ወረርሽኝ በሁለተኛ ዙር ጠንካራ ምቱን ሊያሳርፍ ይችላል ተብሎ ሥጋት ተፈጥሮ፣ እስካሁን በመጠኑ የደባበሳቸውን የአፍሪካ አገሮች ምስቅልቅላቸውን ሊያወጣ እንደሚችል እየተተነበየ፣ ዛሬም ከትናንቱ ጥፋት ያልተማሩና የራሳቸው ህልውና ጭምር ዕጣ ፈንታው ያልታወቀ ወገኖች ነውር እየፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በመጪው ትውልድና በታሪክ ተጠያቂ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ በዚህ ዘመን ግን በሕግ አምላክ መባል አለባቸው፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየፈጸሙ ያሉት ወንጀል ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡ ንብረት ማውደም፣ ንፁኃንን መግደልና መዝረፍ፣ በአገርና በሕዝብ ላይ ማሴር፣ በአሰልቺ ፕሮፓጋንዳ ዘረኝነትን ማቀንቀንና ሌላ ዙር መጠነ ሰፊ ግጭት በመቀስቀስ ቀውስ ለመፍጠር መዳከር የዘወትር ድርጊታቸው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሕዝብ በኮሮና ወረርሽኝ ከመጠቃት ጀምሮ የረሃብ ዕልቂት ሊያጋጥመው እንደሚችል በተለያዩ አቅጣጫዎች የሥጋት ሪፖርቶች እየወጡና ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ተብሎ አደራ ሲባል፣ በሌላ በኩል ሕዝብን ለረሃብ አገርን ደግሞ ለውድቀት የሚዳርጉ ሴራዎችን ይጎነጉናሉ፡፡ ከሴራዎች በተጨማሪ በሕዝብ ስም እየነገዱ ሰላምና ፀጥታ ያደፈርሳሉ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ነፍጥ በማንገብ ሳይሆን በሕዝብ ነፃ ፈቃድ ሥልጣን የሚያስገኘውን ቀና ጎዳና በመሸሽ፣ የሽፍትነት መንገድን የመረጡ ለማንም እንደማይበጁ የታወቀ ነው፡፡ ራሳቸውን በነፃ አውጪነት ሾመው ሕፃናትና ሴቶችን የሚያግቱ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያውኩ፣ የሕዝብ ሰላም የሚነሱና አገር የሚያመሰቃቅሉ ኃይሎች በሕግ አደብ እንዲገዙ ካልተደረገ፣ እንኳንስ ይህንን ቀውስ የሚፈጥር ወረርሽኝ ለመከላከል መደበኛ ሕይወት መምራት ያዳግታል፡፡ በሕዝብ ስም መቆመር ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ነው፡፡ ትውልድና ታሪክም ይቅር አይሉም፡፡
ሕዝብ በአገሩ ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውንም ድርጊቶች የማወቅ መብት አለው፡፡ መንግሥትም አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በሚስጥር መያዝ ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩ የሚታመንበት ጉዳይ ቢሆንም፣ አጋጣሚውን ለማያስፈልግ ዓላማ ማዋል ግን የሚወገዝ ድርጊት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግለሰቦች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ቆልለው የፈጸሙት ድርጊት፣ በዚህ ጊዜ በፍፁም መደገም አይኖርበትም፡፡ የሚያስቡ ካሉም የሕዝብ ዕይታ ውስጥ እንዳሉ ሊረዱ ይገባል፡፡ ዛሬ ጠያቂ ቢጠፋ እንኳ ነገ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መረዳት ያሻል፡፡ መንግሥት ወረርሽኙን አስመልክቶ ለሕዝብ የሚሰጠው መረጃ በሀቅ ላይ የተመሠረተና ወቅቱን የጠበቀ ሲሆን፣ ተዓማኒነቱ በየዕለቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎች ሲለቀቁም በተደራጀና አሳማኝ በሆነ መንገድ ሲያስተባብል እውነቱን ጭምር መናገር አለበት፡፡ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው የበለጠ መደናገር የሚፈጥሩና የማስረዳት ክህሎት የሌላቸውን ሹሞቹን ከሚዲያ አካባቢ ቢያርቅ ይመረጣል፡፡ እግረ መንገዱንም የተዝረከረከውን የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩን ብቁ ባለሙያዎችን ቢያሰማራበት፣ ወይም ብቃት ላላቸው የግል ድርጅቶች በጨረታ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡ ዘመኑ መረጃ በፍጥነት የሚተላለፍበት እንጂ የሚያንቀላፉ ቢሮክራቶች የሚቀልዱበት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ዛሬ ችላ ቢባል ነገ በታሪክና በትውልድ ያስጠይቃል፡፡
የመንግሥት ሕግ የማስከበር ተግባር በንቃት ሊከታተላቸው ከሚገቡት መሀል፣ ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ሕዝብ ውስጥ ውዥንብር የሚነዙ ይጠቀሳሉ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ገደብ ሊጣልበት አይገባም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች የሚፈልጉትን ሐሳብ በነፃነት ማቅረባቸው፣ ለአንድ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦ ስለሚኖረው ነው፡፡ ሰዎች በነፃነት ሲነጋገሩና የሐሳብ ልውውጥ ሲያደርጉ፣ አምባገንነትና የአንድ ወገን የበላይነት እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡ በሰዎች መካከል ክብር፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሐዊነት እንዲኖር ያግዛል፡፡ በሥልጣኔ ከገሰገሱ አገሮች ብዙዎቹ እዚህ ደረጃ የደረሱት ለሐሳብ ነፃነት በከፈሉት ዋጋ ነው፡፡ ሰዎች ነፃ ሲሆኑ ዕምቅ የሆነ የፈጠራ ችሎታቸውን ለማውጣት አይቸገሩም፡፡ ለዚህም ነው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር፣ እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል የሚያስፈልገው፡፡ ነገር ግን ‹‹የቀበሮ ባህታዊ›› ይመስል ይህንን ክቡርና ታላቅ ጽንሰ ሐሳብ ለተፃራሪ ድርጊቶች የሚጠቀሙበት ሥርዓተ አልበኞች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እስከ ስም ማጥፋት ድረስ የተሰማሩ የተደራጁ ግለሰቦችና ቡድኖች ይህንን የማይገሰስ መብት ሲያልከሰክሱት፣ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ ሕግ የማስከበር ተግባሩን ውሽልሽል እያደረገው ነው፡፡ አምባገንነትን መፀየፍ ማለት በየሥርቻው እያቆጠቆጡ ያሉ የድል አጥቢያ አርበኞችን፣ በሕግ አደብ እንዲገዙ ማድረግን ይጨምራል፡፡ ማንም አይነካኝም እያሉ ክቡር በሆነው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሥር ለመጠለል የሚሞክሩ የቀውስ ነጋዴዎች ጉዳይ የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ፣ ሥርዓት ባለው መንገድ ተንቀሳቅሶ ፈር ሊያሲዛቸው የግድ ይላል፡፡ በነፃነት ቀልድ ስለሌለ ትውልድና ታሪክ ይታዘባሉ፡፡
ሕዝብን ከአጭበርባሪዎችና ለአደጋ ከሚዳርጉት መሰሪዎች የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑ የታወቀ ስለሆነ፣ በተለይ የኮሮና ወረርኝ ሥጋት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት በእምነት ሥፍራዎችና በተለያዩ አካባቢዎች እንደ እንጉዳይ የፈሉ ማፍያዎች ጉዳይ ሌላው ዓበይት ችግር ነው፡፡ ትንቢት፣ ጥንቆላ፣ አስማትና ውዥንብር የመሳሰሉትን በመቀላቀል መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ዲስኩሮች በማድረግ፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስቱ በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒት አግኝተናል ከሚሉ ጀምሮ አካላዊ ርቀትንና የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ጥንቃቄዎችን የሚፃረሩ ድረስ፣ እጅግ ነውረኛ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መንግሥት በአገሩ የለም ወይ ያስብላል፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት የወጡ የጥንቃቄ መመርያዎች በሁሉም አገሮች እኩል ተፈጻሚ መሆን እንዳለባቸው፣ መንግሥታትም እዚህ ላይ በርትተው መሥራት እንደሚኖርባቸው ከበቂ በላይ መነገሩ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገና ከዚያም አልፎ ተርፎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ፣ ተፃራሪ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችንና ጭፍራዎቻቸውን ሕጉ እንዴት ዝም ይላቸዋል? በተፅዕኖአቸው ሥር ያሉ ወገኖችን አዳራሾች ውስጥ እያጨቁ በሕይወታቸው ላይ ሲቆምሩና ማንም አይነካንም በሚል መታበይ፣ ለዘመኑ በማይመጥን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት እስከ መቼ ድረስ ይቀጥላሉ? መንግሥት የሚያስጠይቀው ድርጊት ፊቱ እየተፈጸመ ዝም ማለት የለበትም፡፡ መጪው ትውልድና ታሪክ እንደሚወቅሱት ይገንዘብ፡፡
ሰሞኑን ከኮሮና ወረርሽኝ በተጨማሪ የበረሃ አንበጣ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡ አሁን ኮሮና የጋረጠው ችግር ሚሊዮኖችን ለሥራ አጥነትና ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያጋልጣል እየተባለ፣ የመከላከል ሥራው በአግባቡ ካልተከናወነ ዕልቂት ደግሷል ተብሎ እየተፈራና የመጪው ጊዜ ዕጣ ፈንታ ባለየበት ሁኔታ፣ ጥርስን ነክሶ ለጋራ ዓላማ ከመተባበር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በተደጋጋሚ ብዙ ተብሏል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ‹‹ቫይረሱ ከእኛ ጋር ለረዥም ጊዜ›› ይቆያል ብለው ዓለምን ሲያስጠነቅቁ፣ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ገዳይ የሆነውን ቫይረስ በጋራ ከመመከት በላይ ሌላ አጣዳፊ ተልዕኮ እንደሌላቸው፣ ከዚህ ማስጠንቀቂያ በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ የአፍቅሮተ ንዋይ ጥማትን ማርካት የሚቻለው፣ ማንንም ሳይመርጥ አፈር የሚያስግጠው ኮሮና ቫይረስ ሲወገድ ነው፡፡ በስግብግብነት የማይበሉትን ሀብት ለማከማቸት መቅበዝብም ሆነ ለቀናት ሊቆዩበት እንደሚችሉ ማረጋገጫ የሌለውን ሥልጣን በአቋራጭ ለመቆናጠጥ ማድባት፣ በኮሮና ተጠልፎ መውድቅን ሊያስከትል እንደሚችል ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለትውልድና ለታሪክ ተጠያቂነት ራስን ማጋለጥ ስለሚያሳፍር፡፡
አሁን ወሳኙ ሥራ አገርና ሕዝብን ማዳን ብቻ ነው፡፡ በክፉ ጊዜ ለሕዝብ ያልደረሰ አወዳደቁ አያምርም፡፡ ለታይታና ውለታ ፍለጋ የሚደረግ ልግስናም ሆነ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ሕዝብ ለመዝረፍ የሚደረግ አልጠግብ ባይነት ከጠላትነት አይተናነስም፡፡ ይህ ወቅት እጅግ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እንኳንስ ለቁሳዊ ሀብትና ለሥልጣን ለመንገብገብ፣ መቅሰፍቱን ተሻግሮ መጪውን ጊዜ ለማየት ማንም ምድራዊ ኃይል መተማመኛ እንደሌለው ግንዛቤ ከተያዘ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ ሕይወት በነበረው ሁኔታ ሊቀጥል ባይችልም ሰብዓዊ ፍጡራን ግን ወደፊት ስለሚኖሩና የትውልድ ጅረት መፍሰሱ ስለማይቋረጥ፣ የሚያስከብር ታሪክ መሥሪያው ጊዜ አሁን መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የሰው ማንነቱ የሚለካው በከፋ ወቅት ነውና በታሪክና በትውልድ ተጠያቂ ላለመሆን አስቀድሞ ማሰብ ብልኅነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ ጠንካሮችና ለማንም የማይበገሩ እንደሆነ፣ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ ከሆነው የዓድዋ ድል የበለጠ ምስክር እንደሌለ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ መተባበር ሲያቅታቸው ግን የአምባገነንነት፣ የድህነት፣ የኋላቀርነትና የውርደት መቀለጃ እንደነበሩ መቼም አይዘነጋም፡፡ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ትብብርን ወደ ትንቅንቅና ወደ ከንቱ ድርጊቶች መለወጥ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ፣ በትውልድና በታሪክ ይቅር የማይባል ወንጀል መሆኑን መገንዘብ የግድ ይሆናል!