Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ 88 በመቶ የሚሆኑ ሆቴሎች በኮሮና ምክንያት ሥራ እንዳቆሙ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

12 በመቶ የሚሆኑት ሆቴሎች ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች ለይቶ ማቆያ በመሆን እያገለገሉ ነው

በወር እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያጋጥም ተገምቷል

በሰሎሞን ይመር

በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ ሳቢያ የእንግዶች ቁጥር መቀነስ ያስከተለው የገበያ መዳከም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ 88 በመቶ ሥራ እንዳቆሙ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር የኮሮና ቫይረስ በኢንዱስትሪው ላይ ያስከተለውን ጉዳት ለመረዳትና የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም ያለመ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ፣ ያገኘውን ውጤት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡

በዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ በማኅበሩ ሥር ከሚገኙ 130 ሆቴሎች መካከል 56 በመቶው የኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል፡፡ 32 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎታቸውን በከፊል ለማቆም እንደተገደዱ፣  የተቀሩት 12 በመቶ ሆቴሎች ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች በለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ማኅበሩ በጥናቱ አመልክቷል፡፡

ቫይረሱ የተገኘባቸው የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘታቸው ምክንያት አስደንጋጭ በሚባል ሁኔታ ዘርፉ ችግር ውስጥ መግባቱን የሚገልጸው የማኅበሩ  የጥናት ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች የእንግዳ ቅበላ መጠን ወደ ሁለት በመቶ እንዳሽቆለቆለና በወር እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እያጋጠመ እንደሚገኝ ያስረዳል፡፡

የገበያ መዳከም ከዚህም በከፋ ሁኔታ ከቀጠለ ሆቴሎች ከፍተኛ የሆነ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት ስለሚገጥማቸው፣ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል እንደሚቸግራቸው አሳስቧል፡፡ በሥራ ላይ ለመቆየትም የሆቴል ባለሀብቶች ተጨማሪ ካፒታል ለመመደብ እንደሚገደዱ፣ ይህን ማድረግ ሳይችሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል በሪፖርቱ ሠፍሯል፡፡

ማኅበሩ ሆቴሎቹ የገቡበትን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታ ከመንግሥትና ከሌሎች ፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን እየሠራ እንደሚገኝ፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ቢንያም ብሥራት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ 82 በመቶ የሚሆኑት ሆቴሎች ከፍተኛ የብድር ጫና ስላለባቸው፣ ባንኮች የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙላቸው እየጠየቅን እንገኛለን፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ ግን ሆቴሎቹ ከፍተኛ ጉዳት ሊጋጥማቸው ይችላል፣›› ያሉት አቶ ቢንያም፣ የቫይረሱ ሥርጭት የሚጨምር ከሆነና በኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ በማሳደር ህልውናቸውን ጥያቄ ውስጥ ካስገባው ግን፣ ሠራተኞቻቸውን በመበተን ሆቴሎቹ እስከ መዝጋት እንደሚደርሱ አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ የሆቴል ባለቤቶች የመንግሥትን አቅጣጫ በመከተል ሠራተኞቻቸውን በሥራ ላይ ማቆየት ይገባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ወቅት ተደጋግፈን ማለፍ ይገባናል፡፡ ይህ ጊዜ አልፎ ወደ ቀድሞ ሥራችን በቶሎ እንደምንመለስ ተስፋ አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የቫይረሱ ሥርጭት የከፋ ሁኔታ ላይ ቢደርስ ሆቴሎችን በማስተባበር የሚገባውን ድጋፍ ለማድረግ ማኅበሩ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የሆቴል ክፍሎች ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት እንዲውሉ እስከ መፍቀድ የሚደርስ ዝግጅት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ግርማ፣ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተዋንያን በተለይም ከቱሪስቶች በሚገኝ ገቢ የሚተዳደሩ አስጎብኝ ግለሰቦች፣ በመዳረሻ አካባቢ የቱሪስት አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በሆቴሎች ላይ ብቻ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ በዋቢነት ሲያመላክቱም፣ ከ2.5 እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የአንድ ዓመት የባንክ ዕዳ ክፍያ ማራዘሚያን በሚመለከት የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች